የጥንታዊቷ ከተማ ትሩፋቶች

0
113

ታሪካዊቷ የደብረ ታቦር ከተማ ስያሜዋን ያገኘችው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ለከተማዋ መሠረት ከጣሉት አጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመን ጀምሮ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነበረች።

ደብረ ታቦር ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በጋፋት የሀገር ውስጥ ጥበብን በመጠቀም የመጀመሪያውን መድፍ የሠሩበት ታሪካዊ ቦታ እና በሀገራችን የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ መንደር (ጋፋት) መገኛ ናት።

በከተማዋ እና ዙሪያ ገባዋ የጎብኚዎችን ትኩረት የሚስቡ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የመስህብ ሀብቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከልም በ1327 ዓ.ም የተመሠረተው እና የበርካታ ቅርሶች ባለቤቱ እንዲሁም በልዩ ጥበብ የታነጸው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ነው።

ከከተማዋ አቅራቢያ የሚገኘው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ የሚነገርለት የአጼ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ሕንፃ፣ በዚህ ዘመን በአካባቢው የተተከሉት የተለያዩ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት፣ ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር የነበረው እና አጼ ቴዎድሮስ ሴባስቶፓልን ያሠሩበት ታሪካዊ ስፍራ፣ የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ቤተ-መንግሥት የነበረው ሕንፃ ቅሪትን ያሠሩት የኅሩይ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ከእነ ቅርሶቹ፣ በወቅቱ አጼ ዮሐንስ ይጠቀሙበት የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ ወንበራቸው፣ የገብርዬ ጦር እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በከተማዋ የተክሌ አቋቋም የዜማ ማስመስከሪያ የቤተክህነት ዩኒቨርስቲም ይገኛል። ደብረታቦር ብርሃን ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተወለዱባት ታሪካዊ ከተማም ናት። ለከተማዋ የውበት እና የውኃ ምንጭ የሆነው የጉና ተራራ በአቅራቢያዋ ይገኛል።

የደብረታቦር ከተማ ለወደፊቱ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ የታሪካዊ መስህብ ባለቤትም ናት። እነዚህ እና ሌሎች የመስህብ ሀብትቶች መገኛ የሆነችው ደብረታቦር ከተማ በቱሪዝሙ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በትኩረት መሥራት ይጠይቃል።

ስለሆነም የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ነው። የመምሪያው የቱሪዝም ባለሙያ ወ/ሮ ፈንታ አወቀ ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት ደብረታቦር እና አካባቢው የጎብኝዎችን ትኩረት የሚስቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ናት። በአማራ ክልል ከሚገኙ ቀደምት ከተሞች መካከል አንዷ እንደሆነች የሚነገርላት ደብረታቦር ከተማ የበርካታ ፀጋ ባለቤት እንደሆነችም አስረድተዋል። በደብረታቦር እና አካባቢው ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች መካከል አጼ ቴዎድሮስ ጥበብን ያስጀመሩበት የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር አንዱ ነው ብለዋል። የአጼ ሱስንዮስ፣ የአጼ ሰርጸ ድንግል እና የአጼ ዮሐንስ ቤተ መንግሥታት አሻራዎችም ይጠቀሳሉ ነው ያሉት። በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ የሕዝብ ፍሰቱ በሚበዛበት ቦታ የእትጌ ጣይቱን ጀግንነት ለማስታወስ “የእትጌ ጣይቱ አደባባይ” ተሰርቶ ተሰይሟል። ይህም ለቱሪዝም ፍሰቱ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። እቴጌ ጣይቱ ማን እንደሆነች እና ለሀገር ያበረከተችውን ሥራ ትውልዱ እንዲያውቅ ያደርጋልም ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ እና በአካባቢው በተለያዩ ዘመናት የተሠሩት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙም ገልፀዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የከተማዋ መለያ የሆነው የደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን ይገኝበታል። ቤተክርስቲያኑ ልዩ ጥበብ የሚስተዋልበት እና በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት መሆኑን ባለሙያዋ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ቀዳሚ ተደርጎ የሚወሰደው የተክሌ አቋቋም ዜማ ማስመስከሪያ መገኛም መሆኗንም ጠቅሰዋል። በዙሪያዋ የጉና ተራራ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ የሆነችው ደብረታቦር ከተማን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።

ሌላው የቡሄ፣ የአሸንድዬ፣ የጥምቀት እና የሆሳዕና ማርያም፣ ጥር 25 ቀን በድምቀት የተከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል እና የፈረስ ጉግሥ ባሕላዊ ጨዋታ እና ሌሎች በዓላት በከተማዋ በድምቀት ከሚከበሩት ውስጥ ይገኙበታል። እውነትም በደብረታቦር ከተማ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ ክብረ በዓላት የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ሆነው ተመልክቻለሁ። በተለይም የቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በተክሌ አቋቋም ዝማሜ፣ በወጣቶች ዝማሬ እና ሆታ፣ በፈረስ ጉግሥ እና ሽርጥ፣ በእናቶች እልልታ፣ በቄሱ ዝማሬ እና ወረብ በደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ ሥር አድምቀውት ውለዋል። የከተማዋ ነዋሪ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት በእጅጉ የሚያስደስት ሆኖም አግኝቸዋለሁ። ከሌላ አካባቢ የመጡ እንግዶችም በከተማዋ እየተዘዋወሩ ፎቶ እየተነሱ ይፈነድቃሉ። በተለይም በቅርቡ ብርሃን ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ለማስታወስ በተሠራው አደባባይ እና የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አደባባይ ላይ ፎቶ ለመነሳት ወረፋ ይዘው ይጠባበቃሉ። ይህም አስገራሚ እና ልዩ ድባብ አለው። በከተማዋ የመንገድ ዳር መብራትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች ደማቅ አድርገዋታል።

የበጌምድር መገለጫ የሆኑት ፈረሰኞች በአጅባር ሜዳ በጀግኖቹ  የሽምጥ ግልቢያ እና የጦር ውርወራ ጥበባቸውን በብቃት አሳይተዋል። ነዋሪዎቹም አጊጠው እና ተውበው እንግዶችን በክብር ተቀብለው አስተናግደዋል።

“አጅባር ከሜዳው ስር እትብቴ ተቀብሮ፣

ደብረ ታቦር ያድራል ልቤ ዞሮ ዞሮ” የተባለላት ደብረታቦር በጉና የባህል፣ ሙዚቃና ቲያትር ቡድን በከተማው ለተገኙ እንግዶች እና ነዋሪዎች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በሙዚቃ ድግስ  ሀሴትን ፈጥረዋል። ደብረታቦር ከተማ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከልም እንደነበረች ባለሙያዋ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በክልሉ የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ ወደ አካባቢው ይመጡ የነበሩ ጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን ጠቁመዋል። በዚህም የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ እንደቆየም አስታውሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ተያይዞ ቱሪዝሙ መነቃቃት ማሳየቱን ተናግረዋል። በተለይም የገና በዓልን ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ለማክበር የሚሄዱ ቱሪስቶች ደብረታቦርን ጎብኝተው ስለሚሄዱ በከተማዋ የተሻለ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል። በጎንደር፣ በወሎ እና በጎጃም መካከል እንደ መሸጋገሪያ ስለምትገኝ ለረጅም ዘመናት የንግድ ልውውጥ ማዕከል ሆናም ቆይታለች። የቡሄ በዓል በልዩ ሁኔታ መከበሩ የበለጠ መነቃቃት መፍጠሩን የተናገሩት ባለሙያዋ የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ በዓል እና የፈረስ ጉግስ ባሕላዊ ጨዋታ በድምቀት መከበሩ በከተማዋ ይበልጥ መነቃቃት መፍጠሩን አስረድተዋል።

መምሪያው ዘርፉን ለማነቃቃት እና መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር  እየሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። በሀገርህን እወቅ መርሐ ግብር  ታሪካዊ ቦታዎች እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል። መጀመሪያ ትውልዱ በአካባቢው የሚገኙ የመስህብ ሀብቶችን ማወቅ እና መረዳት ይጠበቅበታል ያሉት ባለሙያዋ በተለይ ተማሪዎቹ ማወቅ እና ለሌሎች ማሳወቅ እንዳለባቸው አመላክተዋል። ቱሪዝም ጭስ አልባው እንዲስትሪ እና አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በማልማት የተሻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲኖር በቀጣይ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል። ከተማዋን መጥተው ለሚጎበኙ እንግዶች ከጫማ ማሳመር እስከ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ድረስ እንግዶች በሚፈልጉት መንገድ አገልግሎት እንዲያገኙ ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል ሲደረግ ተመልክተናል። አገልግሎት ሰጭ ተቋማት መልካም የእንግዳ አቀባበል፣ ጥራት ያለው አገልግሎት፣ ፅዱ እና ምቹ ማረፊያ ቦታ መስጠት እንዳለባቸው በየጊዜው ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው። ይህ ሆኖም የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት ባሳዩ ተቋማት ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የተደረሰ ሥራ ተከናውኗል። የቱሪስት መስህቦችን በመጠበቅ እና በማልማት፣ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ እና ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ማራዘም እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

በፈረሶች እና ፈረሰኞች ትርዒት የደመቀው የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ዓመታዊ በዓል በታሪካዊቷ ደብረታቦር ከተማ ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ሲከበር ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መልካሙ ጸጋዬ ደብረ ታቦር የበጌምድር ፈርጥ፣ ደብረታቦር በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባት፣ የአጼ ቴዎድሮስ የህልሙ ተጋሪ ከተማ፣ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር መገኛ፣ የሊቃውንት መገኛ፣ የባሕላዊ እና የተፈጥሮ ጸጋዎች ማዕከል መሆኗን ገልፀዋል። ቢሮ ኃላፊው እንዳሉት ደብረታቦር ከተማ ታሪክ የማይሽራቸው፣ ትውልድ የሚኮራባቸው እና ቀልብን የሚስቡ ታሪካዊ እና ሃይማኖት ቅርሶች ባለቤት ናት። በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎችም ከማኅበራዊ መስተጋብር በተጨማሪ የኢኮኖሚም ምንጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ የአጼ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት እና የሴባስቶፖል ኢንዱስትሪ መንደር፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የትውልድ ሀገር የሚገኝበት ከተማ መሆኑን ጠቅሰው የበርካታ ባሕላዊ እሴቶች እና ታሪካዊ ቦታዎች ባለቤት መሆኑን ተናግረዋል።

ጥር 25 ቀን የተከበረው የቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ በዓልም ከተማዋ የሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሁነቶች ማዕከልነቷን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። የበዓሉ ማክበሪያ አጅባር ሜዳም በኪነ ጥበብ ሥራዎች ከፍ ብሎ የሚታወቅ ታሪካዊ ቦታ ነው፤ የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ የተወለደው በዚሁ ነው፣ የደጃዝማች አያሌው ጦር ከሰሜን መልስ በጌምድርን ሲረግጥ ያረፈበት ቦታም አጅባር ሜዳ ነው ብለዋል።

በዓላትን ጠብቆ፣ አልምቶ እና እሴታቸውን አጉልቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉንም ዜጋ ድርሻ ይጠይቃል ብለዋል። የሁነቶችን ክዋኔ ሰንዶ ለመያዝ፣ ጥናት እና ምርምሮችን ለመሥራትም የተቋማት ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል። በዓሉ ለደቡብ ጎንደር ብቻ ሳይሆን ለክልሉ እና ለሀገር ቱሪዝምም ትልቅ ጸጋ በመሆኑ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

መረጃ

 ደብረታቦር የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ናት።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ (ቤተመንግሥት) ሆና አገልግላለች።

ታዋቂው ንጉሠ ነገሥት አፄ ቴዎድሮስ እና አፄ ዮሐንስ 4ኛ ይህችን ከተማ እንደ መናገሻ ተጠቅመውባታል።

አፄ ቴዎድሮስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማምረት ጥረት ያደረጉበት ታሪካዊው የጋፋት ቦታ ከደብረታቦር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

በታሪክ የሚታወቀው እና “ሴባስቶፖል” የተሰኘው መድፍ የተሰራው በዚህ አካባቢ ነው።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከፍተኛ ተራራዎች አንዱ የሆነው ጉና ተራራ ከከተማዋ በቅርብ ርቀት ይገኛል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here