የዓይን ሞራ ግርዶሽ

0
80

ዓይናችን የሰውነታችን መስኮት ነው፡፡ የምንወደውን፣ የምንሳሳለትን፣ የመንኖርባትን ዓለማችንን የምናይበት ውድ ነገር ነው፡፡ ሆኖም አስፈላጊው ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ካልተደረገለት ለጉዳት መዳረጉ አይቀርም፡፡ ዓይናችን ላይ ጉዳት ከሚያስከትሉ በሽታዎች መካከልም አንዱ እና ዋነኛው የዓይንሞራ ግርዶሽ ወይም ካታራክት( cataract) ነው፡፡

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ከፍተኛ መጠን ያለው ዓይነ ስውርነትን እና የማየት እክልን የሚይዝ ዋነኛ ዓለም አቀፍ የጤና ችግር ነው፡፡ እ.አ.አ. በ 2020 የዓይን ሞራ ግርዶሽ  39ነጥብ ስድስት በመቶ ዓይነ ስውርነትን እና 28 ነጥብ ሦስት በመቶ የማየት እክል ምክንያት ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የዓይነ ስውርነት ዋነኛ መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው አብዛኛው የዓይን ሞራ ግርዶሽ የሚከሰተው በእርጅና ወይም በዓይን ሌንስ ላይ ጉዳት ሲያጋጥም ነው፡፡ እድሜ እየጨመረ ሲሄድ  በሌንስ ውስጥ ያሉት ፕሮቲኖች እና ፋይበሮች መሰባበር እና መበላሸት ይጀምራሉ፡፡ ይህም እይታን ደመናማ ወይም ደብዛዛ ያደርጋል፡፡ የዓይን ሌንስ ንጹህ መሆን ሲገባው በሆነ ነገር ደመናማ ወይም ነጣ ያለ ነገር ሲሸፈነው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተከሰተ ይባላል፡፡

ሌንስ በተፈጥሮ ንጹህ መሆን አለበት ያንን ሲያጣ፣የሌንስ መድከም ሲያጋጥም ብርሃንን በትክክል ማሳለፍ ሳይችል ሲቀር ሞራ ይከሰታል፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ (cataract )መታከም እና መከላከል ከሚችሉ የዓይን ሕመሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ነገር ግን ችላ ከተባለ ዓይነስውርነትን የሚያስከትል በሽታ ነው፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሴቶችንም ወንዶችንም የሚያጠቃ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት የየሚዳርግ የተለመደ የዓይን ሕመም ነው፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ አንድ ወይም ሁለቱንም ዓይኖች ሊጎዳ እንደሚችል ልብይሏል፡፡  በአብዛኛው በአረጋውያን ላይ በብዛት ቢከሰትም በማንኛውም እድሜ ላይ ሊመጣ ይችላል፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የማየት ችግርን በማባባስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ሊያውክ ይችላል፡፡

ምክንያቶች

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

የእድሜ 60 ዓመት በላይ መሆን (እርጅና)፣ የስኳር በሽታ መኖር፣ ለፀሐይ ብርሃን ከመጠን በላይ መጋለጥ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ ወፍራም መሆን፣

የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቅርብ ቤተሰብ ውስጥ ተከስቶ ከነበረ፣ ቀደም ሲል የዓይን ጉዳቶች ወይም እብጠት ከነበረ፣ የቀድሞ የዓይን ቀዶ ጥገናዎች፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት…ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪም በዘር የሚተላለፉ በሽታዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ ተጋላጭነትን ከፍ ሊያደርጉ ይችላል፡፡ ቀደም ሲል በሌሎች የዓይን ሕመሞች ምክንያት  የአይን ቀዶ ጥገናዎች ተደርገው ከነበረ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዳንድ የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል አቅም የሚቀንሱ መድሃኒቶችን(corticosteroid) ለረጅም ጊዜ መጠቀም ለዓይን ሞራ ግርዶሽ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ምልክቶች

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸው ሰዎች እይታቸው ደመናማ ወይም ብዥታ ይኖረዋል፡፡ (እይታቸው በደመናማ መነፅር እንደማየት ወይም  በጭጋጋማ መስኮት እንደመመልከት ነው፡፡) ለማንበብ መቸገር፣ በምሽት ለመንዳት ወይም ሰዎችን ገጽታ ለመለየት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፤

ለማንበብ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ደማቅ ብርሃን መፈለግ፣ ቀለሞችን ለመለየት መቸገር፣ በአንድ ዓይን ውስጥ ድርብ እይታ መኖር፡፡ መጀመሪያ ላይ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ምክንያት የሚፈጠረው የእይታ ደመናነት በዓይንዎ ውስጥ ያለውን የሌንስ ትንሽ ክፍል ብቻ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ምንም አይነት የእይታ መጓደልንም ላያስተውሉ ይችላሉ፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግን ሌንሱን የበለጠ ያደመናል፡፡ በእይታዎ ላይ ማንኛውንም አይነት የእይታ ለውጥ ካዩ የዓይን ምርመራ ያድርጉ፡፡

 

የዓይን ሞራ ግርዶሽ ዓይነቶች

የኑክሌር (ካታራክት)የዓይን ሞራ ግርዶሽ የመጀመሪያው ሲሆን  ይህ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የሌንስ መሃል ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ነው፡፡ የሩቅ ነገሮችን በምንመለከትበት ጊዜ ብዥታ  ሊኖር ይችላል፡፡ የቅርብ ነገሮችን ግን ማየት ያስችላል፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ሌንሱ ቀስ በቀስ ቢጫ ወይም ቡናማ ይሆናል፡፡ ይህም እይታን በማባባስ ቀለሞችን ለመለየት ፈታኝ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ሌላው የሌንስ ውጫዊ ጠርዞች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሲሆን ኮርቲካል የዓይን ሞራ ግርዶሽ በመባል ይታወቃል፡፡ ኮርቲካል የዓይን ሞራ ግርዶሽ የሚጀምረው በሌንስ ኮርቴክስ ውጫዊ ጠርዝ ላይ እንደ ነጭ፣ የሽብልቅ ቅርጽ ያላቸው ነጠብጣቦችን በመፍጠር ነው፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሾ ቀስ በቀስ እያደገ ሲሄድ ጭረቶቹ ወደ መሃል በመዝለቅ በሌንስ ውስጥ በሚያልፈው ብርሃን ውስጥ ጣልቃ ይገባሉ ይህም እይታን ይጎዳል፡፡

የኋለኛው የሌንስ ጀርባ ክፍል ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ደግሞ ንዑስ ካፕሱላር የዓይን ሞራ ግርዶሽ በመባል ይታወቃል። የኋለኛው ንዑስ ካፕሱላር የዓይን ሞራ ግርዶሽ የሚጀምረው ከሌንስ ጀርባ አጠገብ እንድ ትንሽ ቦታ ላይ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ብዙውን ጊዜ የንባብ እይታዎን ይነካል፡፡ በደማቅ ብርሃን ውስጥ እንኳ እይታዎ ሊቀንስ ይችላል፡፡ በምሽት በብርሃን አካባቢ ነጸብራቅ በማስከተል እይታዎትን ያውካል፡፡ የኋለኛው ንዑስ ካፕሱላር የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአጠቃላይ ከሌሎቹ ዓይነቶች በበለጠ ፍጥነት ያድጋል፡፡

ሌላው ሲወለዱ አብሮ የሚፈጠረው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ነው፡፡ ኮንጅኒንታል (congenital cataracts) የዓይን ሞራ ግርዶሽ ይባላል፡፡ በዘር ከወላጆች ሊወረስ ይችላል፡፡ ወይም በማሕፀን ውስጥ  በኢንፌክሽን ወይም በጉዳት ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ እንዲሁም በዓይነት 2 የስኳር በሽታ እና እንደ ኩፍኝ ባሉ  አንዳንድ የጤና እክሎች ምክንያት የሚፈጠር የአይን ሞራ ግርዶሽ መኖሩም ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሕክምናዎቹ

ለዓይን ሞራ ግርዶሽ የተለያየ አይነት  ሕክምናዎች ቢኖሩም በዋናነት የሚሰጠው ግን ቀዶ ጥገና ነው፡፡ በተለምዶ መጠረግ ይባላል፡፡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ከሌሎች የዓይን ቀዶ ጥገናዎች በተለየ ውጤታማ ነው፡፡ ቀዶ ጥገናዉም  ከ30 እስከ አንድ ሰዓት ሊወስድ ይችላል፡፡ እንደማንኛውም የበሽታ ቀዶ ጥገናዎች የራሱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡

መከላከያዎቹ

የዓይን ሞራ ግርዶሽን  እንዴት መከላከል ወይም መቀነስ እንደሚቻል የሚያሳዩ ጥናቶች የሉም፡፡ ሆኖም የጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች የሚከተሉትን ጨምሮ በርካታ ስልቶች ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ፡- መደበኛ የዓይን ምርመራዎችን ማድረግ፡፡ ምክንያቱም የዓይን ምርመራዎች የዓይን ሞራ ግርዶሽ እና ሌሎች የዓይን ችግሮችን አስቀድመው ለመለየት ይረዳሉ፡፡

በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስን ማቆም፣ ብዙ አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዘውትሮ መመገብም ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በአመጋገብዎ ውስጥ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ማካተት ብዙ ቪታሚኖችን እና ንጥረ ነገሮችን ያገኛሉ፡፡ ፍራፍሬዎችና አትክልቶችም የዓይንዎን ጤንነት ለመጠበቅ የሚረዱ አንቲኦክሲደንትስ አላቸው፡፡ በቪታሚኖች እና ማዕድናት የበለፀገ ጤናማ አመጋገብ የዓይን ሞራ ግርዶሽ የመያዝ እድልን ይቀንሳል፡፡ የፀሐይ መነፅር ያድርጉ፡፡ ከፀሐይ የሚመጣው አልትራቫዮሌት ጨረር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በመሆኑም ከቤት ውጭ በሚሆኑበት ጊዜ አልትራቫዮሌት ቢ ጨረሮችን የሚከለክሉ የፀሐይ መነፅር ያድርጉ፡፡የአልኮል መጠጦችን ይገድቡ፡፡ ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት የዓይን ሞራ ግርዶሽ የመያዝ እድልን ይጨምራልና፡፡

 

ጤና አዳም

-በምሥራቅ ሜዲትራኒያን ክልል ከ51በመቶ በላይ የሆነው ዓይነ ስውርነት የተከሰተው በዓይን ሞራ ግርዶሽ ነው፡፡

-በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የዓይን ሞራ ግርዶሽ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

-ምንም እንኳን የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀላሉ በቀዶ ጥገና ሊታከም ቢችልም ብዙ ሀገሮች የዓይን እንክብካቤ ተደራሽነት ውስን ነው፡፡

-እ.አ.አ. ከ2026 ጀምሮ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 45በመቶ የሚጠጋ ዓይነ ስውርነት ሊያስከትል እንደሚችል ተተንብዩአል፡፡ ይህም 15 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፡፡ በተጨማሪም 39በመቶ ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከባድ የእይታ እክል ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህም ወደ 78 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ግለሰቦችን ይጎዳል፡፡

መንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት፣contactlenses.co.uk

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here