ልጆች እንዴት ሰነበታችሁ? እረፍት ጥሩ ነበር? ልጆች በጥር ወር የተለያዩ በዓላት ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ስለሚከበረው የአገው ፈረሰኞች በዓል እንገራችሁ፡፡
ፈረስ በአዊ ብሔረሰብ የሚከበር እና ውለታው ሁሌም የሚዘከር ድንቅ እንሰሳ ነው። ይሄ ድንቅ እንሰሳ ለክብረ በዓል እና ለልዩ ልዩ ዝግጅት በሚፈለግበት ጊዜ ተውቦ እንዲታይ እና ለጋላቢው ምቾት እንዲሰጥ የተለያዩ ጌጣጌጦች እና አልባሳትን እንዲለብስ ይደረጋል።
የአገው ፈረሰኞች በዓል በሚከበርበት ጊዜ የፈረሶች አለባበስ እና አጋጊያጥ እጅግ የተለየና ማራኪ ነው። ለበዓሉ ፈረሶቹ አምረው እንዲታዩ እና ለጋላቢው እንዲመቹ መጣምር (ከቆርቆሮና ከቆዳ ውጤቶች የተሰራ ፋርኔሳ)፣ የፈረሱ አንገትና ከጀሮ በላይ ጌጥ(ውዴላ)፣ ኮርቻውን በኋላ በኩል የሚይዘው (እምቢያጉስም)፣ ደረቱ ላይ የኮርቻውን ቀዳማ የሚይዘው እና በኮርቻው ላይ መቀነቻ (ቀበቶ) ይደረግላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ለኮ(የፈረሱ መሳቢያ ልጎም)፣ የፈረሱ መሪ እና ፈረሰኛው ሲቀመጥ ግራና ቀኝ እንዳይሸራተት በእግሩ የሚረግጠው እርካብ ይሟላሉ፡፡
በተዋበው ፈረስ ላይ የሚቀመጠው ፈረሰኛ ደግሞ ሎፊሳ(ለምድ ከዱር እንስሳት የሚገኝ ቆዳ)፣ ጀበርና(ፈረሰኛው ወገቡን የሚታጠቀው)፣ ገምባሌ(ለእግሩ ባቱ መከላከያ)፣ የጉሽ ባርኔጣ፣ በጉግስ ውድድር ጊዜ ጋሻና አብሮት የሚገጥመው ሁለት መውጊያ ዘንጎችና ለፈረሱ ማባረሪያ ጉማሬ አለንጋ ይይዛል፡፡
በአገው ፈረሰኞች ክብረ በዓል ወቅት በዓሉን የሚያስተባብሩት አጋፋሪዎች ወይም አለቃዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በመያዝ ሥነ-ስርዓቱን ይመራሉ፡፡ ሲመሩም “አይሞሎ፣ የዳማ ጌታ፣ ጀምር ጨዋታ፤ አይሞሎ የጥርኝ ጌታ፣ በል ጋሻ ምታ ወዘተ” እያሉ ፈረሱን እያሞገሱ በማቀንቀን ፈረሰኛውን ያስጨፍራሉ፡፡ በዓሉንም በድምቀት ያከብራሉ።
የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል መከበር የጀመረው ከ1933 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ማህበሩ የተቋቋመው በ32 አባላት ሲሆን አሁን ላይ ከ62 ሺህ በላይ አባላት አሉት። በዓሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሃገር ውስጥ እንዲሁም የውጪ ጎብኚዎችን የሚስብ ነው ሲሉ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ቃልዓብ ከሃሊ ነግረውናል።
በዓሉ በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (በዩኔስኮ) ለመመዝገብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህን ተከትሎም በርካታ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ወደስፍራው የመጓዝ ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን መጥቷል።
ሕጻን ማሕሌት እሱነው በእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ናት፡፡ የአንደኛ ክፍል ተማሪም ናት፡፡ የአገው ፈረሰኞች በዓል ስታከብር አግኝተናታል፡፡ ፈረስ እንደምትወድ የነገረችን ማህሌት በምስሉ እንደሚታየው በአገው ባሕላዊ አልባሳት ደምቃ ተገኝታለች፡፡ በእድሜ ከፍ ስትል ፈረስ መጋለብ እና በበዓሉ ዋና ተሳፊ መሆን እንደምትፈልግ ነግራናለች፡፡
ተረት
ረባሹ ወይፈን
ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጋ የቀንድ ከብቶች የነበሩት አንድ ከብት አርቢ የሆነ ባለፀጋ ሰው “እነሆ ከጥቂት ቀን ወዲህ ከብቶቼ ሌሊት ለሊት በበረታቸው ውስጥ እርስ በእርሳቸው እየተተራመሱ ሲታወኩ ያድራሉ። ከዚህም ቀደም በመካከላቸው ይህን የመሰለ ሁከት አልነበረም። አሁን ግን ይህ የሆነበት ምክንያት ጠፍቶኛል፤ ምን ይሆን” ብሎ ጎረቤቶቹን ቢያማክራቸው፤ አስተዋይ የሆነ አንድ ሽማግሌ “ለዚህ ነገር ብልሃቱ አጭር ነው። ሌላ ትልቅ በረት አሰርተህ ከብቶችህን ከሁለት ክፈላቸውና ለየብቻ አሳድራቸው” አለው። ባለፀጋውም ሽማግሌው እንዳለው አደረገ።
ይህንን ባደረገ በማግስቱ “ከብቶችህ ዛሬስ እንደምን አደሩ” ብሎ ቢጠይቀው፤ “ያንደኛው በረት ከብቶች ደህና አደሩ፣ ያንደኛው ግን ሲተራመሱ አደሩ” ብሎ መለሰለት። “በል አሁን ከግሞ ሌላ ሶስተኛ ትልቅ በረት አሰርተህ ሲታዎኩ ያደሩትን ከብቶች ከሁለት ከፍለህ ለየብቻ አሳድራቸው” አለው። አሁንም ደግሞ ባለፀጋው እንዲሁ ሽማግሌው እንደመከረው አደረገ። በማግስቱም ቢጠይቀው “ባንዱ በረት ያሉት ከብቶች ድህና አደሩ ባንደኛው የነበሩት ግን ሢበጠበጡ አደሩ” አለው። ሽማግሌውም መለሰና “እነዚያን ደህና ያደሩትን ከፊተኞቹ ጋር ቀላቅለህ ሲታወኩ ያደሩትን ከብቶች አሁንም ከሁለት ክፈላቸውና ለየብቻ አሳድራቸው” አለው። እንዲሁ እያደረገ የታወኩትን ከብቶች ከሁለት እየከፈለ ደህና ያደሩትን ግን ለብቻ ለይቶ ከደህኖቹ ጋር እየቀላቀለ ስድስት ጊዜ ይህንን ስራ ደጋግሞ ከሰራ በኋላ በመጨረሻ ከሚተራመሱ ከብቶች ወገን አስር ብቻ ቀሩ።
“በነዚህ በአስሩ ከብቶች መካከል የቀሩትን ሁሉ የሚበጠብጡ ሁለት ወይም ሶስት ከብቶች ሳይሆኑ አይቀርምና ሌሊት ጨረቃ ስትወጣ ጠብቀህ ከዳር ቆመህ ከብቶችን ተመልከታቸው” አለው። እውነትም ባለጠጋው ሽማግሌው እንደመከረው አድርጎ ቢመለከት በከብቶቹ መካከል እየሮጠ ሌሎችን እየወጋ ፀትታ ነስቶ ሁሉንም የሚበጠብጣቸው አንድ ወይፈን መሆኑን አየ። “እንግዲህ ይህን ወይፈን ወይም ሽጠው ወይም እረደው” አለው። ወይፈኑም ከከብቶቹ መካከል ከተወገደ በኋላ ከብቶቹን ሁሉ መልሶ እንደ ቀድሞዋቸው ቢቀላቅላቸው ረግተው በሰላምና በፀትታ ያድሩ ጀመር። እነዚህን ሁሉ ከብቶች የሚበጠብጣቸው አንድ ወይፈን እንዳለ ሁሉ በሰዎችም መካከል ሰላምና ስምምነት ጠፍቶ ሁከትና ብትብጥ ሲነሳ ነገሩን ሁሉ እያጣሩ ቢመረምሩት እንዲሁ ሆኖ እንደሚገኝ አያጠራጥርም።
ምንጭ:- ታሪክና ምሳሌ (ከበደ ሚካኤል)
ሞክሩ
- ለሴት ፈረስ የተሰጠ መጠሪያ ምን ይባላል?
- አንድ ግንድ ሁለት ትክሻ ላይ ይጓደዳል፤ ምንድን ነው?
- በቀይ ባህር ውስጥ ነጭ ወይም ጥቁር ወረቀት ቢጣል ምን ይሆናል?
መልስ
1.ባዝራ
2.ቀንብር
3.ይረጥባል
ነገር በምሳሌ
-ለሞኝ ሰኔ በጋው፣ መስከረም ክረምቱ- ሞኝ ማድረግ የሚገባውን ነገር በትክክል በወቅቱ አይሰራም::
-ሲጎርሱ በልክ ሲታጠቁ በጥብቅ- ሁሉም ነገር በወግ በማዕረጉ ያመራል፡፡
-ሁሉም ሸክሙን ፍቅርም ያዥውን- ሸክም ለተሸከመው ሰው ነው የሚታወቀው ፍቅርም የያዘው ሰው ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


