አፍሪካን ዋጋ እያስከፈለ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ

0
65

በቅርቡ በአፍሪካ የተከሰተው ከባድ ዝናብ እና  የአህጉሪቱን ደቡባዊ ክፍሎች ያወደመው  የጎርፍ  አደጋ  በሰው ልጅ ምክንያት መሆኑን ተመራማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ጎርፉ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን ሲገድል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል፡፡

አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው በደቡብ አፍሪካ፣ በሞዛምቢክ እና በዚምባብዌ የጎርፍ አደጋ ያስከተለውን የቅርብ ጊዜ ከባድ ዝናብ የተነተነው የዓለም የአየር ንብረት ድርጅት ጥናት እንዳመለከተው ክልሉ በ10 ቀናት ውስጥ የአንድ ዓመት የዝናብ መጠን አጋጥሞታል፡፡ ይህም በመኖሪያ ቤቶችና በመሠረተ ልማት ላይ  ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ የሰብአዊ ድርጅቶች ደግሞ የተፈናቀሉ ሰዎች በረሃብ፣ በወረርሽኝ እና በደረሰው ውድመት ምክንያት የጤና አገልግሎት እጥረት አጋጥሟቸዋል እያሉ ነው፡፡

የተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች የደረሱት ታኅሣሥ አጋማሽ እና ከጥር ወር መግቢያ ጀምሮ ተጠናክሮ በቀጠለው እጅግ ከባድ እና የማያባራ ዝናብ ምክንያት ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በአንድ ቀን ብቻ ከ200 ሚሊ ሜትር በላይ የዝናብ መጠን መመዝገቡም ታውቋል፡፡

በዚህም ምክንያት በመኖሪያ ቤቶች እና በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል፡፡ ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸው ተገልጿል፡፡

በሞዛምቢክ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕንፃዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ እና በዚምባብዌ ደግሞ መንገዶች እና ድልድዮች መውደማቸውን ከአከባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በሞዛምቢክ በርካታ መኖሪያ ቤቶችና ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ በውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችም ወድመዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የሊምፖፖ እና የማፑማላንጋ ግዛቶች እንዲሁም በዚምባብዌ በሚገኙ አንዳንድ የሀገሪቱ  ክፍሎች መንገዶችና ድልድዮች በጎርፍ መወሰዳቸው ነው የተነገረው፡፡ የዝናብ መጠኑ በ50 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ የሚከሰት መሆኑም ነው የተጠቀሰው፡፡

በአየር ንብረት ላይ ጥናት ያደረጉ የዘርፉ ተመራማሪዎች በሰው ምክንያት የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥ ከሌለ በስተቀር የዝናብ መጠኑ በ40 በመቶ ሊጨምር እንደማይችል ነው የተናገሩት፡፡ በመሆኑም ይህን ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የሰው ልጅ ተፈጥሮን በመጉዳቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካ ከዓለም አቀፉ የበካይ ጋዝ የልቀት መጠን ከሦስት በመቶ እስከ አራት በመቶ ብቻ ድርሻ ያላት ቢሆንም ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች በጣም ተጋላጭ ከሆኑት መካከል አንዷ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ እና እንደ አውሎ ነፋሶች ያሉ ቀደም ሲል የደረሱት ቀውሶችም በአብዛኛው ምጣኔ ሀብታቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሀገራት ላይ ከመቶ ሚሊዮን እስከ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት አስከትለዋል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ ለሚደርሱ አውዳሚ አደጋዎች ለአፍሪካ ድጋፍቸውን እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡ የዝናብ መጠኑ ከሚጠበቀው በላይ በመሆኑ በደቡብ አፍሪካ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በጎርፍ አደጋ መጎዳታቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ጠቁሟል፡፡

በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ የተጎዱ አካባቢዎች ለከባድ ዝናብና ለጎርፍ እንግዳ ባይሆኑም ነገር ግን ሳይንቲስቶች በቅርብ ጊዜ በተከሰቱት የዝናብ መጠን መደንገጣቸው ነው የተነገረው፡፡ “ይህ ክስተት ለእኛ አስገራሚ ነበር፤ ከ25 ዓመታት በፊት የነበረው ድጋሚ  አጋጥሞናል፣ ይህም ተመሳሳይ አካባቢዎችን በጎርፍ አጥለቅልቋል” ሲሉ የሞዛምቢክ የአየር ሁኔታ አገልግሎት ተመራማሪ የሆኑት በርናርዲኖ ንሃንቱምቦ ተናግረዋል፡፡

“በመላው የዝናብ ወቅት የሚጠበቀውን ዝናብ ከሁለት እስከ ሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ያስመዘገቡ ቦታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን በማንኛውም ሁኔታ ለማስተናገድ በጣም ፈታኝ ነበር” ሲሉ የአደጋውን ከባድነት አስረድተዋል፡፡ “ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ወንዞች ወደ ሞዛምቢክ የሚፈሱ ሲሆን ከባድ ዝናብ እንዲሁም በጅረቱ ፍሰት ምክንያት እንዲህ አይነት ክስተትን ተከትሎ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስ ይጠበቃል” ሲሉ ንሃንቱምቦ ተናግረዋል፡፡

እ.አ.አ በ2024 በዓለም ታሪክ ከፍተኛው ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የሙቀቱ መጠንም በአንድ ነጥብ ሁለት ዲግሪ ሴልሺየስ ነበር የጨመረው፡፡ ታዲያ አፍሪካም እንደ ዓለም አቀፉ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት መረጃ እ.አ.አ ከ1991 እስከ 2022 ባለው ሦስት ዐሥርት ዓመታት  በአማካይ የዜሮ ነጥብ ሦስት ዲግሪ ሴልሺየስ የሙቀት ጭማሪ ተመዝግቦባታል፡፡

የአሜሪካው ብሩኪንግስ የጥናት ተቋም እንዳሳወቀው በተያዘው የጎርጎሮሳዊያኑ ዓመት (በ2026) አፍሪካ በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ የአየር ንብረት ተግዳሮቶች ይገጥማታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚህም በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትና እጦት እና የኢኮኖሚ ኪሳራዎች ይጨምራሉ ተብሏል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ መንግሥታዊ ፓነል (አይ ፒ ሲ ሲ) እንደዘገበው ባለፉት 60 ዓመታት አፍሪካ ጉልህ የሆነ የሙቀት መጨመር አሳይታለች፡፡ ይህም እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ያሉ ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች እንዲያጋጥማት አድርጓል፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በየዓመቱ ከ520 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እንደሚደርስባቸው አሳውቋል፡፡ እ.አ.አ በ2026 እነዚህ የኢኮኖሚ ኪሳራዎችም ይጨምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም መሰረታዊ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን ይጎዳል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 282 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን የምግብ ዋስትና እጦት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዘግቧል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርታማነት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን እያባባሰ ይሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እ.እ.አ በ2030 እስከ 118 ሚሊዮን የሚደርሱ እጅግ በጣም ድሃ ሰዎች  በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አስከፊ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ይገመታል፡፡  ይህም የድህነት ቅነሳ ጥረቶችን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርጋል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የሜትሮሎጂ ድርጅት (wmo) ገለጻ በአፍሪካ የአየር ንብረት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም  በሚቀጥሉት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከአህሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ የሚሆነውን ይወክላል፡፡  የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ተጽዕኖዎች በተሻለ ሁኔታ ለመዘጋጀት በሜትዎሮሎጂ አገልግሎት እና በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ላይ ኢንቨስትመንቶችን ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ሜትዎሮሎጂ ድርጅት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥ የአፍሪካን ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ጥቅል ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) ወጪ እየወሰደ ይገኛል፡፡ የአፍሪካ የግብርና ምርታማነት እ.አ.አ ከ1961 በኋላ በ34 በመቶ መቀነሱን የዓለም ሜትዎሮሎጂ ድርጅት የ2024 የአፍሪካ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በተያያዘም ካርቦን ብሪፍ ኦርጋናይዜሽን የሚባል ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ የአየር ንብረት ለውጥ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት በአፍሪካ በወባ ምክንያት ግማሽ ሚሊዮን ተጨማሪ ሞት ሊያስከትል እንደሚችል አዲስ ጥናት ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡ ይህ ጥናት  እንደሚያሳየው ከባድ የአየር ሁኔታ፣ የሙቀት መጨመር እና የዝናብ መጠን መቀያየር በአፍሪካ ተጨማሪ 123 ሚሊዮን የወባ በሽታን ሊያስከትል ይችላል፡፡

የጥናቱ ተሳታፊዎች የአየር ንብረት ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ እንደ ጎርፍ ያሉ አውዳሚ የአየር  ሁኔታዎች በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል እየተባባሱ እንደሚሄዱ፣ የወባ ሕክምና ፕሮግራሞችንም በስፋት እንደሚያስተጓጉሉ እና በመኖሪያ ቤቶች ላይም ጉዳት እንደሚያደርሱ ያስረዳሉ፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው እነዚህ መስተጓጎሎች የወባ ስርጭት ስጋትን 79 በመቶ እና በበሽታው ምክንያት ከሚከሰቱት ተጨማሪ ሞት 93 በመቶውን ይሸፍናሉ፡፡

በሚቀጥሉት 25 ዓመታት ውስጥ የወባ በሽታ የሚጨምረው  በሙቀት መጠን መጨመር እና በዝናብ መጠን መቀያየር ምክንያት ሲሆን ይህም በሽታውን የሚሸከሙትን ትንኞች የመኖሪያ ክልል ይለውጣል፡፡ በዚህም አብዛኛዎቹ አዳዲስ የወባ በሽታዎች የሚከሰቱት ቀደም ሲል ለወባ በሽታ ተስማሚ በሆኑ አካባቢዎች ሳይሆን በአዲስ ክልሎች ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት   እንዳስታወቀው  በ2024 በበሽታው ምክንያት 610 ሰዎች ሞተዋል፡፡ አፍሪካም 95 በመቶ የወባ በሽታ እና ሞት መገኛ ነበረች፡፡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትም በአፍሪካ ውስጥ ካሉት የወባ ሞት ሦስት አራተኛውን ይሸፍናሉ፡፡ ጥናት አድራጊዎቹ የአየር ሁኔታ በከፍተኛ መዛባት ብዙውን ጊዜ ሰፊ የሆነ መስተጓጎል እንደሚያስከትል እና ይህም የጤና አጠባበቅ ተደራሽነትን ሊገድብ፣ መኖሪያ ቤቶችን ሊጎዳ ወይም እንደ የወባ ትንኝ የመከላከያ እርምጃዎችን ሊያስተጓጉል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here