በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ (2004) መሠረት የዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጡ ወንጀሎች በአብዛኛው የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት እና ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያካተቱ ናቸው። እነዚህም የሽብር ወንጀሎች፣ በከባድ ሁኔታ የተፈጸመ ግድያ፣ ከፍተኛ ክህደት እና በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ እጅግ ከባድ ጥፋቶችን ያጠቃልላል።
በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 ላይ እንደተመላከተው በከባድ ሁኔታ የተፈጸመ ሰው መግደል በተለይም በግፍ፣ በጭካኔ ወይም በታቀደ ሁኔታ የተፈጸመ ግድያ በዕድሜ ልክ እስራት ያስቀጣል።
የዕድሜ ልክ እስራት በሕጉ የሞት ፍርድ ካልተተገበረ ከፍተኛው ቅጣት ሲሆን፣ እንደ ጥፋቱ ክብደትም ይወሰናል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በ2017 ዓ.ም አጋማሽ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት የነበሩት የዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ ኅዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም የ25 ኣመት ጽኑ እስራት ቅጣት ውሳኔ ሰጥቶ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ዐቃቤ ሕግ የቅጣት ውሳኔውን ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ነበር፤ የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ የመደበኛ ወንጀል ጉዳዮች የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሀብታሙ አዲስ እንደተናገሩት ተከሳሹ እሱባለው ነበረው ወይም ደግሞ በሌላ መጠሪያው ሳሙኤል ነበረው ካልተያዘው ግብረ አበሩ ሀብታሙ ጌትነት ጋር ወንጀሉን ፈጽመዋል።
የሥራ ሂደት አስተባባሪው እንዳብራሩት ተከሳሹ በሦስት ጉዳዮች ነበር የተከሰሰው፤ ሞትን ያስከተለ ከባድ የውንብድና ወንጀል፣ በተመሳሳይ ቀን እና ቦታ ዶክተር አንዱዓለም ዳኘን ከመግደሉ በፊት ዶክተር በረከት አማረ የተባሉትን ሌላኛው የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሐኪም በጥይት ተኩሶ መሳት እና ተከሳሹ ራሱን ለመደበቅ እንዲመቸው በሀሰት የተዘጋጁ የቀበሌ መታወቂያዎችን ይዞ ሲገለገል መገኘቱ ናቸው፤ ይህም በምርመራ በመረጋገጡ “የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ ሦሥትን ተላልፏል በሚል በባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ ክስ ቀርቦ ነበር” ብለዋል።
በሀገራችን የወንጀል ሕግ እንደተቀመጠው እስራት በሦስት ይከፈላል፤ ፅኑ_እስራት፣ ቀላል እስራት_እና የማረፊያ_ቤት_እስራት_ናቸው:: የእስራት ፍርዱም እንደ ወንጀሉ ዓይነት ይወሰናል:: ቀላል እስራት ከባድነታቸው መካከለኛ ለሆኑ ወንጀሎችና ለሕብረተሰቡ አደገኛ ላልሆኑ ወንጀሎች የተደነገገ የቅጣት ዓይነት ነው:: የቀላል እስራት ቅጣቱ መነሻ ዐሥር ቀን የላይ ጣሪያው ደግሞ እስከ ሦስት ዓመት ይደርሳል::
ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ የቀላል እስራት ጊዜ ከዐሥር ቀን እስከ ሦስት ዓመት ቢሆነም በተለያዩ ምክንያቶች የቀላል እስራት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ እንደሚችልም በወንጀል ሕጉ ተመላክቷል::
የማረፊያ ቤት እስራት የሚባለው ደግሞ ደንብ ተላልፈው የተገኙ ሰዎች ሊጣልባቸው የሚችለው ዓይነት እስራት ነው:: ይህ የእስራት ዓይነት በማረሚያ ቤት ሊፈፀም የማይችል ሲሆን ጠቅላላ አፈጻፀሙም ወንጀል ፈፅመው በእስራት እንዲቀጡ ከተፈረደባቸው ሰዎች የቅጣት አፈጻጸም የተለዬ ነው::
በሌላ በኩል ፅኑ እስራት ለከባድ እና ለሕብረተሰቡ አደገኛ በሆኑ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰን የቅጣት ዓይነት ነው:: የፅኑ እስራት ዘመን እስከ ወንጀለኛው የዕድሜ ፍፃሜ ድረስ ሊቀጥል ይችላል::
ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ የተገደሉበት መንገድ ከባድ እና በሕብረተሰቡ ዘንድ አደገኛ የሆነ ወንጀል እንደሆነ ነው የተመላከተው::
የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ የመደበኛ ወንጀል ጉዳዮች የሥራ ሂደት አስተባባሪው ሀብታሙ አዲስ እንደተናገሩት የመጀመሪያው ክስ ብቻ ሞትን ያስከተለ ከባድ ውንብድና በመኾኑ በአንቀጽ 671 ንዑስ 2 ላይ ያለው በሞት ሊያስቀጣ የሚችል ነው። የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ግን ተከሳሽን አያስተምርም፣ በዐቃቤ ሕግ በኩል ተጠቅሰው የነበሩ አንቀጾች መቀየራቸውን በማንሳትም በዐቃቤ ሕግ በኩል የተከሳሽ ውሳኔዎች እንዲከብዱ የቅጣት ማክበጃ ሀሳቦች ውድቅ የተደረጉ ስለሆነ ቅጣቱ ሊሻሻል ይገባል ብሎ የሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ እንደነበር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ይግባኙ ይቀርባል ካለ በኋላ ተከሳሽ መልስ እዲሰጥ ተደርጎ ክርክር ሲካሄድ ከቆዬ በኋላ ጥር 22 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰጥቶት የነበረውን የ25 ዓመት ጽኑ እስራት በማሻሻል ተከሳሹ የዕድሜ ልክ ቅጣት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።
ወንጀሉ ውሥብሥብ እና የተደራጀ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ አዲስ መንግሥት ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት መሠረት የፍትሕ ቢሮ መሪዎች ከፖሊስ ኮሚሽን እና ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በልዩ ሁኔታ በመከታተል ተከሳሽ በአጭር ጊዜ ተይዞ ፍርድ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዶ/ር አንዱዓለም ዳኜ የመታሰቢያ መርሃ ግብር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል፤ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ዶ/ር አንዱዓለም ለሕክምና ሙያ የተፈጠረ ልዩ ተሰጥኦ የነበረው እና እጅግ ምጡቅ አዕምሮ (Brilliant mind) የታደለ ባለሙያ እንደነበር መግለጻቸውን ከዩኒቨርሲቲው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የናይል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው “በአጭር ህይወት ውስጥ በማያልፍ ዕሴት የማሰብ ጥበብን ከዶ/ር አንዱዓለም ተምረናል” ብለዋል። እንደ ዶ/ር አንዱዓለም ህያው የሆነ ሥራ ሠርቶ ማለፍ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
መረጃ
የሴት ልጅ ግርዛት እና ሕጉ፦
- የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ የሴት ልጅ ግርዛትን እንደ ወንጀል ይደነግጋል። ማንኛውም በሴት ልጅ ላይ የሚደረግ አካላዊ ጉዳት፣ ህግ በሚከለክላቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ስር ተካቶ ከባድ ቅጣት አለው።
- ምክንያቶች:- ባሕላዊ እምነቶች፣ ድንግልናን ለመጠበቅ በሚል፣ ከትዳር ታማኝነት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች።
- መፍትሔዎች:- ሕጉን ተፈጻሚ ከማድረግ ጎን ለጎን የህብረተሰቡን አመለካከት በመቀየር፣ የጤና ባለሙያዎችንና አመራሮችን በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ይሰራል።
በአጠቃላይ፣ የሴት ልጅ ግርዛት በህገ-መንግስቱ ጥበቃ ያገኙትን የአካል ደህንነት እና በህይወት የመኖር መብት የሚፃረር ድርጊት ነው።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


