ይሉኝታን በልኩ

0
94

ይሉኝታ የሚለው ቃል በአማርኛ ፍችው “እንዲህ ይሉኛል! ብሎ ማሰብ፤ ትዝብትን፣ ሃሜትን እንዲሁም ነቀፌታን መፍራት” ማለት ነው። ይሉኝታ በዓለም አቀፍ የስነ-ማህበራዊ ሳይንስ ውስጥ ደግሞ “Politeness, Face, Shame, Honor, Deference, Social harmony” በሚል መልኩ በሰፊው ተፅፎበታል፤ተጠንቷል።

ይሉኝታ ሰዎች ምን ይሉኛል በሚል ሰበብ፤ የራስን ፍላጎት ገትቶ ሌሎችን ለማስደሰት መጣር፤ ሌሎችን ማስቀደም ማለት ነው።

ይሉኝታ የሚያጠቃቸው ሰዎች ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት እና ግዴታ በላይ የሌሎችን ጉዳይ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። ይሉኝታ የራሳችንን ሥራና አጀንዳ ወደ ጎን አድርገን፤ ፍላጎታችንን እና ምርጫችንን ተጭነን ሌሎችን ለማስደሰት የመፈለግ ውጤት ነው።

በማህበራዊ ሳይንስ መስክ ይሉኝታ “ሰው ሌላን ሰው እንዳያስቆጣ፣ እንዳያሳፍር ወይም እንዳይጎዳ ስሜቱንና አስተያየቱን በግዴታ የሚገድብበት ነው” የሚል ፅንሰ-ሃሳባዊ ትርጓሜም ተሰጥቶታል። ይሉኝታ ሁለት ጎኖች ያሉት ባህላዊ እሴት ነው። በመሆኑም አዎንታዊ እና አሉታዊ ገፅታዎቹ ታዲያ በአግባቡ መያዝ ይገባቸዋል።

የይሉኝታ መንስዔዎች

አስተዳደጋችን በይሉኝታ የታሰርን እንድንሆን መሠረት ይጥላል። ያደግንበት ቤተሰብ ሰዎችን ማስደሰት እንደ ትልቅ መርህ የሚያይ ከነበረ፤ ወይም ደግሞ ቤተሰባችን ውስጥ በረባ ባልረባው የሚቆጣ ሰው ከነበረ ያንን ሰው ለማስደሰት ፍላጎታችንን እየተጫን እናድጋለን። ይህ ያደግንበት ሁኔታ በእኛ ላይ ሰርፆ ለይሉታ ተገዢ ያደርገናል። ልክ እንደ ቤተሰብ ሁሉ ያደግንበት ማህበረሰብም ለይሉኝታ መሠረት ይጥላል። በመሆኑም በማንኛውም መንገድ ለመረዳዳት ትኩረት በሚሰጥ እና ያለንን ለማካፈል “እሺ ባይነትን” አንደ መልካም ባህሪ መውሰድን፤ እምቢ ባይነትን ደግሞ እንደ እኩይ ባህሪ የመውሰድ ልማድ ያደግንበት ማህበረሰብ ነፀብራቅ ሆኖ በህይወት ዘመናችን ይገለጻል። ከመጠን በላይ የሆነ የሌሎችን ሰዎች ተቀባይነትና ትኩረት ለማግኘት መሻት፣ በራስ አለመተማመን፣ ሌሎች ስለኛ የሚያስቡት ጥሩ ብቻ እንዲሆን መጨነቅ እና የውስጥ መረጋጋት እጦት የይሉኝታ መንስዔዎች ናቸው።

የይሉኝታ   መገለጫዎች

ይሉኝታ በቃል፣ በተግባር፣ በአመለካከት እና ማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ በተለያዩ ባህሪያት ይገለፃል። የራሳችንን ሃሳብ ውድቅ አድርገን፤ ከሰዎች ሃሳብ ጋር ሁልጊዜ መወዳጀት ቀዳሚው የይሉኝታ መገለጫ ነው።

ሃሳባችንን ስንገልጽ ላመንበት ነገር ከመቆም ይልቅ፤ ለቡድን ፍላጎት እጅ መስጠትም ይሉኝታን ይገልፃል። የሃሳብ ልዩነቶችን እና ግጭቶችን ተጋፍጦ፤ በሃሳብ ከመርታት ይልቅ መሸሽ፣ ሃሳቦች ሳይብላሉ ማቋረጥ፣ መፍራት እንዲሁም “ብዙ መከራከር አልወድም፤ መጋፈጥ አልፈልግም” የሚሉት ይሉንታን ያመላክታሉ።

የፈለገውን ያህል ዋጋ ቢያስከፍለን፤ ሌሎችን ላለማስከፋትና ላለማበሳጨት መጣር ደግሞ የይሉኝታን አሉታዊ ጎን ይገልፃል። “አይሆንም!” የማለት ድፍረት ማጣት፤ ለሁሉም ነገር “እሽ!” ማለትን ማስቀደም ሌላው የይሉኝታ መገለጫ ነው። በዚህም የተነሳ የማይመስለንን “አይመስለኝም”፤ የሚመስለንን “ይመስለኛል” ብሎ የመናገር ድፍረት አይኖረንም። ሁልጊዜ ነገሮችን “እሽ!” በማለት የምናልፍ ከሆነ እጅጉን ለይሉኝታ ተጋልጠናል ማለት ነው።

ሰዎች በውይይት መሃል የተለየ ሃሳብ ሲያነሱ፤ ከሃሳቡ ይልቅ ሰዎች ላይ ማተኮር ስንጀምር የይሉኝታ ባህሪ ይገለፃል። ሰዎች ስለኛ ምን ሊያስቡ፤ ምን ሊናገሩ ይችላሉ በማለት መጨነቅም የአጉል ይሉኝታ ውጤት ሆኖ ይከሰታል። ሳናምንበት ስሌሎች መጥፎ ነገር ሲወራ አብሮ ማውራት እና ማማትም የይሉኝታ መጥፎ መገለጫ ነው።

የይሉኝታ አዎንታዊ ገፅታ

ይሉኝታ በአግባቡ ተግባራዊ ከሆነ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው። ይሉኝታ በማህበረሰብ ውስጥም ሆነ በሥራ ቦታ አስፈላጊ እሴት ሆኖ ያገለግላል። አግባብነት ያለው ይሉኝታ በሰዎች መካከል መልካም መስተጋብር እንዲኖር ያስችላል፤ ሰላምን እና ፍቅርን ያጎናፅፋል።

በሥራ ቦታ ይሉኝታ በሚያሰፍነው መልካም ውጤት መተማመን ይነግሣል። አጉል ተወዳጅነት ከስሞ የሥራ ውጤት በእውነት ሚዛን ይሰፈራል።

ይሉኝታ የሚያስከትለው ጉዳት

የሰዎችን ደስታ እና ሃዘን መካፈል፤ ለሰዎች በችግራቸው ጊዜ ያቅምን ማድረግ አብዛኞቻችንን ያስደስተናል፤ እርካታም ይሰጠናል። ይሁን እንጂ አንዳንዴ ሰዎች በይሉኝታ ሲታሰሩና ከፍላጎታቸው እና ከአቅማቸው በላይ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ሃሳባቸውን ለሌሎች ሰዎች ደስታ ሲያውሉ ይታያል። ይህ አይነቱ ከመጠን ያለፈ ይሉኝታ ደግሞ ከመልካምነቱ ይልቅ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው።

አግባብነት በሌለው ይሉኝታ ምክንያት ከሰዎች የምንጠብቀው ማበረታቻና ተቀባይነት ሁሌም ላይገኝ ይችላል። ራስ ወዳድ ለሆኑ እና በሌሎች  መጠቀም ለሚፈልጉ ሰዎች ተጋላጭ እንሆናለን። ሁሉም ቦታ ለመገኘት ስንጥር በስራችን ውጤታማ አንሆንም። በዚህ የተነሳ  ህይወታችን በደስታ የተሞላ አይሆንም።

ይሉኝታ በኛ ሃገር

የማንኛውም ማህበረሰብ ባህል በረዥም ዘመን ውስጥ በሰዎች እውቀት፣ ልምድ እና እምነት የተገነባ ነው። በኢትዮጵያም ይሉኝታ ከበርካታ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ ሆኖ ይገለጻል። በተለያዩ አግባቦች  በየእለታዊ ህይወታችን ይንፀባረቃል።

ብዙዎች የይሉኝታን ከዝምታ ጋር ያያይዙታል። “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” በሚል አጉል ይሉኝታ ወለድ ብሂል ተተብትበው። ይህ አይነቱ ይሉታን ጎጂ ገፅታን አመላካች ነው። ይሉኝታ ዝም ማለት አይደለም። መቸ፣ እንዴት እና በማን ፊት ምን አይነት እውነትን በሃቅ መናገር እንደሚገባ መለየት ነው።

ይሉኝታ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ በጣም ጠንካራ ሥፍራ ያለው እሴት ነው። በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታ፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በዕለት ተዕለት ሁለቱን መገለጫዎች አጣምሮ ሲከወን ይታያል። በመልካሙ ገፅታ ታናሽ ታላቁን ያከብርበታል። በበጎ ምላሽ “ከእኔ አንተ ብትቀድም መልካም ነው” እንባባልበታለን። በሌላ ጎን ደግሞ ርካሽ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ይሉኝታ በተለያዬ ጎጅ ክንዋኔም ይፈጸማል።

ይሉኝታን በልኩ እንዴት?

ይሉኝታ ሁለት ገፅታዎች የሚንጸባረቁበት ነው። በገንቢ እና ጎጂ መገለጫዎቹ፤ ስለሆነም ለሰዎች መልካም በመሆን እና ባልተገባ የራስ ወዳድነት ፀባይ መካከል ያለውን ውጤት በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ነው።

ሰዎች ስለእኔ ምን ሊያስቡ ይችላሉ? ይህን ብናገር ይህ ይገጠመኛል፤ ከሁሉም ነገር አለመናገር ይሻላል፤ ከበላይ አለቃ ጋር መከራከር ጉዳቱ የከፋ ነው፤ … በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች እውነትን ያለየ ይሉኝታን መጠየፍ እና ለእውነት መቆም ይሉኝታን በልኩ ያጎናፅፋል። ይሉኝታ ራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ አግባብነቱን ዘሎ መተግበሩ ላይ ነው። በመሆኑም ይሉኝታ በዘመናዊ ማህበረሰብ፤ ከግልፅነት እና ከመብት ጋር መመጣጠን አለበት። ክብርን በመጠበቅ እውነትን መናገር የሚችል ትውልድ መገንባት የዘመናችን ጥያቄ ሊሆን ይገባል! ቸር ይግጠመን!

 

ምንጭ፦ Goffman, E. (1959). The Presentation of Self in Everyday Life.

–         Interaction Ritual: Essays on Face-to-Face Behavior (1967)

–         Politeness: Some Universal in Language Usage (1987)

–         Patterns of Culture (1934)

 

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here