የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በተግባር እየተገለጠ ነው

0
291

መግቢያ

የአፈር ጥበቃ በኢትዮጵያ ገበሬዎች ዘንድ ለዘመናት የቆየ ባሕላዊ ዕውቀት ነበር። በሰሜን ኢትዮጵያ (ትግራይ እና ወሎ) እንዲሁም በደቡብ (ኮንሶ) አካባቢዎች ገበሬዎች የድንጋይ እርከን በመሥራት የአፈር ለምነትን ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል:: ነገር ግን ይህ ሥራ በመንግሥት የታገዘና የተቀናጀ አልነበረም።

አስከፊው የወሎ ድርቅ እና ረሃብ የመሬት መራቆት ለሀገሪቱ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ለመንግሥት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ደወል የሆነበት የታሪክ ምእራፍ ለአፈርና ውኃ ጥበቃ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ እንዳደረገ ከዚያ በኋላ በነበሩ መንግሥታት የተሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው::  ለአብነት ድርቁን ተከትሎ የደርግ መንግሥት ምግብ ለሥራ የሚባል ፕሮግራም ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመሆን ጀመረ። አርሶ አደሩ በምግብ ዕርዳታ ምትክ እርከኖችን እንዲሠራ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን እንዲተክል የተደረገበት መንገድ ለትኩረቱ ዋነኛ ማሳያ ነው::

በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በጊዜ ሂደት አሠራሩ ወደ ተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እንዲቀየር ተደረገ:: አንድን ተራራ ብቻ ከመጠበቅ ወጥቶ አጠቃላይ የውኃ መፍሰሻውን ተከትሎ ከአናት እስከ ታች የመጠበቅ ስልት ደግሞ የአፈር ክለትን በዘላቂነት ለመከላከል ሁነኛ ስልት ሆኖ በየዓመቱ በጥርና በየካቲት ወራት  እየተሠራ ይገኛል::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ እና የአካባቢ ጥናት ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በእወቅቱ በኢትዮጵያ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ዙሪያ ሰፊ ጥናቶችን አድርገዋል:: ጥናቶች እርከን መሥራት የአፈር መሸርሸርን ከ50 እስከ 90 በመቶ ይቀንሳል ብለው ያምናሉ:: እርከኖች በአግባቡ ካልተጠገኑ ወይም በቂ የውኃ ማፍሰሻ ከሌላቸው ለተጨማሪ መሸርሸር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉም ጥናታቸው ይጠቁማል::

የአማራ ክልል አሁናዊ እንቅስቃሴ

የአማራ ክልል በየዓመቱ ከወርሃ ጥር መግቢያ ጀምሮ የሚያከናውነው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ዘንድሮም ከታህሳስ 20 ቀን ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል:: ዘጠኝ ሺህ 206 ተፋሰሶችን በመለየት በ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ እየተሠራ ነው:: አራት ነጥብ  አምስት ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በሥራው ይሳተፋሉ:: ሥራው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል::

ፋይዳዎች ሲገለጡ

ነዋሪነታቸውን በምእራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ ያደረጉት አርሶ አደር አበበ ካሴ በየዓመቱ ጥር ወር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ያለማንም ቀስቃሽ እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል:: ለብዙ ዓመታት በከፍተኛ ጎርፍ አፈሩ ተወስዶ ገድል የነበረው እና ሰው የማያሳልፈው መንገድ ዛሬ ላይ ወደ ደልዳላነት መመለሱ ደግሞ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፍ ማድረጉን ተናግረዋል:: በየዓመቱ የሚሰሩ እርከኖችን  ዘላቂ ለማድረግ የሚተከሉ ሳሮች እና ችግኞች ለከብት መኖነት እያገለገሉ በመሆኑ ውጤቱ ከፍ ያለ ነው ብለዋል:: ከከፍታ ቦታ የሚወርደው ጎርፍ ወደ ሰፈር በመግባት በሰው፣ በእንስሳት እና በቤት ላይ ያደርስ የነበረው ጉዳት በእጅጉ መቀነሱንም ተጨማሪ ፋይዳ በማድረግ አንስተዋል::

የምዕራብ ጎጃም ዞንም ለአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል:: የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን ከመጨመር ባለፈ ለአርሶ አደሮች ሰፊ የሥራ ዕድል እና ገቢ እያስገኘ መሆኑ ተገልጿል። እንደ ዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ የሺዋስ ባንቲሁን በ35 ሺህ 247 ሄክታር መሬት ላይ 524 ተፋሰሶችን ለማልማት ታቅዷል:: ቡድን መሪው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እስካሁን 485 ተፋሰሶች ወደ ሥራ ገብተዋል፤  ለተከላ የሚሆኑ 58 ሚሊዮን ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው::

የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራው የተፈጥሮ ሚዛንን ከመመለስ ባሻገር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል:: ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ልማት በተከናወነባቸው 499 ተፋሰሶች ላይ 22 ሺህ 254 አርሶ አደሮች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል:: በእንስሳት ማድለብ፣ በፍራፍሬ ልማት፣ በንብ እርባታ እና በደን ልማት በመሰማራት ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉም ውጤቱን አስታውቀዋል::

የምሥራቅ ጎጃም ዞን በዘንድሮው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ አንድ ሺህ  52 ነባር እና አዲስ ተፋሰሶችን ለማልማት እየተሠራ መሆኑን የግብርና መምሪያ ኃላፊው አበበ መኮንን አስታውቀዋል:: እየተሠራ ያለው የጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን በመመለስ፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የውኃ አካላትን በማጎልበት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል::

አንደ አቶ  አበበ ገለፃ እስካሁን በለሙ የተፋሰስ ሥራዎች የአፈር ለምነትን ከሰባት እስከ 22 በመቶ ማሻሻል ተችሏል። በአፈር አሲዳማነት የተጎዱ (ስናን፣ ማቻከል እና ሌሎች ደጋማ ወረዳዎች) ላይ የተከናወኑ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ሥራዎች ወደ ምርት እንዲመለሱ ማድረጉንም ለፋይዳው ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: ከስምንት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በደን መሸፈኑን ያስታወቁት ኃላፊው፣ ይህም የደን ሽፋኑን ከ17 ነጥብ አንድ በመቶ በላይ ማድረሱን ተናግረዋል::

528 የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መቋቋማቸውንም አረጋግጠዋል:: እነዚህ ማኅበራት ከተፋሰሶች የሚመነጩትን ሃብት ወደ ገቢ በመቀየር አርሶ አደሮችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ አድርገዋል። የተፋሰስ ማኅበራት ከ111 ሚሊዮን ብር በላይም እያንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራዎች የታየው ውጤት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከነበረው ስጋት መውጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል:: ቢሮው የበጋ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን መሠረት አድርጎ ጥር 17 ቀን 2018 ዓ.ም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳጋራው ጽሑፍ ከሆነ በእስካሁን የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች የተራቆቱ እና የተጎራረዱ የወል መሬቶች አገግመው ወደ ምርት ተሸጋግረዋል፤ የአፈር ክለት ቀንሷል፤ ከዓመት ዓመት የሰብል ምርት እና ምርታማነት እድገት አሳይቷል::

የተፋሰስ ልማት ሥራዎችም ምንጮች እንዲጎለብቱ በማድረግ ለመስኖ ልማት ትልቅ አቅም እንደሆኑ የቢሮው መረጃ ያሳያል:: በማሳ ላይ እርከን እና መሰል የተፋሰስ ሥራዎችም ምርታማነትን ማሳደግ፣ የጓሮ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት የገበያ ሰብሎችን በማምረት ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ አቅም መሆናቸው ተገልጿል::

የወል መሬቶችን ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ ወጣቶችን በማደራጀት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በማድለብ፣ በንብ ማነብ እና መሰል ሥራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል። ይህ ደግሞ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ለተፋሰስ ልማት ሥራ ተጨማሪ አቅም ይሆናል፤ ምርታማነትም በማሳደግ የግብርና ውጤት የሆኑ ምርቶችን ዋጋ በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉም አስችሏል። በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለተፋሰስ ልማት ሥራዎች በተሰጠው ትኩረት የአባይ እና የተከዜ ተፋሰሶች በሚገኙባቸው የክልሉ አካባቢዎች በልዩ ትኩረት የተፋሰስ ልማት ስራ በመሰራቱ የህዳሴ ግድቡን ከደለል መታደግ መቻሉንም ቢሮው አስታውቋል።

እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል?

“የመሬት ባለቤትነት መብት” በአፈር እና ውኃ ጥበቃ ላይ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው በዓለም ባንክ የታተመ ጥናት ይፋ አድርጓል:: እንደ ጥናቱ አርሶ አደሩ መሬቱ የራሱ እንደሆነ እና ለወደፊትም እንደማይቀማ ሙሉ ዋስትና ከሌለው በመሬቱ ላይ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ለማድረግ አይነሳሳም። የአፈር ጥበቃ ሥራዎች (እንደ እርከን መሥራትና ዛፍ መትከል) ውጤታቸው የሚታየው ከዓመታት በኋላ በመሆኑ አርሶ አደሩ “ነገ የምቀማው መሬት ላይ ለምን እደክማለሁ?” የሚል ስጋት ስለሚያድርበት ለጥበቃ ሥራው ያለው ተነሳሽነት ይቀንሳል::

የመሬት ባለቤትነትን በማረጋገጥ ውጤታማ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ካከናወኑ ሀገራት መካከል ቻይናን የጠቀሰው ደግሞ የጥናት ውጤቶች የመረጃ አውታር የሆነው ሪሰርች ጌት ነው:: ቻይና በዓለም ላይ በታሪክ እጅግ ግዙፍ የተባለውን የተፋሰስ ልማት በሎየስ ፕላቶ አካባቢ ስታከናውን የተጠቀመችው ስልት የመሬት ባለቤትነት መብትን ለአርሶ አደሩ በመስጠት ነው። አርሶ አደሩ በሠራው እርከን ላይ ለ30 ዓመታት የመጠቀም መብት ስለተሰጠው እርከኑ እንዳይፈርስ በራሱ ተነሳሽነት ይጠብቀዋል። ይህም ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ከድህነት ከማውጣትም በላይ በ ‘የሎው ሪቨር’ ላይ ይከማች የነበረውን ደለል በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

የአፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ ተፅእኖ ፈንድ (CJIFA) የአፈር እና ውኃ ጥበቃን ከአርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ጥቅም ጋር በማያያዝ ኬንያ ውጤታማ ተሞክሮ እንዳላት ጽፏል:: ኬንያ በ1930ዎቹ እጅግ የተራቆተውን እና በድርቅ የተመታውን ማቻኮስ የተባለውን አካባቢ ለማልማት “ከጥበቃ ወደ ገቢ” የሚል መርህን ተከትላለች:: አርሶ አደሮች በበጋ የሠሯቸውን እርከኖች ለቡና እና ለፍራፍሬ ልማት እንዲጠቀሙ ተደረገ:: አርሶ አደሩ አፈሩን ከጠበቀ የሚሸጥ ምርት እንደሚያገኝ ስላወቀ ለሥራው ልዩ ትኩረት ሰጠ፤ ውጤትም ተገኘበት::

ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በውቀቱ “በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ደጋማ አካባቢዎች የተከናወኑ መደበኛ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ስራዎች፦ የአርሶ አደሮች ተቀባይነት እና አጠቃቀም” በሚል ርእስ የሠሩት ጥናት ላይ በየጊዜው ለሚከናወኑ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ዘለቄታዊነት ምክረ ሐሳቦችን አስቀምጠዋል:: ከላይ ወደ ታች የሚመጣ ትዕዛዝን ማቆም፣ ቴክኖሎጂዎች እንደየአካባቢው ስነ-ምህዳር እና አርሶ አደሩ ኑሮ ተግባራዊ ማድረግ፣ አርሶ አደሩ ችግሩን እንዲረዳ እና መፍትሄውንም አብሮ እንዲያመነጭ ማድረግ ለውጤት እንደሚያበቃም ከሳይንስ ዳይሬክት ላይ ያገኘነው ጥናታቸው ያሳያል::

በአጠቃላይ በተፈጥሮ ሀብት (አፈርና ውኃ) ጥበቃ ሥራ ላይ የተሠሩ ጥናቶች  “መሬቱን የምንጠብቀው አርሶ አደሩን ስንጠብቀው ነው” የሚል ጽኑ አቋም አላቸው:: አርሶ አደሩ በመሬቱ ላይ ሙሉ ዋስትና፣ የባለቤትነት ስሜትና የገበያ ዕድል ሲኖረው፣ ያለ መንግሥት ግፊት አፈር እና ውኃውን ለመጠበቅ ቀዳሚ ተዋናይ እንደሚሆን ጠቋሚ ነው::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here