የበለጸገች እና ምንም የተኩስ ድምፅ የማይሰማባት አፍሪካን በ2063 ማየት ራዕዩ የሆነው የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረው እ.አ.አ በ1963 ነበር:: ታዲያ ያን ጊዜ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚል ስያሜ ነበረው:: ዋና አላማው ከቅኝ ግዛት መላቀቅና መረጋጋትን ማስፈን ነበር:: ነፃነትን መጠበቅ፣ አንድነትን ማጠናከር፣ የአፍሪካዊያን ድምፅ በዓለም ላይ እንዲሰማ ማድረግ፣ በአህጉሯ ጸጥታን ማስከበር፣ ልማትን ማረጋገጥ፤ በአፍሪካ ጉዳዮች የአፍሪካ ሀገራትን በጋራ ማሳተፍ የሚሉት ተጨማሪ አላማዎቹ ናቸው:: የኢትዮጵያው መሪ አጼ ኃይለሥላሴ፣ የጋናው ክዋሜን ንኩርማ እና የታንዛኒያው ጁሊየስ ኒሬሬ ድርጅቱን በመመስረት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው:: ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት:: የኅብረቱ (AU )ዋና ጽ/ቤት በአዲስ አበባ መገኘቱ፣ ሀገሪቱን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል:: ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለአፍሪካ አንድነት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች::
የአፍሪካ ኅብረት – የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በነበረበት ጊዜ አህጉሪቱን ከቅኝ ግዛት ማላቀቅ የሚለውን አላማ አሳክቷል ማለት ይቻላል:: ምክንያቱም በወቅቱ ሲመሰረት በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት 22 ሀገራት ነጻ አልወጡም ነበር፤ በሂደት ግን ነጻነታቸውን ሊቀዳጁ ችለዋል::
ይሁንና ድርጅቱ( OAU) በውስጣዊ ግጭቶች፣ በድህነት እና በአምባገነንነት ላይ በቂ መፍትሄ ማቅረብ አልቻለም:: በየሀገራቱ የሚፈጠሩ ጦር ያማዘዙ ግጭቶችን ከመፍታት ይልቅ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ነው በማለት ብዙ ጊዜ ዝም ይል ነበር:: ይህም አዲስ የተጠናከረ ድርጅት እንዲፈጠር ምክንያት አድርጎታል::
በሕብረቱ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው እ.አ.አ በ1999 በሊቢያ የተካሄደው የሲርቴ ስብሰባ የአፍሪካ ኅብረት (AU) ጥንስስ መነሻ ሆነ:: በ2002 በደቡብ አፍሪካም የአፍካ አንድነት ድርጅት (OAU) በአፍሪካ ኅብረት ተተካ:: ኅብረቱ ሕገ መንግሥት እና የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ፕሮቶኮልን እንዲሁም የኅብረቱን ዓላማዎችን አስቀምጧል:: የአባል ሀገራቱን ሉዓላዊነት፣ ግዛታዊ አንድነት እና ነፃነት መጠበቅ፣ የአህጉሪቱን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ውህደት ማፋጠን፣ ለአህጉሪቱ እና ሕዝቦቿ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ የአፍሪካን የጋራ አቋሞች ማሳደግ እና መጠበቅ፣ ዓለም አቀፍ ትብብርን ማበረታታት፣ በአህጉሪቱ ሰላምን፣ ደኅንነትን እና መረጋጋትን ማሳደግ፣ የዴሞክራሲ መርሆዎችን እና ተቋማትን ማሳደግ የሚሉት ይጠቀሳሉ::
የተመዘገቡ ውጤቶች
በመጀመሪያ የአፍሪካ ኅብረት አንዱ ትልቅ ስኬት ተብሎ የሚጠቀስለት አህጉሪቱ በዓለም መድረኮች ላይ በአንድ ድምፅ እንድትናገር እድል መፍጠሩ ነው:: ይህም በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የአፍሪካን ተሳትፎ እንዲኖር አድርጓል:: ሌላው በአህጉሪቱ አፍሪካዊ ተቋም እንዲኖር ማስቻሉ ነው:: ማለትም አፍሪካዊያን መሪዎች በመሰባሰብ ፖሊሲዎቻቸውን እና ቁልፍ በሆኑ ዓለም አቀፍ እና በተለያዩ በአህጉሪቱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎቻቸውን ለማሳለፍ እና ሀሳባቸውን ለማንፀባረቅ የሚያስችላቸው መድረክ መሆን መቻሉ እንደስኬት ይቆጠርለታል::
በዓለምአቀፍ መድረኮችም እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባሉ ስብሰባዎች ላይ ለአፍሪካ አሳሳቢ የሆኑ ጉዳዮችን ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል:: ይህም አፍሪካውያን ድምጻቸው እንዲሰማ ብሎም የአፍሪካ መንግሥታት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስችሏል::
በሰላምና ደኅንነት ዘርፍም፣ የአፍሪካ ኅብረት ለሰላም ማስከበር ከአባል ሀገራት ወታደሮችን የሚልክ ሲሆን በሶማሊያ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ በኮሞሮስ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማሊ እና ሌሎች ሀገሮች የሰላም አስከባሪዎችን በመላክ ግጭቶችን ለመቆጣጠር ሞክሯል:: ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ታንዛኒያ እና ሌሎችም በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው ልዩ ልዩ ኦፕሬሽኖች እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰፊ ተልዕኮዎች ወታደር፣ ፖሊስ እና ሎጂስቲክስ ሰጥተዋል:: እነዚህ ጥረቶች ምንም እንኳን ሙሉ ስኬት ባይሆኑም የበርካቶችን ሕይወት ለማዳን አስተዋጽኦ አድርገዋል::
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕውሓት መካከል በቅርቡ የተደረገውን ግጭት ማስቆም ችሏል:: በዚህም ኅብረቱ በአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል:: መፈንቅለ መንግሥትን በመከላከልና በማስቀረት በሀገራት መካከልና በውስጣቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በማስወገድ ረገድ ተጠቃሽ የሚባሉ የአመለካከት ለውጦችና ተግባራትን አከናውኗል::
ለምሳሌ በየቀጣናው ባሉ በአባል ሀገራት መካከል ቀጣናዊ የምጣኔ ሀብት ትብብርን አበረታቷል፣ ለአብነትም የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) በአፍሪካ ትልቁ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ድርጅት ሲሆን 19 አባል ሀገራት እና ወደ 390 ሚሊዮን የሚጠጉ ህሕዝቦች አሉት:: ኢኮዋስ 15ቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ( ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኬፕ ቨርዴ፣ ኮትዲባር፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሴራሊዮን እና ቶጎ )፣ሳዲሲ (የደቡብ አፍሪካ ልማት ማኅበረሰብ ሲሆን በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን፣ ሰላምን እና መረጋጋትን ለመፍጠር ያለመ 16 አባል ሀገራት ያለው ድርጅት ነው::) ያሉ የክልል የኢኮኖሚ ቡድኖችን እንዲመሰረቱ አስችሏል:: እ.አ.አ በ2018 በ54 የአፍሪካ ሀገራት የተፈረመው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናም (AfCFTA) ስምምነት አፍሪካን የዓለም ትልቁ የንግድ ገበያ ለማድረግ የሚያግዝ ታላቅ እርምጃ ነው:: ይህ ስምምነት በሀገራት መካከል ንግድን በማሳደግ ለሥራ ፍጠራና ለኢኮኖሚ እድገት ትልቅ እድል ይፈጥራል::
የአፍሪካ ኅብረት በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል:: በየሀገሮች እና የመንግሥታት መሪዎች ዓመታዊ ስብሰባ በማድረግ በአባል ሀገራት መካከል ወዳጅነት በመፍጠር ፈር ቀዳጅ ሆኗል:: በአፍሪካ የሰብአዊ መብት ጥሰትን አውግዟል:: የድንበር አለመግባባቶችን ፈትቷል፤ ለምሳሌ በሞሮኮ እና በአልጄሪያ መካከል የነበረውን የድንበር ውዝግብ በመፍታት ተጠቃሽ ነው::
ተግዳሮቶቹ
የአፍሪካ ኅብረት የመጀመሪያው ተግዳሮቱ የገንዘብ ችግር ነው:: ብዙ ፕሮጀክቶቹ በውጭ ድጋፍ መተግበራቸው ነፃነቱን ይጋፋል:: ሁለተኛ ውሳኔዎቹን ማስፈጸም ላይ ደካማ መሆኑ ነው:: ብዙ ጊዜ የተወሰኑ ውሳኔዎች በአባል ሀገሮች አይተገበሩም:: ይህም የኅብረቱን ተፅዕኖ ያን ያህል እንዳልሆነ ማሳያ ነው::
ቀጣይነት ያላቸውን የእርስ በርስ ግጭቶችን ባለማስቆሙ፣ በሀገራት መካከል የሚፈጠረውን ውዝግብ ባለመፍታቱ እና የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን ባለመቆጣጠሩ እና በውጭ ግፊት ተግዳሮት ላይ መገኘቱ እንደድክመት ይወሰዳል:: አንዳንድ ጊዜ የሀገራት ጥቅም ከአፍሪካ ጥቅም በላይ ሲሆን ይታያል:: ከዚህ በላይ የሕዝብ ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ እንዱ ችግር ነው:: ብዙ አፍሪካውያን ስለ አፍሪካ ኅብረት በቂ መረጃ የላቸውም:: ይህም የተቋሙን ድክመት ማሳያ ነው::
በአጠቃላይ የአፍሪካ ኅብረት ከፊል ውጤታማ መሆኑ ግልፅ ነው:: በአንድነት፣ በሰላም እና በኢኮኖሚ ዘርፍ አስፈላጊ መንገዶችን ከፍቷል:: ነገር ግን በገንዘብ፣ በአስፈጻሚነት እና በግልጽነት ዘርፍ አሁንም ብዙ መሻሻል ያስፈልገዋል::
የአፍሪካ ኅብረት የወደፊት ስኬት፣ በአባል ሀገራት ቁርጠኝነት፣ በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ እና በግልጽ አስተዳደር ላይ ይመሰረታል:: ይሁንና ኅብረቱ ዛሬም ቢሆን በብዙ መልኩ ከምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ መላቀቅ አለመቻሉ የድክመቱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል:: አፍሪካ በሌሎች አህጉራት የማይገኙ ውድ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችን አሁንም በርካሽ እየላከች የፋብሪካ ውጤቶችን ደግሞ በውድ ዋጋ የምታስገባ ሀገር ናት:: ታዲያ ይህ ሁኔታ መቀየር ካልተቻለ የአውሮፓ እና የቻይና ምርት ማራገፊያነቷ አሁንም ሊቀጥል ይችላል:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የአፍሪካ መንግሥታት በመተባበር መስራት ይጠበቅባቸዋል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


