በኬኒያ ዋና ከተማ በየጐዳናዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወፎችን አሰባስቦ በሚችለው አቅም ተንከባክቦ ሲያገግሙ ወደ ዱር የሚለቀው ወጣት “የናይሮቢ ወፍ ጠባቂ” (ናይሮቢ በርድማን) የሚል ስያሜ ማግኘቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
የ27 ዓመቱ ሮጀርስ ኦሉ ማጉታ ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ናኩሩ ኃይቅ ብሔራዊ ፓርክ በመሄድ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን አእዋፍ መመልከት ይወድ እንደነበር ነው የተናገረው -የአእዋፍ ፍቅር ስለነበረበት፡፡ ለአእዋፍ የተለየ ስሜት ያደረበትም ከአምስት ዓመታት በፊት መሆኑን ነው ያሰመረበት፡፡
ከአምስት ዓመታት በፊት በመኖሪያ ቀጣናው እየተዘዋወረ ሳለ ከመኖሪያ ጐጆው ወድቆ የቆሰለ የወፍ ጫጩት ይምለከታል፡፡ ጫጩቱን ቀርቦ ሲያስተውለው እየተቁለጨለጨ እርዳታውን የሚጠይቀው መሰለው፤ ጫጩቱን ይዞ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብሎ ከየሰዉ የሰበሰበውን ፍርፋሪ ያበላውም ጀመር፡፡ ሮጀርስ “ጆንሰን” በሚል ስም የሰጠውን ጫጩት ወፍ ትከሻው ላይ ይዞ ሲዞር የተመለከቱ ሌሎች የተጐዱ ወፎችን እያመጡ ይሰጡት ጀመር – በቃ የእሱ ተግባር ተቀብሎ ከሚሰበስበው ፍርፋሪ እያካፈለ መንከባከቡን ገፋበት፡፡
ሮጀርስ የሚንከባከባቸው ወፎች ከጉዳታቸው ሲያገግሙም ወይም መብረር ሲችሉ ወደ ዱር ይለቃቸዋል፤ እዚህ ላይ እንዳይበዙበት ሌሎች አዲስ ተጐጂዎችን ለመንከባከብ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዚህ መልኩም ነው “የናይሮቢው የወፎች ተንከባካቢ” የሚል “ስም” አግኝቶ ከሀገሩ አልፎ በሌሎችም ለመታወቅ የደረሰው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


