ፈጣኑ አሳንሰር

0
4

በቻይና ጉዋንግዙ ከተማ በተገነባው በፋይናንስ ማእከልነት በሚያገለግለው  ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ላይ የተገጠሙ አሳንሰሮች 95 ፎቆችን በ43 ሰከንዶች በመፈትለክ በፍጥነታቸው በዓለማችን ቀዳሚ መሆናቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

ስሪታቸው ወይም መለያቸው “ሂታቺ” የሆኑ 95 አሳንሰሮች – ከነዚሁ ውስጥ 28ቱ ባለሁለት ፎቅ፣ 13 ባለ ከፍተኛ ፍጥነት፣ 52ቱ ባለ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ፍጥነት ሁለቱ ደግሞ በዓለማችን እጅግ ፈጣን የሆኑ አሳንሰሮች ተካተውበታል፡፡

በዓለማችን በፍጥነታቸው ቀዳሚ የተባሉት ሁለቱ በደቂቃ 1200 ሜትር ወይም በሰዓት 44 ነጥብ ሰባት ማይል መፈትለክ የሚችሉ ናቸው፡፡ በዚህም  “እጅግ ፈጣን አሳንሰር” የሚል ማእረግ የተሰጣቸው መሆኑ ነው ለንባብ የበቃው፡፡

የአሳንሰሮቹ አምሯች እና መለያ “ሂታቺ” ደህንነታቸው የተጠበቀ ይሆን ዘንድ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ንድፎችን ገጣጥሞ ለአገልግሎት ማብቃቱም ነው የተገለፀው፡፡ ከነዚህ መካከል ቅርፃቸው ከአራት መዓዘን ይልቅ በሁለቱም ገፅ ሞላላ ወይም ሾል ያለ ቅርፅ ኖሮት ዓየሩን ሰንጥቆ የመሄድ ዓቅም እንዲኖረው ተጠበውበታል- የሰሩት መሃንዲሶች፡፡

ለአሳንሰሩ ፈጣንነት ከመነሻው ለመወርወር ስበት (ማግኔት) ከአንቀሳቃሽ ሞተሩ ጋር ተቀናጅቶ መሰራቱ  የልዩ ስሪቱ ማሳያ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ከሁሉም በላይ አሳንሰሩን የሰሩት ባለሙያዎች በከፍተኛ ፍጥነት ሲፈተለክ በሰበቃ (ፍሪክሽን) የሚፈጠረውን ሙቀት ማመጣጠኛ ማስተንፈሻዎች ነድፈውለታል፡፡

በመጨረሻም አሳንሰሩ በፍጥነት ሲፈተለክ በህንፃዎች መካከል ሲወረወር የተሳፋሪዎች ጆሮ መዘጋት እንዳይገጥመው በዓየር ግፊት አውቶማቲክ ማስተካከያ ስርዓት  የተገጠመለት መሆኑም ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here