የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

0
4

የሰሜን  ተራሮች  ብሔራዊ  ፓርክ   በአማራ ክልል ሰሜን  ጐንደር  ዞን  ነው  የሚገኘው፡፡

በ1969 እ.አ.አ ነው ህጋዊነትን አግኝቶ በፓርክነት የተመሰረተው፡፡

ከአዲስ አበባ በአውሮኘላን ጐንደር ከዚያም ከሁለት ሰዓት የተሽከርካሪ ጉዞ በኋላ ደባርቅ ደርሶ ፓርኩን ማግኘት ይቻላል::የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አስደናቂ የመሬት አቀማመጥ አለው- በዚህም ባለፉት ዘመናት የአፈር መሸርሸር የተንሰራፋባቸው የተራራ ጫፎች፣ ጥልቅ ሸሎቆዎች እና ተዳፋታማ ገደሎችን ይዟል::ፓርኩ ዓለም  አቀፍ ትኩረትን በመሳቡም በ1978 እ.አ.አ በዓለም አቀፍ ተፈጥሯዊ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡ ለዓለም አቀፍ ቅርስነቱ የራስ ዳሽን ተራራ 4533 ሜትር ከፍታ ያለው በሀገሪቱ ቀዳሚው መገኛነቱ፣ ብርቅዬዎቹ – ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጆሮ እና ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉን አቅፎ በመያዙ መሆኑንም ነው የዓለም አቀፉ የአካባቢ፣ ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ድረ ገጽ ያሰፈረው::በፓርኩ 250 የእፅዋት ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ከ3000 እስከ 3700 ሜትር ከፍታ የሳር ምድር እና እስከ 10 ሜትር ቁመት የተለካው “ጃይንት ሎቤላ” ጅብራ የብዝሃ – ህይወቱ አካል ነው፡፡ ከ3000 ሜትር ባነሰው የመሬት ገፅታ የግራር እና የጥድ ዛፍ በጣም ዝቅ ሲል  ደግሞ እፅዋት የማይታይበትን ገላጣ መሬት አካቶ ይዟል፡፡

በፓርኩ 130 የዓእዋፍ ዝርያዎች ብርቅዬዎቹ አጥንት ሰባሪው “ላማርገዬር” እና ግልገል አንሳ (ቮልቹር) የጐብኚዎችን ቀልብ ሳቢ ፈርጦች ናቸው ፡፡

ለፓርኩ ዘላቂነት በቀጣናው ናሪዎች   መስፈር፣ ለግጦሽ ከብት ማስገባት፣ ህገወጥ አደን ስጋት መሆናቸው ተሰምሮበታል:: ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ደብሊው ኤች ሲ ዩኔስኮ፣ ብሪሊያንት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያን ቱር አሶሴሽን ድረገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here