የንብረት፣ የመሬት ይዞታ እና የቤት ባለቤትነት መብቶች

0
50

ንብረት ለሰው ልጆች የመኖር ህልውና ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው:: ምክንያቱም ንብረት በቂ የሆነ የኑሮ ደረጃ (adequate standard of living) የሚያስፈልጉ መብቶችን ለምሳሌ የምግብ፣ መጠለያ እና የመሳሰሉትን ለማግኘት እንደ መሠረት ሆኖ ያገለግላል:: የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር በማሕበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው የንብረት ባለቤትነት መብት ብዙውን ጊዜ የተፈጥሮ ሰዎች ንብረታቸውን በሚመለከት እንደ ሰብዓዊ መብት የሚጎናፀፉት ነው።

መረጃው እንደሚያስገነዝበው ንብረት የራስ የሆነ ነገር ማለት ነው። ስለ ንብረት ሕግ ከሚደነግገው የፍትሃብሄር ሕግ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ነገር ንብረት ለመባል፦ በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል (appropriable)፣ ይህ በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል ነገርም ጠቃሚነት ያለው (useful) መሆን አለበት። ሁሉም ጠቃሚ ነገሮች የንብረት ትርጉም ይሰጣቸዋል ማለት አለመሆኑንም ልብ ይሏል። ለምሳሌ ፀሐይ እጅግ ጠቃሚ ብትሆንም፣ በንብረትነት አትካተትም:: በተመሳሳይ አንድ ነገር ንብረት ነው ለማለት ዋጋ ያለው ወይም ዋጋ የሚያወጣ መሆን አለበት።

በአጠቃላይ ንብረት በባለቤትነት ሊያዝ የሚችል፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና ዋጋ ያለው ነገር የሚለው ትርጉም የዘርፉ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነው።

የንብረት ሕግ የሚባለው ደግሞ የንብረት መብት እንዴት እንደሚገኝ፣ እንዴት እንደሚተላለፍ፣ እንዴት እንደሚቋረጥ፣ የባለሃብትና የባለይዞታ መብቶች ምን እንደሆኑ የሚደነግግ ገዥ ሕግ ነው። ሕጉ ታዲያ ግለሰቦች የግል ንብረታቸውን የመሰብሰብ፣ የመያዝ፣ ውክልና የመስጠት፣ የማከራየት ወይም የመሸጥ መብቶችን እንዲጠቀሙ ያስችላል።

የንብረት ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ ሀገራት ከሚያወጡት ሕግ ባለፈ ዓለም አቀፍ ሕግጋት እና ስምምነቶችም ይተገበራሉ። ይህ መሆኑም ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብት የማፍራት መብትን ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ የንብረት ባለቤትነት መብት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች (Universal Declaration of Human Rights) ድንጋጌ አንቀጽ 17 ላይ ዕውቅና ተሰጥቶታል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት ማንኛውም ሰው ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመሆን ንብረት የማፍራት መብት እንዳለው፤ ንብረቱንም በዘፈቀደ እንደማይነጠቅ ተደንግጓል። የግል ንብረት ሕህዝብ ጥቅም ሲባል የሚወሰድ ቢሆን እንኳ በቂ ካሳ ሊሰጥበት እንደሚገባ ተቀምጧል::

የንብረት መብት በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ እንደሌሎች መሠረታዊ መብቶች ሁሉ የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ለንብረት መብት ዕውቅና በመስጠት ጥበቃ ያደርጋል:: በዚሁ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ እንደሚከበርለት፣ ንብረት የመያዝና በንብረት የመጠቀም፣ የሌሎች መብት ሳይቃረን ንብረቱን የማስተላለፍ መብቶችን ያጎናፀፈ ነው፤ በሌላ በኩል የግል ንብረት ባለቤትነት መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብቻ ለንብረቱ ተመጣጣኝ ካሳ በቅድሚያ በመክፈል የግል ንብረትን ለመውሰድ እንደሚችል ይደነግጋል::

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ኢትዮጵያዊ ማሕበራት ወይም ሌሎች በሕግ በተለየ በጋራ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ማሕበረሰቦች በጉልበታቸው፣ በፈጠራ ችሎታቸው ወይም በካፒታላቸው ያፈሩት ተጨባጭ የሆነና ተጨባጭነት ጠባይ ሳይኖረው ዋጋ ያለው ውጤት ነው። ድንጋጌውም ሰዎች በሦሰት መንገዶች ንብረት ማፍራት እንደሚችሉ ነው የሚያብራራው::

እነዚህም ጉልበታቸውን ተጠቅመው የሚያፈሩት፣ በትምህርት ወይም በልምድ በሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የሚፈጥሩት ነገር እና ካፒታላቸውን አፍስሰው የሚያገኙት ትርፍ የሚሉት ናቸው።

በተመሳሳይ ንብረት በይዞታ፣ በግዥ፣ በስጦታ እና በውርስ ሊገኝ ይችላል:: ለንብረቱ  የባለቤትነት  መብት በሕግ አግባብ ያገኘ  ሰው የመሸጥ፣ የማስተላለፍ እና የማውረስ መብትም ይኖረዋል::

ሰዎች በሀብት ማግኛ መንገዶች የሚፈጥሩት ወይም የሚያፈሩት ንብረት ተጨባጭነት ያላቸው (ኮርፖሪያል) ወይም የተጨባጭነት ጠባይ የሌላቸው (ኢንኮርፖሪያል) ሊሆኑ እንደሚችሉም በሕገ መንግሥቱ 40(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል::

የኮርፖሪያል ንብረት በዓለም ላይ ተጨባጭ ህልውና ያለው (የሚታይ ወይም የሚጨበጥ) ሲሆን እንደ መሬት፣ ቤት፣ ጌጣጌጥ፣ ብር ወዘተ ካሉ ቁሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው። የማይጨበጥ ንብረት ደግሞ ሕልውናው ወይም መኖሩ የማይታይና የማይዳሰስ ሲሆን የቅጅ መብት እና የንግድ ምልክት መብት እንደ ምሳሌ ሊታይ ይችላል::

ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቀሳቀስ በሚልም ንብረት ሊከፈል እንደሚችል በሕጉ ተቀምጧል፤ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚባሉት ቴፕ፣ መጽሐፍ፣ ቦርሳና የመሳሰሉት ናቸው:: እነዚህን ንብረቶች ባለመብት ነኝ ለማለት የባለቤትነት ማረጋገጫ ሳያስፈልጋቸው ይዞ መገኘት ብቻ በቂ ይሆናል:: እንደ መኪና  ያለ ንብረት ደግሞ ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆኑ ይዞ መገኘት ብቻ ሳይሆን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ ሊኖራቸው ይገባል::

በንብረት መብት ላይ ያሉ ገደቦች

ሰዎች ንብረት የማፍራት እና የመጠቀም መብት ያላቸው ቢሆንም ከገደብ የፀዳ ወይም ፍፁም የሆነ መብት አይደለም:: ለሕዝብ ጥቅም እንዲሁም ለአካባ ጥበቃ ሲባል ገደቦች ሊጣሉ ይችላሉ:: ገደቡ ሲጣል ታዲያ ተገቢ ካሳ መሰጠት እንዳለበት ሕጉ ያስገድዳል::

የአንድ ንብረት ባለቤት  በንብረቱ ላይ ያለው ሥልጣን መሸጥ፣ ራሱ መገልገል፣ ለሦስተኛ ወገን በሥጦታ  እና በውርስ ማስተላለፍ ይችላል:: አንድ ሰው ንብረቱን ማስተላለፍ በፈለገበት ጊዜ ደግሞ በሥሙ የተመዘገበውን ቤት በሽያጭ የማስተላለፍ ከፈለገ  ንብረቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ፣ መኪና ከሆነ ሊብሬ ማቅረብ ይገባዋል:: ለዚህም በቀበሌው ቤቱ (ቦታው) መኖሩ፣ ከዕዳ ነጻ መሆኑ እና ለሌላ ሰው አለመተላለፉ መረጋገጥም አለበት::

ሰዎች በይዞታ በሚይዙት ንብረት ላይ በብቸኝነት የማዘዝ መብት አላቸው:: ነገር ግን  ይህ መብት ከባለሀብትነት መብት አንጻር ፍጹም ባለመሆኑ ንብረቱን በእጅ በማድረግ የመገልገል እና ፍሬውን የመጠቀም መብት ካልሆነ በስተቀር ዋነኛውን ንብረት በሽያጭም ሆነ በሌላ መንገድ ለሌላ ወገን አሳልፎ የመስጠት ወይም የመሸጥ መብት አይኖራቸውም:: ምክንያቱ ደግሞ የይዞታ ንብረቶች የሌላ ሰው መብት በውስጣቸው ሊኖር ለሚችል ነው:: ለምሳሌ ብድር ካለበት (ማስያዣ ከሆነ) እዳው ተከፍሎ እስከሚያልቅ ባለሀብቱ ንብረቱን የመሸጥ መብት አይኖረውም::

ምንጭ:- የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር።

 

መረጃ

ንብረት ማግኘት የሚቻልባቸው መንገዶች:-

 

በይዞታ፣

በግዥ፣

በስጦታ እና

በውርስ፡፡

 

የንብረት ዓይነቶች:-

– ተንቀሳቃሽ ንብረቶች

ቴፕ፣ መጽሐፍ ፣ ቦርሳና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

– ልዩ ተንቀሳቃሽ

ለምሳሌ የመኪና ባለቤትነት

– የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች

መብቱን በመያዝ (ይዞታ) ፣ ስጦታም ፣ ግዥም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በሥሙ የተመዘገበ ሰነድ ያለው መሆን ይገባዋል፡፡፡፡

 

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here