የኢትዮጵያዊያን እናት

0
75

“የመኮንን እናት ምነው ምን ነካዎ”

ብቸኛ ጓዶዎን ጥለው መሄድዎ፤…” ተብሎ በቀብራቸው ላይ ተገጥሟል፡፡ ኢትዮጵያዊያን  ባሳዩት ደግነት እና ሰብአዊ አገልግሎት ያውቋቸዋል። የሕፃናት ማቆያ፣ የእጅ ሥራ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም የሴቶች ትምህርት ቤት በማቋቋም የመጀመሪያዋ ንግሥት ናቸው። ግርማዊት እቴጌ መነን አስፋው፡፡

ግርማዊት  እቴጌ መነን መጋቢት 25 ቀን 1883 ዓ.ም በወሎ ጠቅላይ ግዛት  በአምባሰል አውራጃ ልዩ ስሙ ዕጎ ከተባለው ቀበሌ ከጃንጥራር  አስፋው እና ከወ/ሮ ስሀን ሚካኤል ተወለዱ። ‹‹መነን›› የሚለው ቃል በአማርኛ ቋንቋ የሴት ልጅ ስም ሲሆን ታላቁ ምሁር ዓለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹ቀጭን ፈታይ፣ ባለሙያ፣ መልከ መልካም፣ ትክክል፣ ፍጽምት፣ ሕጸጽ የሌለባት›› ማለት እንደሆነ ጽፈዋል። እቴጌ ማለትም የንጉሠ ነገሥቱ ሚስት፣ ባለዘውድ ማለት ሲሆን፤ የዐረቢኛው “አታጂያ እቴጌ” ጋር ተመሳሳይ ትርጓሜም አለው። በዐረብኛ ቋንቋ ታጅ ማለት ዘውድን የምትቀዳጅ ንግሥት ማለት ነው።

እቴጌ መነን በልጅነት  ዘመናቸው በእናት በአባታቸው ቤት መምህር ተቀጥሮላቸው አማርኛ ማንበብና መፃፍ ጠንቅቀው አወቁ። በተጓዳኝ ልዩ ልዩ የቤት ባልትና ሙያዎችን ተምረው በማጠናቀቃቸው የቤት ራስ  ለመባል በቅተዋል በማለት አንጀሊ ፓርኔል “የእቴጌ መነን አስፋው የሕይወት ታሪክ፡ የኢትዮጵያዊያን እናት” በሚል በጻፉት መጽሐፍ ገልጸዋል፡፡

እቴጌ መነን በ1892 ዓ.ም ለመጀመሪያ ባለቤታቸው  ተዳሩ፡፡ ከዓመታት በኋላ ከእኝህ ባለቤታቸው ወ/ሮ  በላይነሽ ዓሊን እና ጃንጥራር አስፋው ዓሊን ወለዱ፡፡ ከዚያም  ሁለተኛ ባለቤታቸውን በማግባት ጃንጥራር ገብረእግዚ አብሄር አመዴንና ወ/ሮ ደስታ አመዴን ወልደዋል፡፡ በ1903  ዓ.ም ወደ  መጀመሪያ ራስ ልኡልሰገድ አጥናፍሰገድን አገቡ። ይህ ጋብቻ ሳይዘልቅ ቀረና በዚያው ዓመት የመጨረሻ ባለቤታቸውን ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ)ን አገቡ፡፡። የእቴጌ መነን እና  የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋብቻ ፓለቲካዊ ሲሆን የአጎታቸውን የልጅ ኢያሱንና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጠብ ለማስወገድ  ይቻላል በሚል መኳንንቱ ሁሉ በተለይም እነራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው መክረው የፈፀሙት ነበር፡፡

እቴጌ መነን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ያፈሯቸው  ልጆች ስድስት ሲሆኑ ዝርዝራቸውም የሚከተለው ነው፤ ልዕልት ተናኘወርቅ ኃይለሥላሴ፣ ልዑል አልጋወራሽ እስፋወሠን ኃይለሥላሴ፣ ልዕልት ዘነበወርቅ ኃይለሥላሴ፣ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ፣ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ እና ልዑል ሣህለሥላሴ ኃይለሥላስ ናቸው፡፡ እቴጌ መነን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር በተጋቡ በ20 ዓመታቸው  ማለትም 1923 ዓ.ም  የእቴጌነት ዘውድ ጫኑ፡፡ በእድሜ  ዘመናቸው በግል  ገንዘባቸው  በኢትዮጵያ እና  በእየሩሳሌም  በርካታ ቤተክር ስቲያናትን  አሳንፀዋል፡፡ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን እና ተቋማትን አቋቁመዋል፡፡

አንዳንዶችን ለመጥቀስ ያህል  መጋቢት 16 ቀን 1910 ዓ.ም የሐመረ- ኖህ ኪዳነምህረት  ቤተ-ክርስቲያንን  አሠሩ፡፡ በ1923  ዓ.ም  በመስከረም ወር  እቴጌ መነን ተማሪ ቤትን  አቋቋሙ፤  በ1925 ዓ.ም በፉሪ ቀበሌ የምትገኘውን የቅድስት ሐናን ቤተከር ስቲያን አሠሩ፤ በመስከረም ወር 1926 ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው በዮርዳኖስ ያሰሩትን የቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያንን እርሳቸው  በተገኙበት አስመረቁ፤ በ1935 ዓ.ም ለገሀር የሚገኘውን የእጅ  ጥበብ ት/ቤት አቋቋሙ፤ በ1939 ዓ.ም የካቲት ወር ሰበታ ከተማ  የምትገኘውን የጌቴሴማኒን ቤተክርስቲያን በገንዘባቸው አሠሩ፤  በ1943 ዓ.ም ወደግሸን ማርያም ቤተክርስቲያን የሚወጣውን የሰርጥ መንገድ አሠሩ፡፡ በዚሁ ዓመት በጠላት ዘመን ፈርሶ የነበረውን የቦሩ ሥላሴን ብር ወጪ አድርገው አሠሩ፡፡

ግርማዊት እቴጌ መነን ኢየሩሳሌምን ለመሳለም እና በዮርዳኖስ ያሠሩትን ቤተክርስቲያን ለመመረቅ አድካሚ ጉዞ አድርገዋል፡፡ ጉዟቸውም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በባቡር፤ ከጅቡቲ ግብፅ በመርከብ፤ ከግብፅ ወደ ኢየሩላሌም በባቡር ነበር፡፡ አቡነ ቄርሎስም አዲሱን ቤተክርስቲያን  ለማየትና ለመባረክ ከግርማዊት እቴጌ ጋር አብረው መጓዛቸው ተዘግቦ ይገኛል፡፡

ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለነፃነት ተጋድሎው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን እንደሚወር  ይፋ በሆነበት ጊዜ ግርማዊት እቴጌ መነን መስከረም 1  ቀን 1928  ዓ.ም የዘመን መለወጫ ዕለት ለዓለም ሁሉ ሴቶች የትግል ጥሪ  አድርገው ነበር፡፡ በንግግራቸውም “…በሀገራችን እና በሕዝባችን ላይ የአጥቂነት ሥራ ሊደረግበት  በሚዘጋጅበት ጊዜ ሰላምን እና ነጻነትን ለማጽናት የቆመው የዓለም ሴቶች ማኅበር ስለገለጠልን የጋለ ወዳጅነት አሳብ ጥልቅ የሆነ ምስጋናችንን ስናቀርብላችሁ ደስ ይለናል፡፡ …በዓለም ያላችሁ ሴቶች ሁሉ  በዓለም ላይ እውነተኛ ፍርድና ሰላም እንዲነግስ የመንግሥት ሰዎች ሁሉ በሚሠሩት ሥራ በእግዚአብሔር መንፈስ እንዲመሩ በምናደርገው ፀሎት ተባባሪዎች እንድትሆኑ እንለምናለን” የሚል ነው።

እቴጌ መነን በ1928 ዓ.ም ግርማዊ ባለቤታቸው ጦር ሜዳ ሄደው  ከጠላት ጋራ ስላገራቸው ሲዋጉ በከተማው ያሉ ወይዛዝርትን እያሰበሰቡ ለቁስለኞች እና ለሠራዊቱ የሚሆን ስንቅ፣ ትጥቅ እና የህክምና ቁሳቁስ እያዘጋጁ ይልኩ ነበር፡፡ የከተማውም ፀጥታ እንዲጠበቅ ከከተማው የዘበኛ ኃላፊዎች ጋር በመመካከር በትጋትና በብርታት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

በጦር ሜዳ ካሉት ባለቤታቸው እና  በዚያው ከሚገኙ የመረጃ ሰዎች የጣሊያን አውሮፕላኖች በአዲስ  አበባ በሚኖረው በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የቦንብ ጥቃት ለማድረስ እና  ህፃን፣ ሽማግሌ እና ሴት ሳይለይ በአንድነት ለመደምስስ እየመጡ  እንደሆነ በስልክ በተላለፈ ጊዜ ግርማዊት እቴጌ መነን በአውቶሞቢል ሆነው በድፍረት በከተማው እየዞሩ በየመንገዱ እና በየገበያው  ያለው ሕዝብ በአንድነት እጅብ ብሎ መቆሙን ትቶ እንዲበተን እና አደጋውን ወደሚከላከልበት ቦታ እንዲደበቅ በማድረጋቸው ብዙ ሕዝብ ሊድን ችሏል፡፡

እቴጌ መነን በፓለቲካዊ አስተሳሰብ የተነሳ  የእናታቸው የወይዘሮ ስህን ወገኖች በተለይም አያታቸው ንጉሥ ሚካኤል እና አጎታቸው ልጅ ኢያሱ ከባለቤታቸው ከቀዳማዊ ኃይለሥላሤ ጋር በፈጠሩት ፓለቲካዊ ቅራኔ  ሰበብ በተካሄደው የሰገሌ ጦርነት  ከግራ ከቀኝ ተሰልፈው የተዋጉ ወገኖቻቸው ያለቁባቸው ቢሆንም በየጊዜው ሁለቱንም ወገኖች እያስማሙ በአንድነት እንዲኖሩ  አስችለዋል፡፡

እቴጌ መነን አስፋው የዐፄ ፋሲል ተወላጅ ናቸው፡፡ ከዐፄ ፋሲል ጀምሮ  የዘር ሃረጋቸው ሲመዘዝ አያታቸው ንጉሥ ሚካኤል ስምንተኛ ትውልድ ናቸው፡፡ እናታቸው ወ/ሮ ስሀን ዘጠነኛ እራሣቸው ግርማዊት እቴጌ መነን አስፋው ደግሞ አስረኛ ትውልድ ናቸው፡፡  በዐፄ ፋሲል በኩል እቴጌ መነን አስፋውና ቀዳማዊ ኃይለሥላሤ  ዝምድና አላቸው። ዝምድናቸው ግን ጋብቻ የማይከለክል ሲሆን  አሥራ ሁለተኛ ትውልዳቸው ላይ የሚገጥም ነው፡፡

እቴጌ መነን አስፋው የካቲት 9 ቀን 1954 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፤ ሥርዓተ ቀብራቸውም በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል፡፡ በተቀበሩበት ዕለት ከተሰሙት የሃዘን እንጉርጉሮ ዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የመኮንን እናት ምነው ምን ነካዎ፣

ብቸኛ ጓዶዎን ጥለው መሄድዎ፡፡

እረ ምን ይወራል ምን ትንፋሽ አለና፣

መነን ስታቋርጥ የሞትን ጉዳና፡፡

መኮንን ገሥግሦ ሥላሤ መግባቱ፣

ቤት ሊሠራ ኖሯል ለወላጅ እናቱ።

 

ሳምንቱ በታሪክ

 

ራስ ቢትወድድ ተወለዱ

ታላቁ ደራሲና ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ራስ ቢትወደድ መኰንን እንዳልካቸው የካቲት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ተወለዱ። አርበኛ፣የውጭ ጉዳይ አደራዳሪ፣ ደራሲ እና በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡

ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ ካርቱም ከሚገኘው ከሦስት የጦር መኮንኖች ትምህርት ቤቶች ተመርቀዋል፡፡ በዳግማዊ ሚኒልክ ትምህርት ቤት ሳሉ የትምህርት እኩዮቻቸው ልጅ ተፈሪ መኮንን ( በኋላ ዐፄ ኃይላሤ እና ልጅ እምሩ ኃይለ ሥላሤ (በኋላ ራስ እምሩ) ነበሩ፡፡

ራስ ቢትወደድ መኮንን የሕልም ሩጫ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የጀመረው የሥልጣን ጉዟቸው የልጅ እያሱ እንደራሴ የነበሩት አጎታቸው ራስ ተሰማ ናደው ካረፉ በኋላ በተለያዩ ባለሥልጣናት እንደተገታ ጽፈዋል፡፡

ዶንግ ዥያው ፒንግ

የአዲሲቷን ቻይና የሰብዓዊ እና ኤኮኖሚካዊ ገጽታዎች በማነጽ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን የያዘችውን የኤኮኖሚያዊ ኃያልነት ሥፍራ እንድትይዝ ያስቻሏት መሪዋ ዶንግ ዥያው ፒንግ የካቲት 12 ቀን 1989 ዓ.ም አረፉ።

ቻይና አሁን ላለችበት ኃያልነት እና የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ከማኦ ዘዶንግ ቀጥሎም የቻይናን ሁለንተናዊ እድገት የቀረጹ እንደሆኑ የብሪታኒካ መረጃ ያሳያል፡፡

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here