ታሪካዊቷ ደብረ ታቦር

0
94

ደብረ ታቦር በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ፣ በኢትዮጵያ ታሪክም ከፍተኛ ስፍራ ያላት ከተማ ናት። በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መዲና ሆና በማገልገሏ “የንጉሦች ከተማ” ተብላ ትጠራለች። ደብረ ታቦርን መጎብኘት የታላላቅ ነገሥታትን ፈለግ መከተል፣ የዘመናዊነትን ትልም መረዳትና ጥንታዊ መንፈሳዊ ዕሴቶችን በአንድ ላይ መቃኘት ማለት ነው።

 

ታሪክ እና የፖለቲካ ማዕከልነት

ደብረ ታቦር ምንም እንኳን በ13ኛው ክፍለ ዘመን እንደተቆረቆረች ቢነገርም፣ ዝናዋ ናኝቶ የታወቀችው ግን በዘመነ መሳፍንት ማብቂያ አካባቢ ነው። ከተማዋ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በራስ አሊ አልጋ ዘመን የመንግሥት መኖሪያና የፖለቲካ ማዕከል ሆና ተመሠረተች። በዚያ ወቅት የአካባቢው የአስተዳደርና የጦር እንቅስቃሴ ማዕከል ሆና አገልግላለች።

የከተማዋ ስያሜ በኢየሩሳሌም ከሚገኘውና ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን ከገለጠበት “ደብረ ታቦር” ተራራ የተወሰደ ነው።

ከተማዋ እቴጌ መነን እና ሌሎች ታላላቅ መሪዎች የኖሩባት በመሆኗ የታሪክ ክብሯ የላቀ ነው።

ከደብረ ታቦር ታሪክ ጋር ስማቸው የማይነጣጠለው ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው። ንጉሡ በ1847 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ሆነው እንደነገሡ፣ ቀደም ሲል የራስ አሊ መቀመጫ የነበረችውን ደብረ ታቦርን ዋና ከተማቸው አደረጓት። ለዚህ ምርጫቸው ዋነኛው ምክንያት የከተማዋ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ሲሆን ደብረ ታቦር ከጎንደር፣ ከወሎ እና ከሸዋ ጋር ለመገናኘት እጅግ ምቹ ነበረች።

ንጉሡ ደብረ ታቦርን የመረጡበት ሌላው ምክንያት ከአየሯ ቅዝቃዜ በተጨማሪ ለጦር ስልት አመቺ የሆነውና ጠላት በሩቁ የሚታይበት ከፍታ ስላላት ነው። በዚህም ምክንያት ቤተ መንግሥታቸውን አስገንብተው የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አደረጓት።

በከተማዋ ውስጥ በድንጋይና በኖራ የታነጹ ሕንፃዎችንና ለቤተሰቦቻቸው መኖሪያ የሚሆኑ ቤቶችንም አሳንጸው ነበር። ዛሬም ድረስ በከተማዋ ውስጥ “የቴዎድሮስ አደባባይ”  እና የተለያዩ ታሪካዊ ፍርስራሾች  የዚያን  ዘመን ትዝታ  ይዘው ይገኛሉ።

የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ትልቁ ሕልም ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ማዘመን ነበር። ለዚህም ደብረ ታቦር አጠገብ የሚገኘውን ጋፋት የተባለውን ስፍራ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር አደረጉት። በዚህ የታሪክ ስፍራ ንጉሡ የአገር ዘመናዊነትን ለማሳደግ የመሣሪያ እና የብረት ሥራ ማዕከል አቋቁመው ነበር።

በጋፋት ከአውሮፓ የመጡ ሙያተኞች ከኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን የጦር መሣሪያዎችን እና ሌሎች የብረት ሥራዎችን ይሠሩ ነበር። በዚህ ስፍራ ነበር በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ታላቅ የቴክኖሎጂ ውጤት ተደርጎ የሚወሰደው እንዲሁም ከሰባት ቶን በላይ የሚመዝነው “ሴባስቶፖል” መድፍ የተሠራው። ዛሬ ጋፋት መንደር ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ዘመን የቴክኖሎጂ ሙከራ ምስክር በመሆን ለታሪክ ፈላጊዎችና ለጎብኚዎች የሚስብ ቅርስ ሆኖ ይገኛል።

 

ቤተ መንግሥቶች እና ቅርሶች

ደብረ ታቦር በዘመነ መሳፍንት ዘመን የፖለቲካ ማዕከል ስለነበረች ብዙ ታሪካዊ ቤተ መንግሥቶች ይገኙባታል።

 

የራስ አሊ ቤተ መንግሥት

ራስ አሊ ከተማዋን እንደ መኖሪያና የአስተዳደር ማዕከል በመጠቀም ቤተ መንግሥቱን አቋቁመው ነበር። ይህ ስፍራ በዘመነ መሳፍንት ወቅት ታላላቅ የፖለቲካ ውሳኔዎች የተላለፉበት ቦታ ነው።

 

የእቴጌ መነን ቤተ መንግሥት

የእቴጌ መነን ቤተ መንግሥት የዚያን ዘመን የንጉሣዊ ሕንፃ አሠራርና የአካባቢውን የሕንፃ ባሕል የሚያሳይ ድንቅ ቅርስ ነው።

 

የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት

የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በከተማዋ በነበሩበት ወቅት ይጠቀሙባቸው የነበሩ የህንፃ ፍርስራሾች እና የታሪክ ምልክቶች ዛሬም ድረስ ይገኛሉ።

 

ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት

ደብረ ታቦር የታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት ማዕከልም ናት። ደብረ ታቦር ኢየሱስ (ማርያም)፣ ቅዱስ ገብርኤል (ዳግማዊ ቁልቢ)፣ የአቡነ መርቆሬዎስ ቤተክርስቲያን እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

 

ደብረ ታቦር ኢየሱስ (ማርያም)

ይህ ቤተክርስቲያን ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ጥልቅ ቁርኝት አለው። ንጉሡ ቤተክርስቲያኑን በማሳደስና በመጠገን ረገድ ትልቅ አሻራ አሳርፈዋዋል። ብዙ ጊዜያቸውንም በጸሎት የሚያሳልፉትና መንፈሳዊ ምክሮችን የሚሰሙት እዚሁ ደብር ነበር።

 

ቅዱስ ገብርኤል (ዳግማዊ ቁልቢ)

ይህ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት ማዕከል ብቻ ሳይሆን በርካታ ታሪካዊ ዕቃዎችንና የእምነት ቅርሶችን የያዘ መዳረሻ ነው።

 

የአቡነ መርቆሬዎስ በዓል

በደብረ ታቦር በየወሩ በ25ኛው ቀን የሚከበረው የመርቆሬዎስ በዓል ልዩ ድምቀት አለው። በቅዱስ መርቆሬዎስ ስም የተሰየመው ቤተክርስቲያን ዙሪያ ብዙ ምዕመናን በመሰብሰብ ቅዳሴ፣ ጸሎትና ማህሌት ያደርሳሉ። በዓሉ የእምነት ጽናትና የመንፈሳዊ አንድነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

 

የተፈጥሮ ውበት እና የቱሪስት መስህቦች

ደብረ ታቦር በተፈጥሮ ውበቷም የታደለች ናት። ለከተማዋ መቆርቆር ምክንያት የሆነው የታቦር ተራራ ከላዩ ላይ ሆኖ የደብረ ታቦርን ከተማ እና አካባቢዋን ማራኪ ተፈጥሮ ለመመልከት ምቹ ነው። ተራራው የመንፈሳዊ ጉዞም መዳረሻ ስፍራ ነው።

ከተማዋ ከአዲስ አበባ 667 ኪሎ ሜትር እና ከባሕር ዳር ከተማ ደግሞ 102 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛች፤ በመንገዷ ላይ ያሉትን እንደ ጉና ተራራ ያሉ አስደናቂ የተፈጥሮ መስህቦችንም ለመጎብኘት ዕድል ትሰጣለች። በተጨማሪም ከጣና ሐይቅ እና ከጎንደር ከተማ ቅርብ (155 ኪሎ ሜትር አካባ) መሆኗ በጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ ያደርጋታል።

ደብረ ታቦር የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት አና የባሕል ታሪክ የሚያሳዩ እጅግ አስፈላጊ ቅርሶች ያሉባት ከተማ ናት። የራስ አሊ እና የእቴጌ መነን ቤተ መንግሥቶች፣ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት እና ቅርሶች፣ የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር እንዲሁም የታቦር ተራራ መገኛ ሙሆኗ ከተማዋን የባሕልና ታሪክ ማዕከል ያደርጋታል። ዛሬም ድረስ የነገሥታቱን ትዝታ እና የዘመናዊነት ሙከራዎችን አቅፋ የያዘችው ደብረ ታቦር፣ ለታሪክ ተመራማሪዎች እና ለጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ ሆና ትቀጥላለች። እኛም ይህቺን የታሪክ ማዕከል እንዲሁም “የንጉሦች ከተማ”  በሚል የምትጠራውን ደብረ ታርን እንድትጎበኙ በመጋበዝ ሽርሽራችንን በዚሁ ቋጨን፡፡

 

 

አጭር እውነታ

 

  • በ18ኛው ክፍለ ዘመን የንጉሥ መኖሪያ ከተማ ነበረች።
  • ከተማው በተራራማ አካባቢ ስለምትገኝ አየር ንፁህና ቀዝቃዛ ነው።
  • የኦርቶዶክስ እምነት ታላላቅ ቤተክርስቲያናትና በዓላት የሚታወቅባት ከተማ ናት።
  • ከጣና ሐይቅ አቅራቢያ ስለምትገኝ የቱሪዝም እድል አላት።
  • እርሻ እና ንግድ ዋና የኢኮኖሚ መሰረቶች ናቸው።
  • የመርቆርዮስ በዓል እና ሌሎች የሃይማኖት በዓላት በታላቅ መንገድ ይከበራሉ።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here