ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ውጤታማ ተግባር!

0
18

ዓመታዊው የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በአማራ ክልል እየተከናወነ ነው:: ከታኅሣሥ 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ዘጠኝ ሺህ 206 ተፋሰሶች የተለዩ ሲሆን ሥራው እየተከናወነ ያለው በ456 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ነው:: አራት ነጥብ አምስት ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በሥራው እየተሳተፉ ይገኛሉ:: በሥራው እየተሳተፉ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንደገለጹት ሕዝቡ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው እየተሳተፈ ያለው ያለማንም ቀስቃሽ በራሱ ተነሳሽነት ነው::

በሕዝቡ ተሳትፎ  በያመቱ በሚከናወነው በዚህ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለብዙ ዓመታት በከፍተኛ ጎርፍ አፈሩ እየተወሰደ ወደ ገደልነት ተቀይሮ ሰው አላሳልፍ ብሎ የነበረው መንገድ   ወደ ቀደመ ገጽታው ተመልሷል::

በየዓመቱ የሚሠሩ እርከኖችን  ዘላቂ ለማድረግ የሚተከሉ ሳሮች እና ችግኞችም  ለከብት መኖነት እያገለገሉ ነው:: ከከፍታ ቦታ የሚወርደው ጎርፍ ወደ ሰፈር በመግባት በሰው፣ በእንስሳት እና በቤት ላይ ያደርስ የነበረው ጉዳትም ቢሆን በእጅጉ ቀንሷል::

ይህ ለውጥ  ሁሉም ወገን በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በንቃት እንዲሳተፍ አድርጎታል::

ተቋማትም ለአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ይገኛሉ::

የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ የአፈር ለምነትን ከመጨመር ባለፈ ለአርሶ አደሮችም ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እና ገቢ እያስገኘ ነው። አርሶ አደሮቹ  በእንስሳት ማድለብ፣ በፍራፍሬ ልማት፣ በንብ እርባታ እና በደን ልማት በመሰማራት ገቢ ማግኘት ችለዋል::

እየተሠራ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ሥራ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የውኃ አካላትን በማጎልበት ረገድም ሁነኛ ሚና እየተጫወተ ነው::

በተለይም በአፈር አሲዳማነት በተጎዱ አካባቢዎች የተከናወኑ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ሥራዎች አካባቢዎቹ ወደ ምርት እንዲመለሱ አድርገዋል:: አምስት መቶ ሀያ ስምንት የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተቋቁመው ከተፋሰሶች የሚያመነጩትን ሃብት ወደ ገቢ በመቀየር አርሶ አደሮችን የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ አድርገዋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ሥራዎች የታየው ውጤት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከነበረው ስጋት መውጣት እንደሚቻል ያመላከተ ሆኗል:: የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ምንጮች እንዲጎለብቱ በማድረግ ለመስኖ ልማት ትልቅ አቅም ሆነዋል:: በተጨማሪም የማሳ ላይ እርከን እና መሰል የተፋሰስ ሥራዎችም ምርታማነትን በማሳደግ፣ የጓሮ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት የገበያ ሰብሎችን በማምረት ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ አቅም እየሆኑ ነው::

የወል መሬቶችን ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ ወጣቶችን በማደራጀት በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በማድለብ፣ በንብ ማነብ እና መሰል ሥራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል። በዚህም የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለተፋሰስ ልማት ሥራ ተጨማሪ አቅም ሆኗል፣ ምርታማነትም በማሳደግ የግብርና ውጤት የሆኑ ምርቶችን ዋጋ በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

“በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ደጋማ አካባቢዎች የተከናወኑ መደበኛ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የአርሶ አደሮች ተቀባይነት እና አጠቃቀም” በሚል ርዕስ የተሠራ ጥናት ውጤት እንዳመለከተው ከላይ ወደ ታች የሚመጣ ትዕዛዝን ማቆም፣ ቴክኖሎጂዎችን እንደየአካባቢው ሥነ-ምህዳር እና አርሶ አደሩ ኑሮ ተግባራዊ ማድረግ፣ አርሶ አደሩ ችግሩን እንዲረዳ እና መፍትሄውንም አብሮ እንዲያመነጭ ማድረግ ለበለጠ ውጤት ያበቃል:: ስለሆነም አርሶ አደሩ  የሥራው ባለቤትም ሆነ ተጠቃሚ ራሱ መሆኑን እንዲረዳ በማድረግ እንዲሁም በማሳተፍ እየተከናወነ ያለው ይህ በውጤት የታጀበ  ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት::

 

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here