የአፈጣጠር ችግር መንስኤ እና መፍትሔዎች

0
249

የአፈጣጠር ችግር ጨቅላ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ለአጭር እና ለረዥም ጊዜ የጤና እክል የሚያስከትል ችግር ነው:: ከሰሞኑም ከአፈጣጠር ጋር የሚከሰቱ የጤና እክሎችን ለማከም የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክ ሾፕ (አውደ ጥናት) በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል::

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ እንደተገለጸው የጨቅላ ሕጻናት የአፈጣጠር ችግር ማለት ሕጻናት ሲወለዱ አብሯቸው የሚኖር የአካላት አወቃቀር ወይም  የአሠራር ጉድለት ነው:: የጨቅላ ሕጻናት የአፈጣጠር ችግር አንደኛው የጨቅላ ሕጻናት ሞት መንስኤም ነው::

 

የአፈጣጠር ችግር አይነቶች

በርካታ የአፈጣጠር ችግሮች ያሉ ሲሆን የተለመዱትን ለመዘርዘር ያህል፡-

የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ (የሕፃኑ የላይኛው ከንፈር ወይም የአፍ ጣሪያ ሙሉ በሙሉ ሳይገጥም ሲቀር በአመጋገብ እና በንግግር ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ክፍተቶችን ይፈጥራል)፣ የእግር መቆልመም (የእግር ወደ ውጭ ወይም ወደ ውስጥ በመታጠፍ በአግባቡ ለመራመድ ሲያስቸግር፣ የልብ ክፍተት (በልብ ውስጥ ያሉ ቀዳዳዎች ወይም የተበላሹ ቫልቮችን ወይም መተላለፊያ ያካትታሉ)፣ የጭንቅላት ውኃ መቋጠር፣ የጨጓራ ዕጢ (gastroschisis) ወይም የሆድ ግድግዳ ላይ ክፍተት መኖር፣ የአዕምሮ ውስንነት እና የነርቭ ቱቦ ጉድለቶች በአንጎል እና በአከርካሪ አጥንት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ከባድ የአፈጣጠር ችግሮችም ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ለውጦች በማንኛውም የሕጻናት የሰውነት ክፍል ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ::

 

መንስኤዎች (አጋላጭ ነገሮች)

የአፈጣጠር ችግር ትክክለኛ ምክንያቱ ባይታወቅም አጋላጭ ምክንያቶች ግን አሉት:: ከዘረ መል እና ከመኖሪያ አካባቢ (environment) ጋርም ሊያያዝ ይችላል:: በእርግዝና ጊዜ ሐኪምን ሳያማክሩ የተለያዩ መድኃኒቶችን መውሰድ፣ ትንባሆ (ሲጋራ) ማጨስ፣ አልኮል አብዝቶ መጠጣት፣ ጫት መቃም፣ ለጨረር መጋለጥ፣ የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ፣ ቀድሞ የነበሩ ሕመሞችን አለመቆጣጠር (እናትየው ስኳር የመሳሰሉ በሽታ ካለባት)፣ የእናትየዋ እድሜ ከፍ ያለ ከሆነ(እድሜ ከ36 ዓመት በላይ መሆን) እንዲሁም ጾታ ወንድ መሆን ከሴቶች ሁለት እጥፍ ለአፈጠጣር ችግር   ተጋላጭ ያደርጋል::

 

ምልክቶች

የጤና ባለሙያ በእርግዝና ወቅት ወይም  ከተወለደ በኋላ የልጅ የአፈጠጠር ችግሮችን መለየት ይችላል:: እንዲሁም አብዛኛዎቹን ችግሮችም   በልጁ  የመጀመሪያ ዓመት ላይ መለየት ይቻላል::

አንዳንድ  የአፈጣጠር ችግሮች ለሕይወት አስጊ ሊሆኑ ይችላሉ::  አንዳንዶቹ ደግሞ የልጁን ገጽታ  ይለውጣሉ:: አንዳንዶቹ ደግሞ አስተውሎታቸው፣ እንቅስቃሴያቸው እና ተግባራቸው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ::

በጨቅላ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ የአፈጣጠር ጉድለቶች እንዳሉ የሚያሳዩ የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፡-  ያልተለመደ የልብ ምት፣ በራሳቸው የመተንፈስ ችግር (በሕክምና መታገዝ)፣ ስማቸው ሲጠራ ወይም ለከፍተኛ ድምፆች ምላሽ አለመስጠት፣ የዓይን እንቅስቃሴ አለመኖር ወይም ከፊት ለፊታቸው ያሉትን ነገሮች አለመከተል፣ የመመገብ ችግር፤ ጭንቅላታቸው፣ ፊታቸው፣ አይናቸው፣ ጆሯቸው ወይም አፋቸው ከተለመደው ተለየ መሆን፣ በዕድሜያቸው የዕድገት ደረጃዎች ላይ አለመድረስ እና በዐይን የሚታዩ አካለዊ ለውጦች ናቸው::

 

ሕክምናዎቹ

የመጀመሪያው የቀዶ ሕክምና ሲሆን ሁለተኛው የተሐድሶ አገልግሎት መስጠት ነው:: የንግግር ክህሎት ሕክምና፣ የልዩ ፍላጎት ትምህት ቤቶችን ማቋቋምም ተገቢ ነው::

 

መከላከያዎቹ

በእርግዝና ወቅት የፎሊክ አሲድ መውሰድ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ቅድመ ውሊድ ክትትል ማድረግ፣ በእርግዝና ወቅት ከአልኮል፣ ከትንባሆ እና ከአደንዘዥ ዕጽ መራቅ፣ ሐኪም ሳያማክሩ መድኃኒቶችን በእርግዝና ወራት አለመውሰድ፣ ከማርገዟ በፊት እናትየው የጤና ሁኔታዋን ማወቅ አለባት::

ወላጆች የወለዱት ልጅ የአፈጣጠር ችግር እንዳለበት ካወቁ ሳይደናገጡ ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ ይጠበቅባቸዋል:: በጤና ተቋም በሰለጠነ ባለሙያ ታግዞ መውለድ ምክንያቱም የአፈጣጠር ችግር ያለበት ሕጻን ቢወለድ እንኳ በፍጥነት የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ ያስችላል::

በግንዛቤ ማስጨበጫ ወርክ ሾፑ ላይ  የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እንዳስታወቀው በተያዘው ወር በክልሉ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን በተለይም የከንፈር እና የላንቃ መሰንጠቅ ያጋጠማቸውን ሕጻናት በነጻ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል:: በዚህም  በደሴ ሰላም ሆስፒታል ከየካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ጋምቢ ሆስፒታል ደግሞ ከየካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሕክምናው ይሰጣል::

ሕክምናው የሚሰጠውም ከአዲስ አበባ በሚመጡ ከዚህ በፊት ይህንን ሕክምና በሰጡ ስፔሻሊስት ሐኪሞች መሆኑን የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ አስታውቀዋል::

ምክትል ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት በክልሉ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕጻናት በሕክምና መርዳት የተጀመረው ከስምንት ዓመት በፊት ነው:: በዚህም ሁለት ሺህ 300 ለሚሆኑ ሕጻናት ሕክምና ተደርጎላቸዋል::

የአፈጣጠር ችግር የጤና ችግር ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖ ያለው ጉዳይ በመሆኑ የተጎዱትን ወገኖች ወደ ሕክምና ማቅረብ እና ማሕበረሰቡ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት መቀየር ዋና ትኩረት የሚደረግበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል::

በጤና ሚኒስቴር የስፔሻሊቲ እና ተሃድሶ አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ሙላቱ በበኩላቸው የአፈጣጠር ችግር ሕክምናን በሁሉም ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ (ሮድ ማፕ) በመቅረጽ በሰው ኃይል ሥልጠና፣ በመሣሪያ አቅርቦት እና በተቋማት ማጠናከር ላይ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::

የአፈጣጠር ችግር በጤና ተቋማት ውስጥ ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን በማንሳት የማኅበረሰብ አመለካከት ለውጥ እና የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል::

በስብስባው   እንደተገለጸው የአፈጣጠር ችግር የሚያስከትለው ጉዳት በርካታ ሲሆን የመጀመሪያው የስነ ልቦና ጫና ነው:: በኢትዮጵያ ሁኔታ አንዲት እናት ልጇን ወልዳ አቅፋ መሳም እንደምትፈልግ እና  በዚህ ጊዜ ልጇ የአፈጣጠር ችግር እንዳለበት ስታይ የእኔ ልጅ አይደለም በማለት ችግሩን አምኖ የመቀበል ጉዳይ እንዳለም ተጠቁሟል:: ይህም የስነ ልቦና ጠባሳ እንደሚያስከትል ነው የተነገረው::

ሌላው የአፈጣጠር ችግር የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ጫና ነው:: ይህ ችግር ያለባቸው ሕጻናት ካደጉ በኋላ ትምህርት ስላልተማሩ (ቀድሞንም በማሕበረሰቡ ይገለላሉ ትምህርትቤት አይገቡም)፤ እንዲሁም እንደ ጤነኛ ሰው ተንቀሳቅሰው ሥራ መሥራት አይችሉም:: ስለሆነም የሌሎች የኢኮኖሚ ጥገኞች ይሆናሉ::

ይህን ችግር ለመቅረፍም ሁሉም የሕብረተሰብ አካል አብዛኛው የአፈጣጠር ችግር መከላከል እና መታከም የሚችል መሆኑን ተገንዝቦ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሕጻናትን እና ታዳጊዎችን ወደ ጤና ተቋማት እንዲወስዱ ጥሪ ቀርቧል::

 

ጤና አዳም

አብዛኛዎቹ የአፈጣጠር ችግሮች የሚከሰቱት በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ነው፡፡

የአፈጣጠር ችግር የአካል እና የስነ ልቦና ጫና ያደርሳል፡፡

አብዛኛውን የአፈጣጠር ችግር መከላከል ይቻላል፡፡

አብዛኛው የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ሕጻናት በደንብ መመገብ ስለሚያስቸግራቸው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያጋጥማቸዋል፡፡

የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ሕጻናት እና ታዳጊዎች ከማሕበረሰቡ መገለል ይደርስባቸዋል፡፡

የአፈጣጠር ችግሮች በእርግማን ወይም በወላጆች ሐጢያት የሚመጣ አይደለም፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 16  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here