በቻይና ሲቹዋን መንደር አሳማ በገመድ አስሮ እና አንጠልጥሎ ሲያጓጉዝ የነበር ሰው አልባ በራሪ “ድሮን” ከከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ጋር ተጠማጥሞ ኃይል ከማቋረጡ ባሻገር ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማስከተሉን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
ዘመናዊው አርቢ አሳማውን ወደ እርድ ቤት ለማጓጓዝ ነበር ስልቱን መርጦ ተግባራዊ ያደረገው:: ግለሰቡ በርቀት መቆጣጠሪያ በሚታዘዝ ድሮን በገመድ አስሮ እና አንጠልጥሎ ሲያጓጉዝ ከከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ጋር ተገናኝቶ ይጠመጠምበታል::
ግለሰቡ የተንጠለጠለውን አሳማ እና የተተባተበውን ድሮን በቀላሉ ማላቀቅ እንደማይችል ሲረዳ በአቅራቢያው ለሚገኝ የሚመለከተው ጣቢያ ያመለክታል::
ጥያቄውን የተቀበለው ጣቢያም 12 ባለሙያዎችን ልኮ ለ10 ሰዓት ባደረጉት ጥረት የተቋረጠውን ኃይል በማስተካከቸው የሲቹዋን መንደር ኗሪዎችም የተቋረጠባቸውን ኃይል ከ10 ሰዓታት በኋላ ማግኘት ችለዋል::
የኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣናት ግን ግለሰቡ በረራ በተከለከለበት ቀጣና ድሮን በማብረሩ ጥፋተኛ መሆኑን ነው ያሰመሩበት:: የኃይል መስመሩን ለማስተካከልም ከ1400 ዶላር ወይም ከ100 ሺህ ብር በላይ ወጪ ማስተከተሉም ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


