በጎ ቅናት እንዲያድርብን

0
228

የመንገድ መሠረተ ልማት ለአንድ ሃገር ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የጀርባ አጥንት ነው፤ ይህንንም በተግባር ያሳዩ ሀገራት በርካቶች ናቸው። በአንጻሩ ደግሞ የመንገድ መሠረተ ልማቶች መጓደል ለመንግሥት የሚደጋገም አሥተዳደራዊ ጥያቄ የሆነባቸው ሀገራትም ብዙዎች ናቸው::

በመንገድ መሠረተ ልማታቸው ተምሳሌት የሚሆኑ ሀገራትን በወፍ በረር ቃኝተን ከሠሯቸው ሥራዎች ለመማር፣ ከስህተቶቻችን ለመታረም እና ባለንበት ክፍለ ዘመን መንገዶች ጥርጊያ፣ የጠጠር ወይም ከሌላ አነስተኛ የመንገድ ፕሮጀክትነት አልፈው በሰው ሠራሽ (በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) እየታገዙ መዘመናቸውን ልብ ልንል ይገባናል::

በዓለማችን ላይ በመንገድ መሠረተ ልማት የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው በርካታ ሀገራት ይገኛሉ:: ለአብነትም ጀርመን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ፣ ቻይና እና ስዊዘርላንድ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱት ሀገራት የመንገድ መሠረተ ልማታቸውን ጥራት በሚለው መስፈርት ያሳለፉ ሀገራት ናቸው:: ለአብነት የተጠቀሱት ሀገራት የመንገድ መሠረተ ልማታቸው በመንገድ ደህንነት፣ በትራፊክ አሥተዳደር እና በቴክኖሎጂ የበለጸጉ መሆናቸውም ሌላኛው የተምሳሌትነታቸው መገለጫ ነው::

ጀርመን አውቶ ባን የሚባለው ከፍተኛ ጥራት ያለው መንገድ ባለቤት ናት:: በጥራቱ ብቻ ሳይሆን በመንገድ ደህንነቱ እና በትራፊክ አሥተዳደሩም በእጅጉ ተሞክሮ የሚወሰድበት መንገድ ነው::

በጀርመኑ አውቶ ባን መንገድ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች የፍጥነት ገደብ የለባቸውም:: ይህ ማለት የመንገዱ የግንባታ ጥራት እና የመንገድ አሥተዳደሩ በቴክኖሎጂ የበለጸገ መሆኑ በመንገዱ ላይ ያለው የእንቅስቃሴ ፍጥነት ገደብ የሌለበት እንዲሆን አስችሎታል::

በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር ማስጓዝ የሚያስችለው መንገዱ 13 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው:: ከፍተኛ የግንባታ (የኢንጂነሪንግ) ክህሎት የተንጸባረቀበት አውቶ ባን የመታጠፊያ ቦታዎች፣ የተከለከሉ አቅጣጫዎች እና ሌሎችም በአግባቡ በተሰናዱ መመሪያዎች የታገዙ ናቸው::

የጃፓን የመንገድ መሠረተ ልማትም ተሞክሮ በዓለም ላይ እጅግ የተሻለ እና ለብዙ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ነው:: ጃፓኖች መንገዶቻቸውን የሚሠሩት ጥራታቸውን በጠበቁ ጥሬ ዕቃዎች (ግብዓቶች) ነው::

የጃፓን የመንገድ ግንባታዎች ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ ወይም በጥቂት ወጪ መጠገን የሚችሉ እንዲሆኑ ተደርገው መሠራታቸውም ተሞክሮ ይወሰድበታል::

በጃፓን የመንገድ ሁኔታን የሚቆጣጠሩ ሴንሰሮች (አንባቢዎች) በየመንገዶቹ መገጠማቸው፣ ያለማቋረጥ የሚሠሩ የመንገድ ብርሃን መቆጣጠሪያዎች እና ስማርት ትራፊክ (የዘመነ የትራፊክ ሥርዓት) ወይም በቴክኖሎጂ የተደገፈ መሆኑም ሌላኛው የመንገድ ልማት ተምሳሌትነት ማሳያ ነው::

አውሮፓዊቷ ኔዘርላንድስም ከመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ አንጻር ለዓለም ሀገራት የምታስተምረው ጥንካሬዎች ባለቤት ናት::

ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብስክሌት መንገዶች ግንባታ ስሟ በከፍታ ይነሳል:: ከ35 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መንገዶችን በጥራት የገነባችው ሀገሪቱ፣ የብስክሌት መንገዶቹ ከመኪና መንገድ የተለዩ እና ደህንነታቸው የተረጋገጠ ነው፤ በመሆኑም ኔዘርላንድሳዊያን የመንግሥት ሠራተኞች እና ተማሪዎች ብስክሌትን ዋነኛ መጓጓዣቸው አድርገው እንዲመርጡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል::

ኔዘርላንድስ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ከመጠቀም በተጨማሪ የአረንጓዴ መንገድ ንድፎችን በማውጣት መንገድን ከዓየር ንብረት ጋር በማሳለጥ ተሞክሮ የሚሆኑ ሥራዎች ባለቤት ናት::

ኔዘርላንድስ ፈጠራ የታከለባቸው እንደ «ውነርፍ» ያሉ መንገድን እንደ ሕዝብ መዋያ አድርጎ የመጠቀም ወይም መንገዶችን ለሽርሽር አመቺ በማድረግ ተዝናኖትን እንዲፈጥሩ ማስቻል ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ድንቅ የመንገድ መሠረተ ልማቶቿ ናቸው::

በተመሳሳይ ቻይናም በዓለማችን የመንገድ መሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በአጭር ጊዜ ረጅምና ሰፋፊ መንገዶችን በመገንባት ትታወቃለች:: ቻይና በዓለማችን 170 ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፍጥነት መንገድ በመገንባትም ቀዳሚዋ ሀገር ናት::

ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ብዙ መንገዶችን ለመገንባቷ የሀገሪቱ መንግሥት ጠንካራ የፋይናንስ ድጋፍ እና ለዘርፉ የምትጠቀማቸው ትላልቅ እና ዘመናዊ የግንባታ ማሽኖች ድርሻቸው የጎላ ነው::

የቻይና የመንገድ መሠረተ ልማቶች ከኢንዱስትሪ ዞኖች፣ ከወደቦች እና ከገበያ ማዕከላት ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው የመንገድ መሠረተ ልማቱ ለሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት አስተዋጽኦው የጎላ ነው:: የሰው ሠራሽ አስተውሎትን (የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን) ለትራፊክ ደህንነት መቆጣጠሪያነት ተግባራዊ ማድረጓም በመንገድ መሠረተ ልማቱ ዘርፍ ላሳየችው ዕመርታ ማሳያ ነው::

ስዊዘርላንድም መንገዶቿን በከፍተኛ ጥራት በመገንባት እና ለመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ የምትጠቀማቸውን ጥሬ ዕቃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች:: ሀገሪቱ የተራራ ላይ መንገዶችንና ረጃጅም ድልድዮችን በመገንባት ያላት ተሞክሮ ብዙ ሀገራትን የሚያስተምር ነው::

ስዊዘርላንድ «ጎት ሀርድ ቤዝ ተነል» የተባለው የዋሻ ውስጥ መንገዷ 57 ነጥብ ዘጠን ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን ይህም የዓለማችን ረጅሙ የዋሻ ውስጥ መንገድ ሆኖ ተመዝግቧል:: በርዝመቱ ብቻ ሳይሆን በጥራቱ ልዩ የሆነ የስዊዘርላንድ የዋሻ ውስጥ ዘመናዊ መንገድ ለሀገሪቱ የመንገድ መሠረተ ልማት ዝማኔ ማሳያ ሆኖ በብዙ ሀገሮች ዘንድ እንደ ተምሳሌት ይጠቀሳል::

የመረጃ ምንጫችንን (ወርልድ ትራንስፖርቴሽን ኢንጂነሪንግ)ን ዋቢ አድርገን ስለ መንገድ መሠረተ ልማት ያነሳናቸው ነጥቦች ሀገራችንን ጨምሮ ሀገራት በመንገድ ልማት የሚማሩባቸው ናቸው፤ በተለይ የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ ስለመሆኑ ማሳዎች ናቸው::

በተቋማት አለመቀናጀት መሠረተ ልማቶች ከመፍረሳቸው በተጨማሪ በነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታን ይፈጥራሉ፤ ለዚህ ደግሞ ሀገራችን ማሳያ ናት::

የጃፓን መንገዶች ከባቡር ሀዲድ እና ከሕዝብ ትራንስፖርት መስጫ መንገዶቻቸው ጋር ያላቸውን ጥምረት በተናጠል ስንመለከተው በኛም ሀገር የመንገድ መሠረተ ልማቶች ሲገነቡ ከጥራታቸው ባሻገር እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ ቴሌ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጋር ተናብበው መሥራት እንዳለባቸው እንማርበታለን::

በኛ ሀገር (አማራ ክልልን ጨምሮ) በቅርብ ገዜያት እየተገነቡ ያሉ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ከችግር የጸዱ ባለመሆናቸው የጃፓንን ተሞክሮ መውሰዱ ይጠቅመናል:: አንዱ ተቋም ሲገነባ ሌላው ማፍረስ የለበትም፤ ለዚህ መድኃኒቱ ደግሞ ተቀናጅቶ መሥራት ነው::

በቅርቡ በሀገራችን በስፋት በመሠራት ላይ ያሉት የኮሪደር ልማቶች የእግረኛ፣ የብስክሌት እና የተሽከርካሪ መንገዶችን የተለያዩ ከማድረግ አንጻር ጥሩ እመርታዎች የታየባቸው ናቸው:: በዚህ ላይ ኔዘርላንድስ ያሳየችውን እመርታ በሀገራችን የኮሪደር ልማቶች ላይ መተግበር ከቻልን ደግሞ የምናተርፈው ብዙ ይሆናል::

ለመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደ ቻይና መንግሥት በመንግሥት ደረጃ ጠንካራ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግና ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ማስቻልም ሀገራችንን ጨምሮ ብዙ ሀገራት ሊማሩበት የሚገባ ተግባር ነው::

የተለያየ መልክዓ ምድር ባለቤት የሆነችው ሀገራችን በተራሮች ላይ እና በተራሮች መሀል (እንደ ሊማሊሞ መንገድ ዓይነት) ለሚገነቡ መንገዶች የስዊዘርላንድን የተሳካ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ አርዓያ ማድረግ አዋጭነቱ ላቅ ያለ ነው፡

ስዊዘርላንድ የገነባቻቸውን የዋሻ ውስጥ መንገዶችም ተጨማሪ እንደ ደብረሲና ያሉ የዋሻ ውስጥ መንገዶችን ለመገንባት አስተማሪነታቸው ከፍተኛ ነው::

በአጠቃላይ የመንገድ መሠረተ ልማት ለአንድ ሀገር የሕዝብ ለሕዝብ መገናኛ አውታር ብቻ ሳይሆን የምጣኔ ሀብት መሠረት እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ማሳለጫ ነው:: በብዙ ያደጉ ሀገሮች መንገድ አሥተዳደራዊ ጥያቄ ሆኖ ካለመነሳቱም በተጨማሪ መንገዶቻቸው የምጣኔ ሀብታቸው ማስተሳሰሪያ ገመድ ሆኖ እያገለገላቸው  ነውና እኛስ? ብለን ራሳችንን መጠየቃችንም ግድ ይሆናል::

የሀገራቱን ተሞክሮ በአግባቡ ሰንዶ ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ ነዋሪው ለሚያነሳቸው አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል፤ ነዋሪውም ሙሉ ትኩረቱን ልማት ላይ ያደርጋል::

መረጃ

ጀርመን፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድስ፣ ቻይና እና ስዊዘርላንድ በመንገድ መሠረተ ልማት የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው ናቸው:: መሠረተ ልማቶቹ በመንገድ ደህንነት፣ በትራፊክ አሥተዳደር እና በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ናቸው::

ተቋማት የተናበቡ መሆናቸውም ለስኬታቸው ቁልፍ ድርሻ አለው:: ከዚህ ጋር በተገናኘ ታዲያ በእኘ ሀገር ላይ የመሠረተ ልማት ካለመሟላቱ ባለፈ ተቋማት ተናበው ሥራዎችን አይከውኑም፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ውስኑን መሠረተ ልማት ሲፈርስ ይስተዋላል:: ነገሩም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆናል::

በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱ ሀገራትን እንደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ተሞክሮውን መውሰዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኛል::

(እሱባለው ይርጋ)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here