“ሥራ ሳይንቁ፣ በታማኝነትና በቆጣቢነት ከሠሩ ስኬት አይቀርም”

0
362

አቶ ፈንታሁን ደምመላሽ ይባላሉ፤ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው በጠንካራ የሥራ ዲሲፕሊንና በቆጣቢነት አሁን ላሉበት ከፍተኛ የስኬት ማማ የደረሱ ብርቱ ሰው ናቸው። በላባቸውና በጥረታቸው ለብዙዎች ተምሳሌት መሆን የሚችሉ ሥራ ሳይንቁ በመስራት ጠንካራ የስራ ባህል የገነቡ ግለሰብ ናቸው።  ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን አጠቃላይ ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።

አቶ ፈንታሁን በመጀመሪያ ለቃለ-መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን። እስኪ ትውልድና የልጅነት እድገትዎን በአጭሩ ያስረዱን?

እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ! የተወለድኩት በደቡብ አቸፈር ወረዳ በ1966 ዓ.ም ነበር። አሁን 52 ዓመት ሞልቶኛል። የልጅነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት እዚያው በትውልድ መንደሬ ነበር። አባቴ ገና የአንድ ዓመት ጨቅላ እያለሁ ከዚህ ዓለም በመለየቱ በእናቴ እና እህቴ አማካኝነት ማደግ ነበረብኝ።

በልጅነትዎ ሕይወትን ለማሸነፍ ብዙ እንደለፉ ይነገራል፤ ያ ጊዜ እንዴት ነበር?

በልጅነቴ ሕይወትን ለማሸነፍ መስራት ነበረብኝ። የዘጠኝ ዓመት ሳለሁ በተወለድኩበት አካባቢ ከብት ለማገድ ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ።  መጀመሪያ በ33 ብር ደመወዝ ለአንድ ዓመት ሰራሁ፤ በቀጣዩ ዓመትም በአንድ ፍየል ደመወዝ ለአንድ ዓመት ሰራሁ። በሦስተኛው ዓመት በስምንት ቁና እህል እዚያው ተቀጥሬ ሰራሁ።

ወደ ቤተ-ክህነት ትምህርት የገቡት ከዚያ በኋላ ነው?

አዎ፣ ከዚህ በኋላ ነበር የቤተ ክህነት ትምህርት የገባሁት። በመጀመሪያ በመራዊ አካባቢ በመርጌታ ወርቄ አማካይነት ተማርኩ፤ ያኔ የአስራ ሁለት ዓመት ታዳጊ ነበርኩ። በመቀጠል በ13 ዓመቴ ምናዳ ማርያም ውስጥ ከመርጌታ ይባቤ ትምህርቴን ተከታተልኩ። በአስራ አራተኛ ዓመት እድሜዬ በቀድሞው የባህር ዳር አውራጃ በአቡነ በርናባስ እጅ ድቁና ተቀብዬ ከመራዊ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ስማድ በርሀ ማርያም በቅዳሴ ለሁለት ዓመታት አገለገልኩ።

ወደ ባህር ዳር ከተማ የመጡት በምን ሁኔታ ነበር? ከአክስትዎ ጋር የነበረዎት ቆይታስ?

አዎ! በቅዳሴ ለሁለት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ በልጅነት ልቤ ውስጥ የነበረውን ሰርቶ የመለወጥ ህልሜን ለማሳካት ቆርጨ ወደ ባህር ዳር መጣሁ። በባህር ዳር ከመጣሁ በኋላ ከአክስቴ ጋር ሆኜ መኖር ጀመርኩ። በዚህ አጋጣሚ ስራ የሚባልን ማንኛውንም ነገር ለመሞከር በመድፈር በዘበኝነት ተቀጥሬ ማታ ማታ ሆቴል እጠብቅ ነበር።  ይህ ብቻ አይደለም፤ ጥዋትና አመሻሽ ላይ የልብስ ቦንዳ የማውጣትና የማስገባት ሥራ እሰራ ነበር። ቀን ላይ ደግሞ ቋጠሮ በመሸከም ከአስር ሳንቲም ጀምሮ ገቢ አገኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ገንዘብ ማጠራቀም በመቻሌ በቅሎ ከነጋሬው መግዛት ቻልኩ።

ከዚያስ ሥራዎን እንዴት አስፋፉ?

ከጊዜ በኋላ ቦታ ቀይሬ ለመስራት በማሰብ ጋሪዬን እየነዳሁ ወደ ዱር ቤቴ ከተማ ሄድኩ። በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት ነበርኩ እና በዱር ቤቴ ከተማ በአምስት ብር ቤት በመከራየት የጋሪ ሥራውን ቀጥዬ ለሁለት ዓመታት ሰራሁ። በኋላ በ1500 ብር መኖሪያ ቤት እና በ500 ብር የእህል መጋዘን ገዝቼ እየኖርኩ እያለ በቅሎየ ባልታወቀ ምክንያት ሞተችብኝ። በወቅቱ ገዝቶ ለመተካት ትርፍ ገንዘብ ስላልነበረኝ ወደ መተማ ለሰሊጥ አጨዳ በቀን ሰራተኛነት ሄድኩ።

የመተማው ቆይታዎ ግን አስቸጋሪ እንደነበር ሰምተናል?

ሰሊጥ አጨዳ የሄድኩት ከአካባቢዬ ስድስት ጓደኞቼ ጋር ነበር። በዚያም በጉልበት ሰራተኝነት ተቀጥረን መስራታችንን ቀጠልን። ነገር ግን አካባቢው በርሃ በመሆኑ ወባና ሌላም ወረርሽኝ ስለሚከሰትበት እንታመም ነበር። ችግሩ በቀላሉ የምንወጣው አይነት አልነበረም እና አራቱ ጓደኞቼ እዚያው ሕይወታቸው አለፈ። ከዚያም በኋላ ትልቅ ወንድሜ ምትኩ ደመላሽ በወቅቱ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ቢሆንም ሁመራ ድረስ በመሄድ ወደ ዱር ቤቴ እንድመለስ አድርጓል። ይህ ለእኔ በሕይወት  የመኖር ሁለተኛ እድል የማግኘት ያህል ትልቅ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ በኋላ ሕይወት በአዲስ አበባ ይጀምራል።

ከዚያስ ወደ አዲስ አበባ እንዴት ሄዱ  በሕይወትዎስ ምን ተከናወነ?

አዲስ አበባ ሌላኛው ትልቅ ወንድሜ ስለነበር እርሱ ሊያስተምረኝ ወሰደኝ። ዘመናዊ ትምህርት ስላልነበረኝ ፈትነው አራተኛ ክፍል አስገቡኝ፤ ከወንድሜ ጋር ሆኜ እስከ 8ኛ ክፍል ተማርኩ። ከዚህ በኋላ ግን ወደ ውትድርና ገብቼ በሁርሶ የፓራ ኮማንዶ ስልጠና ወስጄ ተመረቅኩ። በወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ስለነበር አዲስ አበባ ከተማ የፌደራል ተቋማትን ለመጠበቅ ተመርጠን አዲስ አበባ ስንቀር ሌሎች ጓደኞቼ ወደ ኤርትራ ዘመቱ። በዚህ አጋጣሚ ትርፍ ጊዜየን እየተጠቀምኩ በመማር ከአንድ ዓመት በኋላ የተሽከርካሪ መንጃ ፈቃድ አወጣሁ። በውትድርና ሀገሬን በታማኝነት አገልግያለሁ ከዚህ በኋላ በኢኮኖሚ ራሴን የመለወጥ የልጅነት ውጥኔን ለማሳካት በግሌ ለመስራት መልቀቂያ አስገባሁ። ጥያቄየም ቀና ምላሽ በማግኘቱ መሳሪያየን አስረክቤ በክብር ተሰናበትኩ፤ እናም ወደ ዱር ቤቴ ተመለስኩ። የአጎቴን ሚኒ ባስ በ600 ብር ደመወዝ ተቀጥሬ ማሽከርከር ጀመርኩ።

እኔ በጣም ቆጣቢ ነበርኩ። እንደ ሌሎች ሆቴል ገብቼ አልመገብም ነበር፤ አበልና ደመወዜን በማጠራቀም በአንድ አመት ውስጥ ዘጠኝ ሺህ ብር አካባቢ አጠራቀምኩ። ከዚያም መንጃ ፍቃዴን ወደ ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ አሳደግኩት። በኋላም አይሱዙ መኪና እየነዳሁ ወደ መተማ ሰሊጥ መጫንና መነገድ ጀመርኩ።

ወደ ንግዱ ዓለም የገቡት በምን ያህል መነሻ ካፒታል ነው?

መተማ እየሰራሁ 18 ሺህ ብር ማጠራቀም ቻልኩ። ከሹፌርነቱ በተጨማሪ አብሬ በመነገድ 45 ሺህ ብር አፈራሁ።  ከትልቅ ወንድሜ ጋር በ85 ሺህ ብር ባህር ዳር ከተማ ላይ ቤት ገዛን። በቤቱ መያዣነት ሶስት መቶ ሺህ ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሬ የሕዝብ አውቶቡስ ገዛሁና በየወሩ 9ሺህ 471 ብር ከፍዬ ጨረስኩ። አውቶቡሱን በኮንትራት ካከራየሁ በኋላ አሁንም በቤቱ 1 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ብር ተበድሬ ተጨማሪ ቤት ገዛሁ፤ የእህል ወፍጮም ተከልኩ።

አሁን ላይ የደረሱበት የኑሮ ደረጃና የቤተሰብ ሕይወትዎ ምን ይመስላል?

በ2009 ዓ.ም ከወይዘሮ አበባ ይስማው ጋር ጋብቻ ፈጽመን ሁለት ልጆችን (አርሴማና ሀና ማርያምን) አፍርተናል። ባለቤቴ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ትሰራ ስለነበር ተጨማሪ የእህል ወፍጮዎችን ተክለን፣ ቤቶችንም እየገዛንና እየጠገንን በመሸጥ ስራችንን ቀጠልን። ከ2009 ዓ.ም በኋላ ያለ ምንም የባንክ ብድር እየሰራሁ ነው የምገኘው። ከመንግስት ምንም ዓይነት የመሥሪያ ቦታ አግኝቼ አላውቅም። ሁሉም የመጣው በጥረቴ ነው።

ወደፊትም መንግሥት ቦታ ቢያመቻችልኝ ትልቅ ፋብሪካ ተክየ ሀገሬን እና ወገኔን ለመጥቀም ብርቱ ሀሳብ አለኝ፣ ከፈጣሪ ጋር።

እርስዎ ለማኅበረሰቡ የሚያደርጉት ድጋፍም በሰፊው ይነሳል፤ እስኪ ስለ ማኅበራዊ ኃላፊነትዎ ጥቂት ይበሉን?

ለብዙ ሰዎች ብድር ያለ ወለድ በማበደር እንዲለወጡ አስተዋጽኦ አድርጌአለሁ። ለሦስት ወንድሞቼ እያንዳንዳቸው የመኪና ስጦታ ሰጥቻለሁ። መንገድ በማሰራት፣ ለጤና መድን መክፈል፣ ለነዳያን ምግብ ማጋራትና ቤተክርስቲያን ማሰራት (ዱር ቤቴ ገብርኤልን) የመሳሰሉ ሥራዎችን ሰርቻለሁ። በባህር ዳር ያሉ ቤቶቼን ሳከራይም ለብዙ ዓመት የኪራይ ጭማሪ አላደረግኩም።

ለወጣቱ ምን ምክር ይለግሳሉ?

ከዚህ ደረጃ ለመድረስ ምንም ዓይነት ሱስ የለብኝም። ዋናው ነገር በቁጠባና በሥራ ማመን እንደሆነ እገልጻለሁ። ሁሉንም ሥራዎች ስሰራ እንደ አንድ ባለሙያ ወይም የቀን ሠራተኛ ሆኜ በመሥራት እታወቃለሁ። እናም ወጣቶች ሥራን ሳይንቁ፣ በታማኝነት እና በቆጣቢነት ከሰሩ ስኬት አይቀርም።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here