ምርጫ ሥልጣን በመሣሪያ ሳይሆን በድምፅ መስጫ ወረቀት ብቻ እንዲሸጋገር በማድረግ ሀገርን ከትርምስና ከጦርነት የሚያድን፣ ዴሞክራሲን የሚያሰፍን፣ ልማትን የሚያፋጥን ትልቅ የፖለቲካ ተግባር ነው።
በርካታ ሀገራት በልማት እንዲሁም በዕድገት ጎዳና ለመራመድ፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ፣ ሀገራቸውን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሸጋገር ኃያል ለመባል የበቁት ስኬታማ ምርጫን በማከናወን ነው::
ስኬታማ ምርጫን በማከናወን ለለውጥ ከበቁት ሀገራት ደቡብ አፍሪካ በአብነት ትጠቀሳለች። ደቡብ አፍሪካ ለብዙ ዓመታት በዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓትና በከፍተኛ ግጭት ውስጥ ኖራለች። ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1994 የተደረገው የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ እንደቀየረው የደቡብ አፍሪካ የታሪክ ትምህርትና ምርምር ተቋም ‘ሳውዝ አፍሪካ ሂስትሪ ኦንላይን’ በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ ይጠቁማል::
የደቡብ አፍሪካ ምርጫ የነጮች የበላይነት አብቅቶ ሁሉም ዜጋ እኩል መብት እንዲኖረው፤ ሀገሪቱ ወደለየለት የርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ አድርጓል::
ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከተካሄደ ታሪካዊ ቁስሎችን ለመፈወስ፣ አዲስ ሀገራዊ ስምምነት ለመፍጠርና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሁነኛ መሣሪያ ነው የሚባለውም ከዚህ የተነሳ ነው::
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሲሆን ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ ዕምነት ይኖራቸዋል፤ ዜጎች በመንግሥታቸው ላይ እምነት ሲኖራቸው ደግሞ መንግሥት በሚያደርጋቸው ማናቸውም የለውጥ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ:: ሕዝብ ለለውጥ ከሚተጋ መንግሥት ጎን ሲሰለፍ ደግሞ ልማት ይፋጠናል:: ከዚህ አንጻር ሲታይ ምርጫ ላንዲት ሀገር ልማት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው::
ከዚህ በመነሳትም ሀገራት ለምርጫ የሚሰጡት ትኩረት ከፍ ያለ ነው:: ሀገራችን ኢትዮጵያም ለምርጫ የምትሰጠው ቦታ ከፍ ያለ መሆኑን ያለፉት ምርጫዎች ማሳያዎች ናቸው:: ኢትዮጵያ መደበኛ ምርጫ ማካሄድ የጀመረችው ከ31 ዓመታት በፊት እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል::
በያዝነው ዓመትም ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ከቦርዱ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል:: መረጃዉ እንደሚጠቁመው እስካሁን 23 ሀገር አቀፍና 44 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበዋል::
ምርጫ ቦርድም ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከማድረግ ጀምሮ ዜጎች በዕውቀት ላይ ተመሥርተው ድምጻቸውን እንዲሰጡ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ግንዛቤ ለመፍጠር ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል:: በተመሳሳይ በተዋረድ አስፈላጊ ጽ/ቤቶችን መክፈቱንም ቦርዱ አስታውቋል::
የፖለቲካ ፓርቲዎችም የምርጫ ቅስቀሳ፣ የመራጮች ምዝገባና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ:: በተለያዩ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎችም ለጥያቄያችን ምላሽ ይሰጠናል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ናቸው::
ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ እስካሁን የተደረጉ ጥረቶች እንዲሁም የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል::
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ከካርድ እንጂ ከጠብመንጃ የሚቀዳ አለመሆኑን ተገንዝበው ለሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን መሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል::
ዕድሜው ለምርጫ የደረሰ ሁሉ ድምጹ ዋጋ እንዳላት በመገንዘብ ለመምረጥ መመዝገብና የምርጫ ካርድ ማውጣት ይጠበቅበታል:: የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሀሰተኛ መረጃዎች መጠንቀቅና እውነተኛ መረጃን በመያዝ ለምርጫዉ ስኬታማነት የሚደረጉ ጥረቶችን አጠናክሮ መቀጠል ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው::
በኲር የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


