የሰው ልጅ በምድር ላይ በሚያደርገው የሕይወት ጉዞ ውስጥ ያልታሰቡ የጤና ፈተናዎች ድንገት ብቅ ይላሉ። አንዳንዶቹ ፈተናዎች በአካል ላይ ህመም ከማስከተል አልፈው በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ሥም፣ ክብር እና ማህበራዊ መስተጋብር የሚፈትኑ ናቸው። ለዘመናት በተሳሳተ ትርክት ሰዎችን ለከፍተኛ ጭንቀት፣ መገለል ሲዳርግ የኖረው የስጋ ደዌ በሽታ ከእነዚህ ከባድ ፈተናዎች ቀዳሚው ነው።
ይህን አሰቃቂ ማህበራዊ መገለል እና አካላዊ ህመም በጽናት ተጋፍጠው ካሸነፉ ብርቱ ሰዎች መካከል አቶ እንዳለው ሙሉዓለም አንዱ ናቸው። ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ እንዳለው በሰውነታቸው ላይ የተለየ ነገር እንዳለ ያስተዋሉት ድንገት ነበር። አጋጣሚውንም እንዲህ ያስታውሱታል፤ “በጀርባዬ ቀላ ያለ… ጨረቃ የመሰለ ነገር ወጣ” በማለት።
በሽታው በሰውነታቸው ላይ እየበረታ ሲሄድ እና የነርቭ ጉዳት በማድረስ እጅ እና እግራቸውን መጉዳት ሲጀምር የስጋ ደዌ መሆኑ እንደ ተረጋገጠወዲያውኑም ህክምና እንዲጀምሩ መደረጋቸውን አስታውሰዋል። ዛሬ ላይ አቶ እንዳለው በሽታውን ሙሉ በሙሉ አሸንፈዋል፤ ይሁን እንጂ ህክምናውን ዘግይተው በመጀመራቸው ምክንያት በእጅና እግራቸው ላይ ያስከተለው ጠባሳ እና ህመም አሁንም አልፎ አልፎ ይሰማቸዋል።
በሽታው እንደ እርግማን፣ የእርኩስ መንፈስ ቁራኛ እና በዘር የሚተላለፍ ተደርጎ ስለሚታሰብ ታማሚዎች ከማህበረሰቡ ይገለላሉ። አቶ እንዳለው ይህን ድቅድቅ ጨለማ እና የብቸኝነት ጊዜ “በወቅቱ በጣም ችግር ነበር። ጋብቻ ሁሉ ተከልክሎ ነበር፤ አብሮ መጫወትም የለም ነበር፤ ከማህበራዊ ሕይወት መገለልም ነበር” በማለት ያስታውሱታል።
በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የቲቢ፣ የስጋ ደዌ እና ሌሎች የሳንባ መከላከል እና መቆጣጠር ባለሙያ ሲስተር አበራሽ አቤ የስጋ ደዌ በሽታ ዛሬም በአማራ ክልል የበርካቶችን ሕይወት በጸጥታ እየፈተነ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ የስጋ ደዌ ጫና ካለባቸው 23 ሀገራት አንዷ ስትሆን በዓመትም ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ ታማሚዎች ሪፖርት ከሚያደርጉባቸው ሀገሮች ተርታ ትመደባለች። በአፍሪካም ከዛምቢያ እና ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደ ምትገኝ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በሀገር ደረጃ ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ ከፍተኛ የስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂ ያለበት አማራ ክልል ነው ተብሏል። ይሁን እንጂ ባለፉት ዐስርት ዓመታት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ለውጦች መጥተዋል። በ1983 ዓ.ም 19 ነጥብ ስምንት የነበረው የስርጭት ምጣኔ አሁን እንደ ሀገር ወደ ዜሮ ነጥብ 28 ወርዷል። “በአማራ ክልል ደግሞ በ2017 ዓ.ም በወጣው መረጃ ዜሮ ነጥብ 46 የስርጭት ምጣኔ እንደ ነበር ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
ምንም እንኳን የስርጭት ምጣኔው አነስተኛ ቢሆንም በአማራ ክልል አሁንም በዓመት ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ ታማሚዎች እንደሚገኙ የጠቆሙት ሲስተር አበራሽ፤ በሽታው የአካል ጉዳት ስለሚያስከትል ቀላል የሚባል የጤና ስጋት እንዳልሆነም አስረድተዋል።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ የስጋ ደዌ የእርግማን ወይም የሀጢያት ውጤት ሳይሆን ልክ እንደማንኛውም በሽታ በባክቴሪያ የሚመጣ ነው። በሽታው በዐይን በማይታይ ተህዋሲያን (ባክቴሪያ) አማካኝነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው። ይሁን እንጂ በሽታው እንደሌሎች ተላላፊ በሽታዎች አጣዳፊ አይደለም፤ ቀስ በቀስ የሰውነትን ክፍሎች የሚያጠቃ ሲሆን ቶሎ ህክምና ከተጀመረ ግን ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ ወዲያውኑ ያቆማል።
በሽታዉ በአብዛኛዉን ጊዜ የቆዳን፣ የነርቭ ህዋሳትን እና ዐይንን የሚያጠቃ ሲሆን በፍጥነት ሕክምና ካላገኘ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ያስከትላል። በህሙማኑ እና በቤተሰቡ አባላት ላይም ማህበራዊ እና ሥነልቦናዊ ቀውሶችን ሊያስከትል ይችላል። በሽታዉ ፆታን የማይለይ እና በየትኛዉም የእድሜ ክልል የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያጠቃል ብለዋል ባለሙያዋ። ድህነት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና በአንድ ቤት ዉስጥ ተፋፍጎ መኖር ለስጋ ደዌ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጋልም ነው የተባለው።
የስጋ ደዌ በሽታ በትንፋሽ አማካኝነት የሚተላለፍ ሲሆን ሕመምተኛዉ በሚስልበት እና በሚያስነጥስበት ወቅት የበሽታዉን አምጪ ህዋስ ወደ ከባቢ አየር ይሰራጫል፤ ወደ ጤነኛ ሰዉም በአፍንጫዉ በኩል ወደ ሰዉነቱ ይገባል። ከዚያ በኋላም ወደ ሙሉ የሰዉነት ክፍሉ ይሰራጫል።
አንድ ሰው በሽታው እንዳለበት ከሚያውቅባቸው ዋና ዋና ምልክቶች መካከል በቆዳ ላይ ነጣ ወይም ቀላ ያሉ ምልክቶች መታየት ነው፤ በነዚህ የቆዳ ምልክቶች ላይ ምንም አይነት የህመም ስሜት (ማቃጠልም ሆነ ማሳከክ) አለመኖር፣ የእጅ እና የእግር መደንዘዝ ወይም የነርቮች ማበጥ፣ የዐይን ቆብ መዛል እና ስሜት አልባ የሆኑ ቁስሎች መፈጠር ናቸው። እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ቶሎ ብሎ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ ሀኪም ማማከር ያስፈልጋል። ምልክቶቹ ገና ቆዳ ላይ ለውጥ እንደታየ ወደ ጤና ተቋም ከሄዱ ምንም አይነት የአካል ጉዳት ሳይደርስ ሙሉ በሙሉ መዳን እንደ ሚቻል ባለሙያዋ አስገንዝበዋል።
አቶ እንዳለው ሙሉዓለም ዛሬ አካላዊ ህመማቸውን እና ማህበራዊ መገለላቸውን አሸንፈው የራሳቸውን ሕይወት በነጻነት ከመምራት ባለፈ ለማህበረሰባቸው ትልቅ ባለውለታ እና የለውጥ አምባሳደር ሆነዋል። በእሳቸው የደረሰው ስቃይ በሌሎች ላይ እንዳይደገም በሽታውን ደብቀው በየቤቱ የሚሰቃዩትን ወገኖች ፈልጎ በማውጣት ወደ ህክምና ቦታ እየወሰዱ መሆናቸውን ነግረውናል።
“እኔን እዩ… ለምን ትሸማቀቃላችሁ! እያልኩኝ በየቤቱ፣ በየሰንበቴው…ከሌሎች ጋር እየሄድሁ እያሳከምን ነው። እንዲህ አይነት አካል ጉዳት ያለውን ሰው አምጡልን፣ ሀኪም ይዘን ቢሮ ድረስ እንመጣለን እያልኩ እቀሰቅሳለሁ” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ የማያቋርጥ ቅስቀሳቸው ፍሬ አፍርቶ ህሙማን “አይ ይሄማ የስጋ ደዌ ነው” ብለው በመጠራጠር ምርመራ ለማድረግ ወደ ጤና ተቋም በራሳቸው ፍቃድ መምጣት ጀምረዋል። ድሮ ድሮ በሽታው አለበት የተባለን ሰው በባህላዊ መንገድ በስለት ነገር ቆዳውን በመግፈፍ እና በእሳት በማቃጠል የሚደረገው አሰቃቂ ድርጊት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ መቆሙን አቶ እንዳለው ይመሰክራሉ።
የበሽታው ምልክት የታየባቸው የማህበረሰብ ክፍሎችም በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት በመምጣት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። ህክምናው እስከ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ድረስ በነጻ የሚሰጥ፣ መድኃኒቱም ያለምንም ክፍያ የሚታደል መሆኑ ለማህበረሰቡ ትልቅ የመዳን ተስፋ አለው። ከህክምናው ጎን ለጎንም በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን መገለል ለማስቀረት ታማሚዎች ከእድር፣ ከእቁብ እና ከሌሎች ማህበራዊ ተሳትፎዎች እንዳይገለሉ ሰፊ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ንጹህ ሽፈራው ተናግረዋል።
በበሽታው ተጠቂ የሆኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች በማህበር ተደራጅተው በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ እየተደረገም ነው። አጋር ድርጅቶች በሽታውን ለመከላከል እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ በመውረድ የግብዓት እና የበጀት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ንጹህ ሽፈራው አስገንዝበዋል። “እስከታች ድረስ አደረጃጀቶች አሉ፤ ከማንኛውም ማህበረሰብ ይልቅ በዚህ አደረጃጀት ውስጥ የታቀፉ አባላት አሉ፤ ከአባላት ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለይተው ለእኛ በማሳወቅ ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳሉ” በማለትም በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የአባላት ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል::
የስጋ ደዌ ሕሙማን ፈጥነው ህክምናቸውን እንዲያገኙ እና በየትኛውም የጤና ጣቢያ አስፈላጊው ግብዓት እንዳይጓደልባቸው ከጤና ተቋማት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ቢሯቸው የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም ወ/ሮ ንጹህ ሽፈራው ተናግረዋል። ከስጋ ደዌ ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ታማሚዎችን ከማግለል ይልቅ በፍቅር ወደ ህክምና በማምጣት ሁሉም የድርሻውን መወጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ምክትል ኃላፊዋ አስገንዝበዋል::
እ.አ.አ በ2030 በሽታውን ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት እቅድ ተቀምጧል። ይሄንን ለማሳካት ከአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም 34 ከሚሆኑ የህሙማን ማህበራት ጋር በጋራ እየተሠራ ነው።
ጤና አዳም
ለምጽ (Vitiligo) እና ስጋ ደዌ ምንም አይነት ሳይንሳዊ ግንኙነት የሌላቸው ፍጹም የተለያዩ በሽታዎች ናቸው።
የሚያመሳስላቸው፡-ሁለቱም በቆዳ ላይ የቀለም ለውጥ (ነጣ ወይም ቀላ ያለ ምልክት) ያመጣሉ። ሁለቱም በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የስነ ልቦና እና የማህበራዊ መገለል (Stigma) ጫና ያደርሳሉ።
ልዩነታቸው፡-የስጋ ደዌ በባክቴሪያ የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ለምጽ (Vitiligo) ግን የሰውነት በሽታ ተከላካይ ህዋሳት ለቆዳ ቀለም የሚሰጠውን ሴል በስህተት ሲያጠቁት የሚመጣ ነው። በፍጹም ከሰው ወደ ሰውም አይተላለፍም። የስጋ ደዌ ትልቁ መለያ ቆዳው ላይ የነርቭ መደንዘዝ ማምጣቱ ነው። ለምጽ ባለበት ቆዳ ላይ ግን ልክ እንደ ጤናማው ቆዳ ህመም፣ ሙቀትም ሆነ ቅዝቃዜ በደንብ ይሰማል።የስጋ ደዌ ቶሎ ካልታከመ ነርቮችን በመጉዳት የእጅ እና የእግር መቆረጥን(መጉደልን) ያመጣል። ለምጽ ግን ከቆዳ ቀለም መቀየር ውጪ ምንም አይነት የአካል መጉደልን አያስከትልም።
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


