የኢትዮጵያውያት ገድል – በዓድዋ

0
183

እ.አ.አ በ1896 ዓ.ም በተደረገው የዓድዋ ጦርነት ላይ ሴቶች ወሳኝ እና ዘርፈ ብዙ ሚና ተጫውተዋል:: ኢትዮጵያ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ላይ ድል እንድትቀዳጅ በወታደራዊ ትጥቅ፣ ስንቅ እና የመጓጓዣ አልግሎት(በሎጅስቲክስ)፣ በሕክምና እና በቀጥታ በጦርነቱ በመሳተፍ ውጤት አስመዝግበዋል:: በእቴጌ ጣይቱ ብጡል መሪነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ከ100ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወታደሮች  ከመመገብ ጀምሮ ለወገንም ሆነ ለጠላት ጦር ቁስለኞች ሕክምና ሰጥተዋል::

በእቴጌ ጣይቱ ብጡል በሚመራ የጦር ሰራዊት አዛዥ ሴቶች ጦርነቱን በመምራት እና ግንባር ተሰልፈው ጠላትን በመምራት  ሀገራቸውን ከጠላት ተከላክለዋል:: በጦርነቱ አንዳንድ ግምቶች ከ20ሺህ እስከ 30ሺህ የሚደርሱ ሴቶች በዘመቻው እንደተሳተፉ ይጠቁማሉ::

በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያዊያን ሴቶች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ነበሩ:: እቴጌ ጣይቱ ቆራጥ ዲፕሎማት ሴት ብቻ ሳይሆኑ በጦርነት ጥበብ የተካኑ ብልሃተኛ አዛዥ፣ ታክቲክን የተላበሱ የላቀ ብቃት ያላቸው ነበሩ:: እቴጌ ጣይቱ የፖለቲካ ሰው ብቻ ሳይሆኑ ወሳኝ ወታደራዊ መሪም ነበሩ::

እቴጌይቱ በጦርነቱ ውስጥ ለወታደሩ ስንቅ፣ ትጥቅ እና መጓጓዣ በማቅረብ እና በማደራጀት በጥልቅ ተሳትፈዋል:: ከጣልያን ጋር የሚቆሙ ተፎካካሪ ኀይሎችን በማሰባሰብም ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራቸው::

እቴጌ ጣይቱ በጦርነቱ ወቅት ከፈጸሙት ጉልህ ተግባር አንዱ የጣሊያን ጦር ኀይሉን በሰሜን ኢትዮጵያ በምትገኘው መቀሌ ከተማ ቢሰበስብም   ቅኝ ገዥዎች ሽንፈት እንዲከናነብ ያደረጉበት እንከን የለሽ ስልታዊ አመራር ነው::: በዚህም አምስት ሺህ እግረኛ እና 600 ፈረሰኞችን ያቀፈ የራሳቸውን ጦር አደራጅተው የጣሊያን ጦር የሚመካበትን የውኃ ምንጭ የመያዝ እና የመጠበቅ ተልዕኮ በመስጠት በውኃ አቅርቦቱ ላይ በጣም ጥገኛ የነበሩትን የጣሊያን ተዋጊዎች ማዳከም ችለዋል:: ይህም የጠላትን ውጤታማ በሆነ መንገድ የመንቀሳቀስ ችሎታን በእጅጉ አስተጓጉሏል:: በዚህም የእቴጌዋ  አርቆ አስተዋይነት የተረጋገጠበት ነበር:: ይህ ስልታቸው ጣሊያኖችን በማዳከም ረገድ ለአድዋ ድል ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት አስችሏቸዋል::

በዓድዋ ጦርነት የሴቶች ተሳትፎ ዘርፈ ብዙ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በርካታ ሴቶች በግንባር ቀደምትነት ተዋግተው ኢትዮጵያን በመከላከል ረገድ ንቁ ሚና ተጫውተዋል:: እነዚህ ሴቶች ብዙውን ጊዜ “ተፋላሚ ሴቶች” እየተባሉ ነበር የሚጠሩት::

ሴቶች በዓድዋ ጦርነት ወቅት የነበራቸው ሚና በአግባቡ እንዳልተነገረ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ:: ሆኖም በዓድዋ ጦርነት እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሴቶች በአዋጊነት ተሳትፈዋል፤ በተለይም ወንዶቹን በሽለላ እና ቀረርቶ በማበረታታት የትግል ወኔያቸውን ከፍ አድርገዋል:: መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዝዘው አዋግተዋል፤ ቀን ከውጊያ ማታ ከስንቅ ዝግጅት ሳይነጠሉም ረጅሙን የውጊያ ወራት በጀግንነት መወጣታቸውን ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በጽሑፉ  አስፍሯል::

ለጦርነቱ መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ውል ስምምነት በጣሊያንኛ የተጻፈውን  ቀድመው የተረዱት እና በባለቤታቸው በአፄ ምኒልክ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳደሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ነበሩ:: ይህ ብቻ አልነበርም እቴጌዋ የፈጸሙት፤- ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ የተባለው ታሪክ የሚዘክር መጽሐፍ ደራሲ ብሩክ መኮንን በጽሑፉ እንዳሰፈረው  ምኒልክ ከጣሊያን ጋር ስለሚያደርጉት ጦርነት ከመሳፍንቱ እና ከጦር አዛዦቻቸው ጋር በቤተ መንግሥታቸው እንዴት እንደሚያካሂዱ ሲመካከሩ እቴጌ ጣይቱ ከአጎታቸው  ከራስ ዳርጌ ጋር ቤተ መንግሥቱንና ከተማውን  እንዲጠብቁ ሀሳብ ቀርቦ ነበር:: ይሁንና እቴጌ ጣይቱ በእልህ እና በቁጣ “እንዴት ተደርጎ እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያን የጠላት ጦር ገጥሟት ባላቤቴ ንጉሠ ነገሥቱ ለመፋለም በጠላት ፊት ተሰልፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ መከራ እና እልቂት በገጠመበት ወቅት…በደኅንነት መቆየት የማይሞከር ነው! ለዚህ ደግሞ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌ እቀርባለሁ! በማለት መቃወማቸውን መጽሐፉ ላይ ሰፍሮ ይገኛል::

ዓድዋ የአንዲት ወይም የሁለት መሪዎች ታሪክ ብቻ እንዳልነበር ልብ ሊባል ይገባል:: የሺዎች ሴቶች የጉልበት፣ የድፍረት እና የመንፈስ ተሳትፎ ያለበት የሕዝብ ትግል ነበር:: በጦርነቱ ሴቶች ስንቅ ከማዘጋጀት፣ ቁስለኛን ከመንከባከብ ባለፈ በቀጥታ መዋጋታቸው መዘንጋት የለበትም:: ለአብነትም በጦርነቱ ወቅት ከሴት መሪዎች አንዷ የሆኑት የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሚስት ከባለቤታቸው ጋር እንደተዋጉ ይነገራል::

ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ በዓድዋ ጦርነት ወታደሮቹን የመሩት ታዋቂ የኢትዮጵያ ጦር መሪ ነበሩ። ባለቤታቸው በወቅቱ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ሀገራቸውን መጠበቅ አስቸኳይ እንደሆነ ተሰምቷቸው ወደ ተዋጊዎች ጎራ ገብተው ትጥቅ አንስተዋል::

በተጨማሪም ስማቸው በታሪክ ያልተመዘገበ በርካታ ሴቶች አንዳንዶቹ ከባሎቻቸው ጋር  በቀጥታ ተዋግተዋል፤  ሌሎች በራሳቸው ውሳኔ ጦርነቱን ተቀላቅለዋል::

ዓድዋ የኢትዮጵያ የነፃነት ምልክት ብቻ አይደለም፤ የሴቶች ተሳትፎ የታየበት ታሪክ ነው:: ከእቴጌ ጣይቱ ጀምሮ ስማቸው ያልተመዘገቡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተሳትፈዋል:: ድሉም የሁሉ ነበር::

ዛሬ ዓድዋን ስናስብ በጦር መሪዎች ብቻ አንቆምም፤ ከድል ጀርባ ያሉ የሴቶች ድፍረት ይዘከራል:: እነሱ በታሪክ ውስጥ የተሰወሩ ቢሆኑም በዓድዋ ድል ውስጥ ያላቸው ሚና ዘላቂ ነው::

“ዓድዋ  የጦርነት ድል ብቻ አይደለም” ሲባል  ሴቶች በሀገር ጉዳይ  እኩል ሊሳተፉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ታሪካዊ ምሳሌም ነው ለማለት ነው:: የኢትዮጵያ ሴቶች የክብር ታሪክም ነው::

ማን ናት

እቴጌ ጣይቱ ብጡል

 

‘‘ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ’’ በሚል ቅፅል ሥም የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብዳር በነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም በድሮው አጠራር በበጌምድር ደብረታቦር ከተማ ተወለዱ፡፡

በልጅነት ዘመናቸው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሃይማኖት ትምህርትን በታላላቅ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ የተማሩባቸውም መጻሕፍት የተጻፉት በግእዝ ቋንቋ ስለነበር ቋንቋውን አጣርተው ያውቁ ነበር፡፡

ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጋር ሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተጋብተዋል፡፡

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፏቸው የገነነውና በሀገር አስተዳደርም ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25  ቀን 1981 ዓ.ም በውጫሌ ላይ ከጣሊያን ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በጣሊያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል የተቀመጠው ጽሑፍ ነው፡፡

ምንጭ፡-  *የጳውሎስ ኞኞ ፡-አጼ ምኒልክ ከሚለው መጽሐፍ

*የባሕሩ ዘውዴ ፡-የኢትዮጵያ ታሪክ

*የብሩክ መኮንን ተክለየስ ፡- እቴጌ ጣይቱ ብርሐን ዘኢትዮጵያ

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here