የተሰጠኝ ሕይዎት ዛሬ በነጻነት ፣
ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት፡፡
ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር፣
ትናገር አድዋ ትናገር ሀገሬ ፣
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ”፡፡
ድምጸ መረዋዋ እጅጋየሁ ሽባባሁ በስንኟ እንደገለጸችው ዛሬ ኢትዮጵያዊያን በሄዱበት የባዕድ ሀገር ሁሉ አንገታቸውን ቀና አድርገው ደረታቸውን ነፋ አድርገው እንዲሄዱ ካስቻላቸው ምክንያት መካከል የአድዋ ድል አንዱ ነው፡፡
በጎርጎሮሳዊያኑ መጋቢት 1፣ 1896 የተካሄደው የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ እና በዓለም ታሪክ ውስጥ ካሉት እጅግ አስፈላጊ ክስተቶች አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ ጣሊያንን አሸንፋ ነፃነቷን ከቅኝ ግዛት ጠብቃለች፡፡ ድሉ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የነፃነት እና የመቃወም ዓለም አቀፍ ምልክትም ሆነ፡፡ ብዙ ዓለም አቀፍ ምሁራን አድዋ ልዩ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም አፍሪካዊያን ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር የአውሮፓ ቅኝ ግዛት ኃይልን ድል ያደረጉት፡፡
ታሪካዊው ዳራ
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የአውሮፓ ሀገራት የአፍሪካን ግዛቶች በኃይል በመቀራመት ያስተዳድሩ ነበር፡፡ እ.አ.አ. በ 1870 ከአፍሪካ 10 በመቶው ብቻ በአውሮፓ ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ማለትም እ.አ.አ. በ 1914 ወደ 90 በመቶ የሚጠጋው የአህጉሪቱ ክፍል በቅኝ ግዛት ተያዘ፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ እና ላይቤሪያ ብቻ ነበሩ ነፃነታቸውን ጠብቀው የቆዩት፡፡
አውሮፓዊያን አፍሪካን ለመቀራመት ያነሳሳቸው በርካታ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነሱም የኢኮኖሚ ፍላጎቶች፣ በአውሮፓ እየተስፋፋ ያለው ኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ እንደ ጎማ፣ የዘንባባ ዘይት፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጥጥ እና ማዕድናት ያሉ የጥሬ ዕቃዎችን ፍላጎት በመፍጠሩ ነው፡፡ አፍሪካም እንደ ሰፊ የጥሬ ሀብት መገኛ እና ለአውሮፓ የተመረቱ እቃዎች መዳረሻ ተደርጋ መታየቷ ፊታቸውን ወደ አህጉሪቱ እንዲያዞሩ አደረገ፡፡
የፖለቲካ ፉክክር የአውሮፓ ኃያላን ግዛቶቻቸውን ለማስፋት እና እንደ ግብፅ ስዊዝ ቦይ ያሉ ቁልፍ ግዛቶችን ለማስጠበቅ በማለም ለክብር እና ለስልታዊ ጥቅም አወዳደራቸው፡፡ በአውሮፓዊያን ያለው የቴክኖሎጂ፣የሕክምና እና የትራንስፖርት እድገቶች የእንፋሎት መርከቦች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ ኮሙኒኬሽን (ቴሌግራፍ) እና በመድኃኒት የመጡ እድገቶች አውሮፓዊያን ወደ አፍሪካ የውስጥ ክፍል እንዲገቡ ቀላል ሆነላቸው፡፡ እንደ ዴቪድ ሊቪንግስተን እና ሄንሪ ሞርተን ስታንሊ ባሉ አሳሾች የተደረጉ ጉዞዎችም የአፍሪካን የውስጥ ክፍል ካርታ በማዘጋጀት ሀብቶቿን በመግለጥ የአውሮፓን የይገባኛል ጥያቄ እንዲገፉበት በር ከፍቷል፡፡
በኋላም ፍላጎታቸው ገፍቶ በመሄዱ እና በማየሉ የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት ቅኝ ግዛትን ለማስፋፋት እና አፍሪካን ለመቀራመት እ.አ.አ በ1884 እና በ1885 በበርሊን ኮንፈረንስ አካሄዱ፡፡ በስብሰባቸውም የትኛው የአፍሪካ ሀገር ለማን እንደሚገባ ተከፋፈሉ፤ ተስማሙ፡፡ ሀገራቱም 14 ሲሆኑ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ፖርቹጋል፣ ስፔን እና ቤልጂየም ደግሞ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ ጣሊያን እ.አ.አ. ከ1882 ጀምሮ የአሰብን ወደብ በቅኝ ግዛት ይዞታዋ አድርጋ ነበር፡፡ በበርሊን ኮንፈረንስም የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ኃያላን ሀገራት ጣሊያን ኢትዮጵያን የወደፊት ቅኝ ግዛቷ አድርጋ ልትወስድ እንደምትችል ተስማሙ፡፡ በዚህ አቅጣጫ ኢትዮጵያም በጣሊያን የቅኝ ግዛት እቅድ ውስጥ ተካተተች፡፡
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የተፈራረሙት የውጫሌ ስምምነት ነበር ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት የሆነው፡፡ ስምምነቱ በአማርኛ እና በጣሊያንኛ የተጻፈ ሲሆን የጣሊያንኛው ትርጉም ኢትዮጵያ ማንኛውንም ከውጭ ሀገራት ጋር የምታደርገው ግንኙነት ጣሊያን ሳታውቀው እና ሳትፈቅድ እንደማይካሄድ የሚያትት በመሆኑ ኢትዮጵያዊያንን አበሳጭቶ ለጦርነት አነሳስቷል፡፡ በተለይም የአጼ ምኒልክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ለባለቤታቸው ውሉን በማስረዳት በኩል ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የታሪክ ድርሳናት ያስነብባሉ፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው ጦርነትም በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የቅኝ ግዛት እንዳበቃ ማሳያ የሆነው የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ የታሪክ ማዕድ አይደለም፤ በዓለም ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለየ ስፍራን ይይዛል፡፡ በአጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ሠራዊት የጣሊያንን ጦር ማሸነፍ በአፍሪካ እየተካሄደ ያለውን ቅኝ ገዢዎች መስፋትን የገታ ነበር፡፡
የአድዋ ድል ምዕራባዊያን ለካ መሸነፍም አለ ብለው እንዲያስቡ ያደረገ ነው፡፡ ሁሌ ፌሽታ ሁሌ ስኬት እንደሌለ ማሳያም ነበር፡፡ ይህ ክስተት በምዕራባዊያን ዓለም ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን አስከትሏል፡፡ አድዋ በምዕራባዊያን እይታ ሦስት መልክ አለው፡፡ አንደኛው በአውሮፓ ውስጥ ድንጋጤ ሲፈጥር ሁለተኛው በጣሊያን ብሔራዊ ውርደት ማስከተሉ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት ተደርጎ መቆጠሩ ነው፡፡ አድዋ የአንድ ሀገር ድል ብቻ አይደለም፤ የኮሎኒያሊዝም ታሪክን ያስተካከለ ክስተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክብር ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እምነት ምልክት ሆኖም ቆይቷል፡፡
እንግሊዛዊው የአፍሪካ ዲያስፖራ ታሪክ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ሃኪም አዲ እንደጻፉት አድዋ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የነፃነት ምልክት አድርጓታል፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ አፍሪካዊያን አውሮፓዊያን ሊሸነፉ እንደሚችሉ ኢትዮጵያን ማረጋገጫ አድርገው እንደሚመለከቷት እና ድሉ የፓን አፍሪካን እንቅስቃሴዎችን እንዳነሳሳ አውስተዋል፡፡
የአድዋ ድል ለአውሮፓዊያን የቴክኖሎጂ እና የወታደራዊ ልምድ ብቻ ያሹትን ለመፈፀም እንደማይበቃ ያመላከተም ነበር፡፡ ብዙ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ጋዜጦች ድሉን በተለያዩ መንገዶች ገልጸውታል፡፡ ይህ ለአውሮፓ የትዕቢት መታጠፍ ነበር፡፡
በአሜሪካና በካሪቢያን ያሉ ጥቁር ሕዝቦች አድዋን እንደ ተስፋ ምልክት ተመልክተዋል፡፡ በማርከስ ጋርቬይ (Marcus Garvey) የተመራው የፓን አፍሪካ (Pan-Africanism) እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ እንደ የነፃነት ምልክት ተቀምጣለች፡፡ በአሜሪካ የጥቁር ጋዜጦች በፊት ገጻቸው አድዋን እንደ ጥቁር ድል ዘገቡት፡፡ ይህ ክስተት በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ነፃነት እንቅስቃሴዎችን አበረታቷል፡፡
አሜሪካዊው የታሪክ ምሁር ሬይመንድ ጆናስ በበኩላቸው እንደገለጹት አድዋ የኢትዮጵያ ድል ብቻ አልነበረም፡፡ የአፍሪካ ድልም ነበር፡፡ በዓለም ዙሪያ የነጻነት ንቅናቄዎችን አነሳስቷልና፡፡ በየቦታው በቅኝ ግዛት ሥር ለሚገኙ ሰዎችም ድል ነበር፡፡ ሬይመንድ አድዋ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ወታደራዊ ዘመቻዎች አንዱ እንደሆነ በብዕራቸው ከትበዋል፡፡ እንደ ታሪክ ባለሙያው ሬይመንድ ዮናስ (Raymond Jonas) “The Battle of Adwa” በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት አድዋ “የአውሮፓ ኮሎኒያሊዝም ላይ የተጣለ የመጀመሪያ ትልቅ ጥይት” ነበር፡፡ የአውሮፓን የበላይነት አፈ ታሪክን አፍርሷልና፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራን አድዋ እንደ ዓለም አቀፍ የነፃነት ምልክት አድርገው ይገልፁታል፡፡ በቅኝ ግዛት የተገዙ ሀገሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሱ አነሳስቷል፡፡ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን አበረታቷል፡፡ ድሉ በአፍሪካ እና ከዚያም በላይ የነፃነት ትግሎችን ያነሳሳ ለቅኝ ግዛት ወሳኝ ሽንፈት ተብሎ ተገልጿል፡፡ የአድዋ ድል በአውሮፓ ቅኝ ግዛት ጦር ላይ የመጀመሪያው ትልቅ የአፍሪካ ድል በመሆኑ እና ለፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄዎች መነሳሳትን ስለፈጠረ ዓለም አቀፍ የታሪክ ምሁራን አድዋ በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ካሉት በጣም አስፈላጊ ጦርነቶች አንዱ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡
ብዙ ምሁራን የአድዋን ድል ከነፃነት ንቅናቄዎች ጋር ያገናኛሉ፡፡ አድዋ በቅኝ ግዛት ለተያዙ ሕዝቦች በራስ መተማመንን እንደሰጠ ይከራከራሉ፡፡ አድዋ የቅኝ ግዛት ኃያላን ሀገራት የማይበገሩ እንዳልሆኑ አሳይቷል፡፡ ይህም በአፍሪካ እና በካሪቢያን የሚገኙ የነፃነት ንቅናቄዎችን ፈጥሯል፡፡
የአድዋ ድል የጦርነት ውጤት ብቻ አልነበረም፡፡ የአውሮፓን ፖለቲካ እና የዓለም እይታን ያናወጠ ታሪካዊ ክስተትም ነው፡፡ በወቅቱ እንግሊዝ የአድዋ ድል የዓለም ኃይል ሚዛን እንደሚቀየር በፍጥነት እንድትገነዘብ አድርጓታል፡፡ በወቅቱ ዘታይምስ( The times) የሚባለው በለንደን የሚታተመው ጋዜጣም ድሉን “አስደናቂ እና ያልተጠበቀ ሲል ዘግቦታል፡፡
ሌላዋ ሀገር ፈረንሳይ ከጣሊያን ጋር የቅኝ ግዛት ውድድር ስለነበራት ድሉን አስመልክቶ በሀገሪቱ የሚወጡ ጋዜጦች ተመጣጣኝ ደስታ ይታይባቸው ነበር፡፡ ሊ ፊጋሮ (Li Figaro)የሚባለው ጋዜጣም ድሉን “የአፍሪካ ክብር ብሎ ነበር የገለጸው፡፡ በዚህም የምኒልክ የአመራር ችሎታ በጥልቅ የተገለጸበት እና ኢትዮጵያ የአስተዳደር ችሎታ ያላት መንግሥት እንደሆነች የታወቀችበት ነበር፡፡
በጣሊያን የነበሩ ጋዜጦች ደግሞ ሀዘን እና ተቃውሞ የተሞላባቸው ነበር፡፡ ኮሪ ዴላ ሴራ(Corriere della sera)የሚባለው ጋዜጣ ድሉን “ብሔራዊ እፍረትብሎ ነበር የገለጸው፡፡ በዚህም በሮም እና በሚላን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነሳ፡፡ መሪው መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ ግፊት ተደረገበት፡፡ የጦር መሪዎች ወቀሳ ተከተላቸው፤ ፖለቲካዊ እርምጃም ተወሰደባቸው፡፡ ድሉ በጣሊያን የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ላይ ጥያቄ አስነሳ፡፡ በወቅቱ ለነበረው የፍሽስቱ መንግሥት ውድቀት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ቁስል በኋላ ፋሽስቱ የጣሊያን መንግሥት 1935ዓ.ም ኢትዮጵያን እንደገና ለመውረር አንዱ ዋና የፖለቲካ ምክንያት ሆኖለታል፡፡
የመረጃ ምንጮቻችን :- history.com. ensyclopidiyabritanica፣ journal of Ethiopian studies ናቸው፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


