ከመራጮች ምን ይጠበቃል?

0
213

ኢትዮጵያ  ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ የፊታችን ግንቦት ወር 2018 ዓ/ም ለማካሄድ በርካታ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነች ትገኛለች። በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ማለት ዜጎች ተወካዮቻቸውን፣ የሕግ አስፈጻሚውን እና የሕግ ተርጋሚውን አካል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቆጣጠርላቸውን እንዲሁም የሚተዳደሩበትን ሕግ የሚያወጣላቸውን ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ የሆነውን የሕግ አውጭ አካል የሚመርጡበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ እንደሆነ ይታወቃል።

ለምርጫ መሰረታዊ የሆኑ የምርጫ መርሆዎች መረጋገጥ እና መከበር ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መለኪያዎች ቀዳሚወቹ እንደሆነ ይታመናል። በሀገራችን የሚከናወነው ምርጫም እነዚህን መርሆዎች ማሟላት ያለበት መሆኑን በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 54 (1) እና በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 5 ላይ ማንኛውም ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛ፣ በምስጢር ድምጽ አሰጣጥ የሚተገበር፣ መራጩ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት እና ያለምንም ልዩነት በሚደረግ ሕዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም በየአምስት ዓመቱ የሚደረግ ይሆናል በሚል ተደንግጓል።

መምረጥ እና መመረጥ የሁሉም ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ቢሆንም ማንኛውም ግለሰብ ይወክለኛል፣ ሃሳቤን ይገልጽልኛል ወይም ድምጽ ይሆነኛል የሚለውን ተመራጭ ለመምረጥ ይችል ዘንድ ማሟላት የሚገባቸው ሁኔታዎች እንዳሉት የምርጫ ቦርድ መመሪያ ይደነግጋል። በመሆኑም ለመምረጥ የሚፈልግ እና የሚችል ማንኛውም ሰው በማንኛውም የምርጫ  ዘመን ለመሳተፍ እንዲችል ከሁሉም አስቀድሞ በመራጭነት መመዝገብ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ተግባር ነው።

መራጩ በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መስፈርቶችን እና የሚያስፈልጉ ሰነዶችንም በምርጫ ሕግና እንደ አስፈላጊነቱም በምርጫ ቦርድ በሚወጡ መመሪዎች ይዘረዘራሉ፡ ነገር ግን እነዚህ መስፈርቶች ተገቢ እና አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ እንጅ አንድን ሰው ያለ አግባብ ከመራጭነት የሚያገሉ  እንዳልሆኑ አዋጁ አስቀምጧል።

በዚህም አንድ መራጭ  ለመራጭነት የሚያስችለውን ምዝገባ ማድረግ ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሲሆን ለመመዝገብም የሚችለውም  በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 18 አዋጅ ቁ. 1162/2011 መሰረት ሲሆን  መራጩ ሊያሟላቸው ስለሚገባው መስፈርቶችም ተዘርዝረዋል።

መረጃው እንደ ሚያመላክተው አንድ ግለሰብ  ለመምረጥ የሚያስችለውን ካርድ ለማግኘት እና ለመመዝገብ ዜግነቱ ኢትዮጵዊ የሆነ፣ በምዝገባው እለት እድሜው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣ ለምዝገባ በሚቀርብበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ ስድስት ወር የኖረ ከሆነ ነው፡፡

ይሁንና እነዚህን መስፈርቶች ቢያሟላም በመራጭነት ለመሳተፍ የማይችልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉም ተዘርዝሯል። እነሱም ግለሰቡ  በአእምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ከሆነ  እንዲሁም የመምረጥ መብቱ በሕግ ወይም አግባብ ባለው ሕግ መሰረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበበት ሰው ከሆነ በመራጭነት ሊመዘገብ አይችልም።

ከዚህ በተጨማሪም መራጩ እነዚህን መስፈርቶች  በማሟላት በመራጭነት ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚሄድበት ወቅት ደግሞ   ተመዝጋቢው በሚኖርበት የምርጫ ጣቢያ ማንነቱን የሚገልጽ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት (ያልታደሰም ቢሆን)፣ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ማቅረብ ካልተቻለ  በቅርብ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ መንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ እና የመሳሰሉትን ማስረጃወች ይዞ መሄድ አለበት።

ከላይ የተዘረዘሩትን ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት መዝጋቢዎች መራጩን ለይተው የሚያውቁት ከሆነ ወይም በገጠር አካባቢ ሲሆን ደግሞ በባህላዊ እና ልማዳዊ ዘዴዎች ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ እንዲሁም ምርጫ ጣቢያው በተቋቋመበት ቀበሌ ኗሪ ከሆነና ለረጅም ጊዜ መኖሩ  ከተረጋገጠ፣ ሦስት ግለሰቦች ለነዋሪው በሚሰጡት ምስክርነት ማስረጃ አልባውን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ በቃለ ጉባኤ ተይዞ ምዝገባውን ማከናዎን ይቻላል።  በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ችለው መመዝገብ የማይችሉ ሰዎች ካሉም  በረዳቶቻቸው አማካኝነት በአካል ተገኝተው መመዝገብ ይኖርባቸዋል።

እነዚህን መረጃዎች ከመያዝ እና ከማሟላት በተጨማሪም መራጩ በሕግ የተደነገጉትን የምርጫ  ሥነ ሥርኣቶችን ማክበር ይጠበቅበታል። መራጮች ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ  ገደብ ውስጥ በቋሚ መኖሪያ ቀበሌያቸው የምርጫ ጣቢያ በመሄድ መመዝገብ፣ ሀሰተኛ መረጃ አለመስጠት እና የምርጫ ጣቢያ ሥነ-ሥርአትን ማክበር አስፈላጊ ነው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው ውስን የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ በሚመዘገብበት ወቅት ሕጋዊ መታወቂያ መያዝና ለምርጫ አስፈጻሚዎች ማሳየት፣ ምዝገባውን በሚኖሩበት ምርጫ ጣቢያ ብቻ ማድረግ እና አንድ ጊዜ ብቻ መመዝገብ የመራጮች ግዴታዎች ናቸው።

መረጃ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ መራጮች እና እጩዎች በምዝገባ ሂደት ሊያጋጥማቸው የሚችለውን መጉላላት፣ የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም  ማንኛውንም ተጽእኖ ለማስቀረት የሚያስችል አሠራር ዘርግቷል፡፡  ቦርዱ አካል ጉዳተኞች (ዐይነ ስውራን) ራሳቸውን በራሳቸው መመዝገብ እንዲችሉ፣ መራጮች ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥር እንዲኖራቸው ለማስቻል እንዲሁም መረጃ አመዘጋገብ እና አደረጃጀትን ቋሚና ዘመናዊ ለማድረግ በማሰብ ከዚህ በፊት ከነበረው የምዝገባ ሥርዓት በተጨማሪ የመራጮችን ምዝገባ በከፊል በቴክኖሎጅ የታገዘ ሲያደርግ የእጩዎችን ምዝገባ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጅ ታግዞ በራሳቸው አማካኝነት ባመቻቸው ስፍራ እንዲያከናውኑ የሚደርግ ሥርዓት ዘርግቷል።

የመራጮች ምዝገባ አማራጮች፦

“ምርጫዬ’’  የተባለውን  የሞባይል ስልክ መተግበሪያ በመጠቀም ራስን በራስ የሚመዘግቡበት አማራጭ፣ በምርጫ ጣቢያዎች የቦርዱን ተንቀሳቃሽ ስልክ /ታብሌት/ በመጠቀም በምርጫ አስፈጻሚዎች አማካኝነት የሚከናወን የመራጮች ምዝገባ እና በቀደመው አሠራር በምርጫ ታዛቢዎች በአካል በመገኘት በእጅ (በማንዋል) የሚከናወን የመራጮች ምዝገባ አማራጮች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ/ም እንደ ሚጀምርም አስታውቋል።፡

 

(ብርቱካን አትንኩት)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here