ታሪክ የቀየረው ድል

0
193

የካቲት 23 ቀን በአፍሪካ ምድር ብቻ ሳይሆን በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ዕለት ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የአውሮፓ ኃያላን አፍሪካን ለመቀራመት በነደፉት እቅድ መሠረት ጣሊያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመግፈፍ ጦር ሰበቀች። ሆኖም በአድዋ ተራሮች ሥር የተከሰተው ክስተት የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ የቀየረ፣ የነጭ የበላይነትን ትርክት የሰበረ እና የጥቁር ሕዝቦችን ኩራት ያበሰረ ሆነ ሲሉ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ  “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸውታል።

የአድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያዊ ድል ነው። አንዲት አፍሪካዊት ሀገር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀና በሰለጠነ የጦር ኃይል የተደራጀን፣ ተስፋፊና ቅኝ ገዢ፣ የወራሪውን የጣሊያንን ኃይል በባህላዊ የእጅ ጥበበኞች ስራ በምታፈራው የጦር መሳሪያ በጦርና በጋሻ፣ በጩቤና በአንካሴ፣ በጦርና በጎራዴ በመመከት ከመቶ 27 ዓመታት በፊት ዓለምን ያስደመመች፣ ምዕራባውያንን ያስደነገጠች፣ ጣሊያንን ያስበረገገች ኢትዮጵያ ናት::

በርሊን ላይ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ያቀዱትን ዕቅድ ደጋግመው እንዲያጤኑት ያደረገች፣ ብቸኛዋ በዓለም ታሪክ ጸሐፊዎችና ሊቀ ሊቃውንት አድዋ ላይ ድል ማድረጓን የመሰከሩላት፣ ድል የተቀናጀችበትን የድል በዓሏን ከአጋሮቿና ከነጻነት ናፋቂው የዓለም ሕዝብ ጋር በጋራ የምታከብረው የአድዋው ድል ባለቤት ኢትዮጵያ ናት:: የአፍሪካውያን የነጻነት አርማ ስትሆን፣ “ኢትዮጵያዊነት የዘር ሐረግ ቆጠራ ሳይሆን…ኢትዮጵያዊነት ታሪክ፣ ሕግ፣ ፍልስፍናና ማህበራዊ ስነ ልቦና መሆኑ የተረጋገጠበት የአድዋ ድል የሁሉም የነጻነት ናፋቂ ሕዝቦች ድል ነው።

ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን አድዋ ላይ ድል ያደረጉት በአንድነትና በብዙ የሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች የነደደ የሀገር ፍቅር ስሜት ጦርነቱ የተካሄደ ስለነበር ነው:: ኢትዮጵያንም ለድል ያበቃው ታላቅ አመራር ኢትዮጵያውያኖችን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ፣ ከዳር እስከዳር በአንድነት ማንቀሳቀስ ስለቻለም መሆኑን ለምለም ተሊላ በኢትዮጵያን ኢ ጆርናል ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ማጠቃለያ ላይ አብራርተዋል::

የምኒልክ ክተት አዋጅና የሕዝብ አንድነት

ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ህዝብን አንድ አድርጎ እና አስተባብሮ በመምራት፣ ጥንቃቄ እና ዕውቀት የተሞላበት ታክቲክ እና ስትራቴጂ ተጠቅመው የአድዋ ድልን እውን ማድረግ መቻላቸው ይነሳል:: ከዚህ ባሻገር አብሮ የሚነሳው በጦርነቱ ጊዜ እና ከጦርነቱ በፊት በነበሩ ሂደቶች ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በሚባል ሁኔታ በምኒልክ አመራር በመታዘዝ አንድ ሆነው በመቆማቸው ነው  ሲል ጳውሎስ ኞኞ – “አፄ ምኒልክ” በተሰኘው መጽሐፉ ያስረዳል::

በነገድ እና በጎሳ ተከፋፍሎ የነበረው፣ ከማዕከላዊ መንግስቱ ይልቅ ለቅርብ አለቆቹ (ባላባቶች) ተጠሪ የነበረውን ሰራዊት ምኒልክ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆኖ ለሀገር ለወገኑ በቁርጠኝነት መዋጋት  አንዳለበት ማሳመን ችለዋል:: ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ በቀጠለው የስልጣን ሽኩቻ እና የማዕከላዊ መንግስት መዳከም ሳቢያ ለበላይ መንግስቶች ሳይታዘዙ አካባቢያቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩትን መሪዎች ሆነ ወታደር የሚያዙትን የጦር አለቆች እንደየምግባራቸው በትዕግስት አግባብተው እና ይዘው የጋራ ጠላታቸውን እንዲያጠቁ ለማድረግ የቻሉት ሰፊ ልቦና ስለነበራቸው እንደሆነ የታሪክ ጸሐፊያን መስክረውላቸዋል::

በምኒልክ የአንድነት ዘመቻ በአገዛዛቸው በቅርብ ጊዜ የተጠቃለሉት አካባቢዎች ሳይቀሩ ጦራቸውን በውዴታ በአድዋ ጦርነት አሳትፈዋል ሲል ጆርጅ በርክሌይ “የአድዋ ዘመቻ እና የምኒልክ መነሳት” በሚለው መጽሐፉ ይገልጻል:: ንጉሰ ነገስቱ በአገር አንድነት ዘመቻቸው ይከተሉት የነበረው ፖሊሲ (አመራር)፣ በመጀመሪያ በውዴታ እንዲገባላቸው መለመን እና ማግባባት ነው:: እምቢ ያለውን ደግሞ በኃይል አሸንፎ ግዛቱን መልሶ ለተሸናፊው መስጠት ነው:: በዚህም ምክንያት ቅራኔ እና ቂም ሳይዙ ለዘመቻ ጥሪ ባቀረቡ ወቅት ከጎናቸው ተሰልፈዋል::

የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመው፣ ከድተው አሊያም አኩርፈው በረሃ ገብተው (ሸፍተው) የነበሩ ሳይቀር “የሞት ጊዜ ነውና ከጌታችን እና ከወገናችን ጋር እንሙት” እያሉ ምህረት ጠይቀው ገብተውላቸዋል:: ምኒልክም ምህረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይገባዋል ያሉትን እየሸለሙ እና እየሾሙ ስለሚሰዱ በጦርነቱ ታላቅ ተጋድሎ ፈጽመዋል:: ከነዚህም ውስጥ የየጁው ደጃዝማች ዘገየ፣ የትግራዩ ራስ ስብሐት እና ደጃዝማች ሀጎስ ተፈሪ ይጠቀሳሉ::

ለአድዋ ድል መሠረቱ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ጥሪና የሕዝቡ ፈጣን ምላሽ ነበር። “ሀገር የሚቀማ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት መጥቷልና ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ እርዳኝ” የሚለው የክተት አዋጅ ከጫፍ እስከ ጫፍ አስተጋባ። በዚህ ጥሪ መሠረት ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ሰራዊት ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ነፃነት በአንድነት ቆመ። ይህ የአንድነት መንፈስ ለወራሪው የጣሊያን ጦር ያልተጠበቀና አስደንጋጭ ነበር።

የእቴጌ ጣይቱ ብልሃትና የሴቶች ሚና

የአድዋ ድል ሲነሳ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ስም ቀድሞ ይጠራል። እቴጌ ጣይቱ በዲፕሎማሲው ረገድ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬን ለሌላ አሳልፌ አልሰጥም” በማለት የወሰዱት ጠንካራ አቋም ለጦርነቱ መነሳሳት ትልቅ ምክንያት ሆኗል። በጦር ሜዳውም ቢሆን የራሳቸውን ጦር እየመሩ ከመሳተፋቸውም በላይ፣ የጣሊያን ጦር ይጠቀምበት የነበረውን የምንጭ ውኃ በማስከበብ ጠላትን በጥማት እንዲዳከም ማድረጋቸው የታሪክ ምሁራን ለድሉ ቁልፍ ስልት እንደነበር ይመሰክራሉ።

የወታደራዊ ስልት የበላይነት

ኢትዮጵያውያን በአድዋ ጦርነት ወቅት የተጠቀሙባቸው ወታደራዊ ስልቶች እጅግ ዘመናዊና ረቂቅ ነበሩ። የጠላትን እንቅስቃሴ የሚሰልሉ ጀግኖች፣ የተሳሳተ መረጃ ለጠላት በማድረስ ወደ መጥፎ መልክዓ ምድር እንዲገቡ ያደረጉ ብልሃተኞች ነበሩ፡፡ በራስ አሉላ አባ ነጋ የሚመራው የደፈጣ ጥቃት ጣሊያኖችን ግራ አጋብቶ ነበር። በመጨረሻም በተጀመረው መጠነ ሰፊ ማጥቃት፣ የጣሊያን ጦር አይቀሬውን ሽንፈት ቀመሰ።

የአድዋን ድል እውን ማድረግ የተቻለው በስሜት ሳይሆን በብልሀት፣ በግልፍተኝነት ሳይሆን በትዕግስት፣ በመላምት ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ የታቀደ የጦር ስልት ስለተነደፈ እና አመራር ስልተሰጠበት ነው::

ጣሊያኖች የነበራቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እና የወታደር ብልጫ የሚያካክስ ብልሀት የተላበሰ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና የስለላ ስልት ምኒልክ ተጠቅመዋል:: ይህም ጠላት እንዳሰበው በጦርነት አሸንፎ ኢትዮጵያን መውረር እንዳይችል አድርጓል:: በተመካባቸው የስለላ፣ የዲፕሎማሲም ሆነ የጦር ዘዴዎቹ በኢትዮጵያዊያን ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶበት ሽንፈትን ተከናንቧል::

ምኒልክ ከጣሊያኖች ጋር ለመነጋገር በትዕግስት በራቸውን ክፍት ያደርጋሉ:: በዲፕሎማሲያዊ ውይይት ጣሊያኖቹ በብልጠት ለማታለል ሲፈልጉ ምኒልክ እንዳላወቁ ሆነው የሚፈልጉትን ለማግኘት በራሳቸው ዘዴ ይጠቀሙበታል:: ጣሊያኖች ሊያታልሏቸው በሞከሩ ቁጥር መልሰው ራሳቸውን ያምታቷቸዋል::

የአድዋ ድል ትርጉም ለዓለም

አድዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያንና በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ የነፃነት ተስፋ ሆነ። “ጥቁር ሕዝብ ነጭን ማሸነፍ አይችልም” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት የሰበረ ድል ነው። ይህም በኋለኛው ዘመን ለተነሱ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄዎችና ለብዙ ሀገራት የነፃነት ትግል ትልቅ ስንቅ ሆኗል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማም የብዙ አፍሪካ ሀገራት የነፃነት ምልክት ሆኖ እንዲመረጥ ያደረገው

ዛሬ አድዋን ስናስብ የታሪክ ማስታወሻ ብቻ አድርገን መሆን የለበትም። አድዋ የአሁኑ ትውልድ ለሀገሩ ዕድገትና አንድነት ሊጠቀምበት የሚገባ የታላቅነት ማሳያ ነው። ያኔ አባቶቻችንና እናቶቻችን በጦር ሜዳ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ዛሬም በልማትና በሳይንስ ዘርፍ አድዋን በመድገም የሀገርን ክብር ማስጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ነው።

 

ሳምንቱ በታሪክ

 

የጉራዕ ጦርነት

የካቲት 29 1871 ኢትዮጵያ የግብፅን ጦር ጉራዕ ላይ በተደረገው ጦርነት ድል አድርጋለች::ግብጾች ወደ 13,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ይዘው ነበር::ረቲብ ፓሻ በተባለ በግብጹ መሪ ወንድ ልጅ የሚመራ ጦር በምፅዋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ::ጉራዕ ሸለቆ አቅራቢያ ሁለት ምሽጎችን በጉራዕ እና ከጉራዕ ጥቂት አለፍ ብሎ በሚገኝ ተራራ ላይ ሰራ። በኢትዮጵያ በኩል በነበረው ምቹ ያልሆነ የጦር ሜዳ አቀማመጥ ምክንያት በአንድ ጊዜ 15,000 ወታደሮች ብቻ ነበሩ ለውጊያ የተሰለፉት::ሁለቱ ኃይሎች ተገናኙ::

ረቲብ በጉራዕ ምሽግ ውስጥ ካሉት 7,700 ወታደሮች ውስጥ 5 ሺዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ እንዲገጥሙ ትእዛዝ ሰጠ::ይህ የግብጽ ኃይል በራስ አሉላ አባ ነጋ በሚመራ የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈጣን ሁኔታ ተከበበ::በተደረገበት ጥቃት ወዲያው ተበተነ::ኢትዮጵያውያኑ ባገኙት ድል ሳይኩራሩ ኃይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ጉራዕ በመሸገው ኃይል ላይ ሁለተኛውን ጥቃት ሰነዘሩ::ግብፆች መከቱ::በሚቀጥለው ቀን የኢትዮጵያ ጦር ምሽጉን ደረመሰው::የግብፅ ጦር ብዙም ሳይቆይ ሸሸ።

ስታሊን ሞተ

የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት መሪ፣ ጆሴፍ ስታሊን፣ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን፣ ታላላቅ መሪዎች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል::ሰውየው፣ በሶቪየት ህብረት ታሪክ፣ በክፉና በበጐ ይነሳል::ግን ክፉው ሚዛኑ ይደፋል ይባልለታል::ጆሴፍ ቫላሳሪዮቬች ስታሊን፣ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፣ የካቲት 28 ቀን ነው::ከሩሲያው የ1917 የጥቅምት አብዮት በኋላ፣ የአብዮቱ መሪ፣ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን፣ በፀና ሕመም አልጋ ላይ መዋሉ፣ ስታሊን መሪነቱን እንዲይዝ፣ መንገድ ከፈተለት::

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here