ፋይዳን ለትምህርት ጥራት

0
105

ለመነሻነት
ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እና አሰራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ የዲጂታል መታወቂያን እንደ መፍትሄ ለመጠቀም ወስናለች፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም በጋራ የሰጡት መግለጫ ነው፡፡ የመግለጫው ጭብጥም የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በትምህርት ተቋማት መደበኛ የተማሪዎች መለያ ሊሆን ነው የሚል ነው፡፡ ተማሪዎችን በዲጅታል አውቆ መማር ማስተማሩን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ባለፈበት በዚህ ወቅት ደግሞ ክልል እና ሀገር አቀፍ ተፈታኞች ማሟላት ከሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ውስጥ የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ አንዱ እና አስገዳጅ ሆኗል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ዞኖችም ተፈታኝ ተማሪዎቻቸው የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ እንዲያወጡ በትኩረት እየቀሰቀሱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ነጋልኝ ተገኘ ሁሉም ተፈታኝ ተማሪዎች የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማድረግ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ እስካሁንም 12 የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ሺህ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

የምእራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የስጋት ደሴ በበኩላቸው ለተፈታኝ ተማሪዎች አስገዳጅ ሆኖ የመጣውን የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ለማሳካት በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። እስካሁንም የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ሙሉ ለሙሉ እንዲያወጡ መደረጉን ተናግረዋል። በገጠራማ ወረዳዎች የሚገኙ ተማሪዎች የፋይዳ መታወቂያ እንዲያወጡ የሚደረገው ጥረት ግን አሁንም ሰፊ ሥራን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ተፈታኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ፋይዳ እንዲኖራቸው ለማድረግ ደግሞ የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ወትሮውንም በርካታ ክፍተቶች የነበሩበትን የትምህርት ዘርፍ ምን ያህል ያሻሽለዋል የሚለውን በዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ በሰራችው ኢስቶኒያ ማየት ይገባል፡፡

ኢስቶኒያን
ኢስቶኒያ በትምህርት ዘርፍ ዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ ያደረገችው መሠረተ ልማትን በማጠናከር እና ሁሉንም የትምህርት አገልግሎቶች በአንድ ዲጂታል መረብ በማገናኘት ነው። ኢስቶኒያ ሁሉንም የትምህርት አገልግሎቶች ኢኮል (eKool) የተሰኘ የኢ ስኩል መድረክን በመዘርጋት ተግባራዊ ስታደርግ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅማበታለች፡፡ ኢኮል ተማሪዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ተቆጣጣሪ አካላትን የሚያገናኝ የዲጂታል መድረክ ነው፡፡ ኢኮል ለተማሪው የተሻለ ትምህርትን ይደግፋል፤ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው የትምህርት እድገት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል፤ የትምህርት ባለድርሻ አካላትም በእነሱ ሥር ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ስለሚከናወኑ ተግባራት ጥሩ አጠቃላይ እይታ እንዲኖራቸው ይረዳል።

ኢስቶኒያ ዲጂታል መታወቂያን በትምህርት ውስጥ በማካተቷ የአስተዳደር ወጪ እና የጊዜ ብክነትን ቀንሳለች፤ መምህራን ውጤት ለመመዝገብ፣ መገኘትን ለመቆጣጠር እና ሪፖርት ለመጻፍ የሚያጠፉት ጊዜ በ45 በመቶ ቀንሷል። ይህ መምህራን ትኩረታቸውን ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ረድቷል።

የማንነት ማጭበርበርን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የቻለችውም በዲጅታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት በመታገዝ ነው፡፡ ዲጂታል መታወቂያው ከባዮሜትሪክ መረጃ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በሌላ ሰው ስም ፈተና መፈተን ወይም ሐሰተኛ ትራንስክሪፕት እና ዲፕሎማ ማዘጋጀት በኢስቶኒያ የማይታሰብ ሆኗል።

ወላጆች በዲጂታል መታወቂያቸው አማካኝነት ወደ ኢ-ስኩል በመግባት የልጆቻቸውን ውጤት፣ የቤት ሥራ እና የባሕርይ ለውጥ በየቀኑ እንዲከታተሉ በማስቻሉ የተማሪዎች ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል፡፡

ሀገሪቱ ወረቀት አልባ ምዝገባን እንድታከናውን ያገዛት ዲጅታል መተዋቂያን ለትምህርት የሚለውን መርህ በማቀንቀኗ ነው፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ለመግባትም ሆነ ከአንድ ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ለመዛወር ምንም ዓይነት የወረቀት ሰነድ አያስፈልጋቸውም። ሁሉም ነገር በዲጂታል መታወቂያቸው አማካኝነት በሰከንዶች ውስጥ ይከናወናል።

ከኢስቶኒያ…
በአጠቃላይ የኢስቶኒያ ስኬት ምስጢር ቴክኖሎጂውን ብቻ ማምጣቷ ሳይሆን ዲጂታል መታወቂያውን ከዜጎች የዕለት ተዕለት የትምህርት ሕይወት ጋር በማስተሳሰሯ ነው። ኢትዮጵያም በፋይዳ መታወቂያ በኩል ይህንን ተሞክሮ በመቀመር የትምህርት አሰጣጧን ዘመናዊና ከማጭበርበር የጸዳ ለማድረግ ትልቅ ዕድል አላት።

ኢትዮጵያም በትምህርት ሚኒስቴር ስር ያለውን የተማሪዎች መረጃ ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ዳታ ቤዝ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ይህም እያንዳንዱ ተማሪ ትምህርት ቤት ሲመዘገብ የሚሰጠው መለያ ቁጥር ከፋይዳ ቁጥሩ ጋር አንድ እንዲሆን ያስችለዋል፡፡ ይህ ተማሪው ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አንድ ወጥ የሆነ ዲጂታል ማንነት እንዲኖረው ከማድረግም ባሻገር ውጤቱም ሆነ የትምህርት ታሪኩ በዚህ ቁጥር ስር ስለሚታሰር የመረጃው መጥፋትና መጭበርበርን ሙሉ ለሙሉ ሊያስቀር ይችላል፡፡

መንግሥት ትኩረት
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ያደረገው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ የማንነት ማጭበርበርን ለመቆጣጠር፣ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ከምንጩ ለማድረቅ እና በፈተና ወቅት የሚታየውን ሌብነት በቴክኖሎጂ ለመከላከል ነው። የተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ በመዋሉ ከሚገኙት ጥቅሞች መካከል የተማሪዎችን ማንነት በወጥነት መለየት የሚያስችል ስርዓት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል፡፡

ይህም ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም የትምህርት ተቋማት አበይት የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችል እና የአሰራር ድግግሞሽን በመቀነስ እንዲሁም በተማሪዎች የትምህርት ሰነዶች መካከል አንድነት እና ቅንጅትን እንደሚያጠናክር ነው ያረጋገጡት፡፡

ከዚህም በላይ በላቀ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የግል መረጃን የማስቀመጥ እና የመጠቀም ደህንነትን በእጅጉ ይጨምራል፤ የውሂብ ጥበቃን ያረጋግጣል፤ ማንኛውም አይነት ጥሰቶችን በእጅጉ ይቀንሳል። በትምህርት ተቋማቱ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ በሚፈልገው ልክ ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ዘንድሮ ደግሞ በቅድሚያ በተፈታኝ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ ለመደረግ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡

መረጃ
ዲጂታል መታወቂያ ለትምህርት ጥራት
የተማሪዎችን መረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡
የሐሰት የትምህርት ማስረጃዎችን ለመከላከል
የብሔራዊ ፈተናዎችን አሰጣጥ ፍጹም ታማኝ ለማድረግና በምዝገባ ወቅት የሚከሰቱ ስህተቶችን ይረዳል፡፡
ትክክለኛውን የተማሪዎች ቁጥር በማወቅ፣ መንግሥት ለትምህርት ቤቶች የሚያደርገውን የመጽሐፍት፣ የመምህራን እና የሌሎች ግብዓቶች ስርጭት ፍትሐዊ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ያግዛል።
ተማሪዎች ከአንድ የትምህርት ተቋም ወደ ሌላ ሲዘዋወሩ ወይም ለከፍተኛ ትምህርት ሲመዘገቡ መረጃቸው በቀላሉ እንዲገኝ በማድረግ የአገልግሎት ጥራትን ያሻሽላል።

(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here