የተናቀው ሎሌ

0
154

እስኪ አሁን ባለህበት ቆም በልና ራስህን በሚገባ ተመልከት! አሁን ኪስህ ውስጥ ወይም በባንክ ደብተርህ ላይ ስንት ብር አለህ? እስኪ ወደ ኋላ መለስ ብለህ አስብ:: ገንዘብ በማጣትህ ብቻ ስንት ወርቃማ አጋጣሚዎች አመለጡህ? አንተ ከእነሱ የተሻለ እውቀት፣ ስነ ምግባርና ችሎታ እያለህ ገንዘብ ስሌለህ ብቻ ስንት ሰዎች ንቀውሃል? የገንዘብ አቅም በማጣትህ ምክንያት ብቻ የተነጠቅከውን ክብር፣ ወላጆችህ ወይም የምትወደው ሰው ታሞ ማሳከሚያ አጥተህ በፀፀት ያነባህበትን የሀዘን ቀን አስታውስ!

በራስህ ላይ የምትወስነውን ውሳኔ ሌሎች ሲወስኑብህ፣ ኑሮ ቢከብድህም አማራጭ ስላጣህ ብቻ አንገትህን ደፍተህ የሰራህበትን ያንን አሰልቺ ስራ፣ የቤት ኪራይ መክፈያ ሲደርስብህ እንቅልፍ አጥተህ  በጭንቀት የተገላበጥክበትን ሌሊት እስኪ አስበው!

ይህ ሁሉ እውነት ሆኖ ሳለ እኛ ኢትዮጵያውያን ለገንዘብ ያለንን አመለካከት መመርመር ያለበት ነው::  በሚያስገርም የድህነት ማዕቀፍ ውስጥ የተተበተበ ነው:: በአንድ በኩል ከማለዳው 12:00 እስከ ምሽቱ 2:00 ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀብን የምንባዝነው፣ የምንለፋው እና የምንዋትተው ያንኑ ገንዘብ ፍለጋ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ አፋችንን ሞልተን “ገንዘብ የእጅ እድፍ ነው”፣ “የሀጢያት ስር ነው”፣ “ከገንዘብ ይልቅ ሰላም ይበልጣል” እያልን እናንቋሽሸዋለን::

ልብ እንበል! ገንዘብ እንደ እስትንፋስ የሕይወታችን መሰረት ሆኖ ሳለ እኛ ግን ከንፈር እንመጥበታለን:: የተፈጥሮ ህግ ደግሞ ግልፅ ነው:: የናቅኸው ነገር ይንቅሃል:: የጠላኸው ይሸሽሃል:: እኛ በአፋችን ገንዘብን ስንሸሸው  እሱ ደግሞ የሕይወታችን ጌታ ሆኖ እየተጫወተብን ይገኛል::

ገንዘብ ማጣት ሆድን ብቻ ሳይሆን አእምሮንም ያኮማትራል፤ ስነ-ልቦናን ይሰልባል፤ ወኔን ይገፋል:: በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና እና የኢኮኖሚክስ ተመራማሪዎች ሴንድሂል ሙላይናታን እና ኤልዳር ሻፊር “ገንዘብ ማጣት በሕይወታችን ላይ ለምን የጎላ ተጽዕኖ ይኖረዋል” በተሰኘው ጥናታቸው አስገራሚ ግኝት አውጥተዋል:: የገንዘብ እጥረት እና ስለ ገንዘብ መጨነቅ የሰውን ልጅ የማሰብ፣ የማመዛዘን እና የፈጠራ አቅም (IQ) በ13 ነጥብ ይቀንሰዋል ብለዋል:: ይህ ማለት አንድ ሙሉ ሌሊት እንቅልፍ ያጣ ሰው ከሚያሳየው የአእምሮ መዛል ጋር እኩል ነው:: ማጣት ጭንቀትን ይወልዳል፤ የቤተሰብ ፍቅርን ያቀዘቅዛል፤ መተማመንን ያጠፋል::

ታዋቂው የስነ ልቦና ምሁር አብርሃም ማስሎው “በፍላጎቶች እርከን” ሥራው  እንዳስቀመጠው አንድ ሰው መሠረታዊ የህልውና ጥያቄዎችን (ምግብ፣ መጠለያ፣ ልብስ) በገንዘብ ካልፈታ በስተቀር ወደ ላቀ የሕይወት ትርጉም፣ መንፈሳዊነት እና የፈጠራ ስራ መሸጋገር አይችልም::

አሜሪካዊው አነቃቂ ጸሐፊ ዚግ ዚግላር ይህንን ሲገልጽ “ገንዘብ ሁሉ ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ልክ እንደ ኦክስጂን አስፈላጊነቱ የማይካድ ነው” ብሏል:: ገንዘብ ማጣት በቁም እንደመታፈን ነው::

ገንዘብ ማግኘት ማለት ዘመናዊ መኪና ከመንዳት እና ትልቅ ቪላ ውስጥ ከመኖር የዘለለ እጅግ ጥልቅ ትርጉም አለው:: ትልቁ የገንዘብ ጥቅም ‘ነፃነት’ ነው:: ሞርጋን ሃውሰል “የገንዘብ ስነ ልቦና” በተሰኘው እና ሚሊዮኖችን ባነቃው መጽሐፉ ላይ “የገንዘብ ትልቁ ዋጋ እና ትርፍ የራስህን ጊዜ እንድትቆጣጠር ማስቻሉ ነው:: በፈለከው ጊዜ፣ ከፈለከው ሰው ጋር፣ የፈለከውን ነገር ማድረግ መቻልህ… ገንዘብ ከሚሰጥህ ነገሮች ሁሉ የላቀው የነፃነት ጣዕም ነው” ብሏል::

ገንዘብ ሲኖርህ “እምቢ” የማለት አቅም ይኖርሃል:: ለማትፈልገው አሰሪ፣ ለሚያስጨንቅህ ስራ፣ አላማህን ለሚያኮላሽ አካባቢ “አልፈልግም” ብለህ መውጣት የምትችለው በባንክህ ውስጥ የነፃነትህ ዋስትና የሆነ ገንዘብ ሲኖርህ ብቻ ነው::

ከዚህም ባለፈ ሰውን መርዳት፣ ቤተ ክርስቲያን ማነፅ፣ መስጊድ መገንባት፣ ትምህርት ቤት መክፈት፣ እና ያሰብከውን በጎ አላማ ከግብ ማድረስ የምትችለው ሃሳቡን ብቻ ሳይሆን አቅሙን (ገንዘቡን) ስትይዝ ነው:: ገንዘብ በባህሪው መጥፎም ጥሩም አይደለም፤ ገንዘብ አጉሊ መነፅር  ነው:: ጥሩ ሰው ከሆንክ፣ በገንዘብህ ብዙ ጥሩ ነገር ትሰራለህ::መጥፎ ከሆንክ ደግሞ ጥፋትህን ያጎላዋል::

ታላላቅ የኢኮኖሚ ምሁራን ጀግና ስራ ፈጣሪዎች እና ፈላስፎች እንደሚሉት ገንዘብ የሚገኘው ላብ በማፍሰስ ብቻ ሳይሆን “እሴት በመፍጠር” ነው:: ገበያ ወይም ዓለም የሚከፍልህ ስላላብህ እና ስለደከምክ ሳይሆን የሰዎችን ችግር በፈታህበት ልክ ነው::

ሮበርት ኪዮሳኪ “ሪች ዳድ ፑር ዳድ” በሚለው መጽሐፉ የደሃና የሀብታም ልዩነት አመለካከት እና የፋይናንስ እውቀት እንደሆነ አጥብቆ ይሞግታል:: “ሀብታሞች ገንዘብ ለእነሱ እንዲሰራ ያደርሉ:: ድሆች እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ግን ለገንዘብ ብለው ይሰራሉ” ይላል:: ገንዘብን ለማግኘት ከስሜታዊነት ወጥቶ የሰዎችን ፍላጎት መረዳት እና ለዚያ መፍትሄ መስጠት ግድ ይላል:: ታዋቂው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት “ተኝተህም ገንዘብ የምታገኝበትን መንገድ ካልፈጠርክ፣ እስከምትሞት ድረስ ትለፋለህ” በማለት ገቢን ማብዛትና ገንዘብን ማሰራት ወሳኝ መሆኑን አስተምሯል::

“ባለጸጋው በባቢሎን” የተሰኘው የጆርጅ ክላሰን ጥንታዊ ጥበብ ያዘለ መጽሐፍ ገንዘብን ለማቆየት እና ለማባዛት መተግበር ያለብንን ወርቃማ ህጎች ያስቀምጣል። “ከምታገኘው ገቢ ቢያንስ አስር በመቶው ያንተ ነውና ለራስህ ክፈል (አስቀምጥ)” በማለት የቁጠባን መሰረት ይናገራል::

ይህ እኛ ኢትዮጵያውያን ልንማረው የሚገባ ትልቅ ትምህርት ነው:: እኛ ብዙ ጊዜ ገንዘብ የምንሰበስበውና የምንቆጥበው (ለዕቁብ፣ ለሰርግ፣ ለበዓል እና ለዕድር) መልሰን ልናጠፋው ነው:: የሀብት ህግ ግን የተለየ ነው:: ገንዘብን ለቅንጦት፣ “ሰዎች ምን ይሉኛል” ለሚል እይታ እና ለታይታ ሳይሆን ተጨማሪ ሀብት ለሚያመነጩ ጉዳዮች ማፍሰስ የጥበበኞች መንገድ ነው:: ያስቀመጥከው እያንዳንዱ ብር እንደ ወታደር ነው:: እሱን ኢንቨስት ስታደርገው ወታደር ዘምቶ ሌሎች ወታደሮችን ማርኮ እንደሚያመጣልህ ሁሉ ሌሎች ገንዘቦችን ያመጣልሀል::

የእንግሊዙ ፈላስፋ ፍራንሲስ ቤከን “ገንዘብ ምርጥ ሎሌ ነው፤ ነገር ግን እጅግም አስከፊ ጌታ ነው” በማለት አስጠንቅቋል:: ገንዘብን መጥላት እና ማናናቅ መንፈሳዊነት ወይም ትህትና ሳይሆን ኃላፊነትን መሸሽ፣ ድህነትን መለማመድ እና ራስን ማታለል ነው። ገንዘብ የሕይወታችንን ጥራት እና የሌሎችን ችግር መፍቻ ኃይለኛ መሳሪያ ነው::

 

(አቢብ አለሜ)

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here