በዓድዋ የድል መንፈስ በመራመድ ችግሮቻችንን እንፍታ!

0
68

ኢትዮጵያውያን  የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የባህል  ልዩነት፣ የቦታ ርቀት ሳይወስናቸው ከያሉበት  ተጠራርተው ወራሪውን የጣሊያንን ጦር ዓድዋ ላይ ድል ካደረጉት እነሆ 130 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በኢትዮጵያውያን ተጋድሎ የተመዘገበው የዓድዋ ድል የቅኝ ገዥዎች ቅስም የተሰበረበት፣ የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ጀግንነት ለዓለም ገዝፎ የታየበት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ከሆኑ ድሎች አንዱ ነው። የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ነጻነት እና ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደሩ ስለመሆናቸው ለዓለም ያስመሰከሩበት  ታላቅ ገድል ነው።

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን  የአሸናፊነት  ተምሳሌት ከመሆኑም በላይ ለአፍሪካውያን ነፃነት መረጋገጥ መንገዱን ያሳየ ሁነኛ ክስተት ነው፡፡ የዓደዋ ድል ባርነት እና ጭቆና የአፍሪካውያን ግብር አለመሆኑ የተረጋገጠበት፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ብዝበዛዎች እልባት እንዲያገኙ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረ  ድል ነው፡፡

የዓድዋ ድል  አውሮፓውያን  “ጥቁር ሕዝብ በሥልጣኔ እና በጦር መሣሪያ የበላይ የሆነን ነጭ ኃይል ሊያሸንፍ አይችልም” ብለው በሚያምኑበት ዘመን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስካፍንጫው የታጠቀ ወራሪ ደል የተደረገበት  የጥቁር ሕዝብ ትንሣኤ፣ የኢትዮጵያዊነት የአልበገርም ባይነት  ማኅተም የታተመበት እና የማይቻል የሚመስለው የአብሮነት ሕብረት ዕውን የሆነበት ታላቅ ድል ነው።  የዓድዋ ድል አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ከመኾኑም በላይ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መነሻ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ድሉ በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ አፍሪካዊ ሉዓላዊነት የተረጋገጠበት ታላቅ ክስተትም  ነው፡፡

የዓድዋ ድል ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ከመቶ ሺህ በላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን  በአንድነት ያስመዘገቡት ምንጊዜም የማይደበዝዝ  ደማቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ነው። የዓድዋ  ድል የተለያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖት እና ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያን  ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ… ሳይባባሉ   ለአንድ ዓላማ ባንድነት ቆመው የ “ኢትዮጵያዊነትን”  ምንነት ለዓለም ያሳዩበት  ትልቅ  ክስተት ስለመሆኑ ያለማችን ታላላቅ የፖለቲካ እንዲሁም የታሪክ ምሁራን ሳይቀሩ በመመስከር ጽፈዋል፡፡ ምሁራኑ ስለ ዓድዋ የመሰከሩት ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ ድል በመሆኑም ነው፡፡

የዓድዋ ድል የቀደምት ኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ገድል ከመመስከር እና የቅኝ ገዥዎችን በቅኝ ገዥነት የመስፋፋት ተስፋ ከማጨለም ባለፈ ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ትምህርትን ያዘለ ድንቅ ክስተት ነው፡፡ አባቶቻችን ከመላው ኢትዮጵያ ተጠራርተው እሾህ ጋሬጣው እየወጋቸው፣ ርሃቡ ጥሙ ሳይበግራቸው፣ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ  ለወራት በእግራቸው ተጉዘው  ዓድዋ ድረስ በመዝመት ድል ማድረጋቸው የዛሬው ትውልድ የመንፈስ ጽናትን ከተላበሰ፣ አንድነቱን ካጠናከረ ካለበት የድህነት እና የኋላ ቀርነት አዙሪት መውጣት ከቶም እንደማይሳነው  ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ የታሪክ አሻራ ነው፡፡ ዘመናዊ ወታደራዊ ትምህርት ቀስሞ፣ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ባይነት ታጥቆ  የመጣን የተደራጀ ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያውያን በጦር እና በጎራዴ ድል ማድረጋቸው  የዛሬው ትውልድ ዕውቀትን እና ቴክኖሎጂን ታጥቆ ባንድነት ከሠራ ድህነትን ማሸነፍ፣ ሀገሩን ኢትዮጵያን ካለም ሀያላን ሀገራት አንዷ ማድረግ ከቶም እንደማይከበደው ሁነኛ ማረጋገጫ ነው፡፡

የፊቱ ከሌለ የኋላው የለም እንዲሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር የዓለማችን ሕዝብ ድል የሆነውን የዓድዋን ድል በያመቱ መዘከር የሚገባ ነው፡፡ ኾኖም ድሉን ከመዘከር ባለፈ መለስ ብሎ የዓድዋን የአንድነት፣ የትግል እንዲሁም የድል መንፈስ  በጥልቀት መፈተሽ፣ ከመሪ እስከ ሕዝቡ በትግሉ ወቅት የነበረውን ሚና ማጤን ያንን ተሞክሮ  ተጠቅሞ ከችግር መውጣት ያስፈልጋል፡፡ የዓድዋን ድል ስንዘክር አንድ ሆነን ከተነሳን የማናሳካው ነገር፣ የማንፈታው ችግር እንደማይኖር አውቀን  በዓድዋ የድል መንፈስ ልንራመድ እና ችግሮቻችንን ልንፈታ ይገባል፡፡

 

በኲር የካቲት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here