የቫይታሚን ዲ እጥረት እና መፍትሔዎቹ

0
162

ቫይታሚን ዲ በስብ የሚሟሟ ንጥረ ነገር ነው:: የካልሲየም እና ፎስፌት ደረጃዎችን በመቆጣጠር ጤናማ አጥንት፣ ጥርሶች እና ጡንቻዎች እንዲኖሩ ይረዳል:: ከተለያዩ የምግብ ዓይነቶችም ይገኛል፤ እንዲሁም በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት ቆዳ ላይ የሚመረት የቫይታሚን ዓይነት ነው::

ቫይታሚን ዲ ካልሲየም የሚባለውን ንጥረ ነገር ከአንጀት ወደ ደም እንዲገባ (እንዲመጠጥ) ይረዳል::

ቫይታሚን ዲ በአጥንት ጤና ላይ ካለው ዋና ሚና በተጨማሪ የተለያዩ የሰውነት ሥርዓቶችን ይደግፋል:: ለአብነትም በልጆች ላይ እንደ የአጥንት መልፈስፈስ (rickets) እና በአዋቂዎች ላይ የአጥንትን መሳሳትን (osteomalacia) ይከላከላል::

ቫይታሚን ዲ በሽታ የመከላከል ሥርዓትን የሚያጎለብት ሲሆን ባክቴሪያ እና ቫይረሶችን ሊዋጋ እና እብጠትን ሊቀንስ ይችላል:: ለጡንቻ እንቅስቃሴ እና ነርቮች በአንጎል እና በሰውነት መካከል መልዕክቶችን እንዲያስተላልፉ አስፈላጊ ነው:: የበሽታ መከላከል አቅምን ለማጠናከር፣ ስሜትን እና የአንጎልን ሥራ ለማስተካከል፣ ቁስል በፍጥነት እንዲድን ለማድረግም ይረዳል:: አንዳንድ ካንሰሮችን፣ የልብ ሕመም እና ለዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ የመጋለጥ ዕድሎችን ሊቀንስም ይችላል::

 

የቫይታሚን ዲ እጥረት እና ምልክቶቹ

የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለበት ሰው አብዛኛውን ጊዜ ምንም አይነት ሕመም ሳይሰማው ይቆያል:: የእጥረቱ ደረጃ ከፍ ሲል ወይም ብዙ ጊዜ ከቆየ የአጥንት  መሳሳትን እና የአጥንት ሕመምን ይፈጥራል:: በተለይም  ከፍተኛ የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለበት ሰው ሰውነቱ ወይም ጡንቻው ሲነካ የሕመም ስሜት ይኖረዋል፣ ወይም ደግሞ በቀላል አደጋ ወይም ግጭት  የአጥንት ስብራት ያጋጥመዋል::

የመገጣጠሚያ ሕመም፣ በተደጋጋሚ የሚከሰት የድካም እና የመዛል ስሜት፣  የትከሻና የወገብ የሕመም ስሜቶች የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለበት ሰው ላይ ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው::

በሽታ የመከላከል አቅም መቀነስ፣ የስሜት መለዋወጥ፣ የእግርና እጅ የመደንዘዝ እና ማቃጠል ስሜት የቫይታሚን ዲ እጥረት ተጨማሪ ምልክቶች ናቸው::

ሆኖም የተጠቀሱት ሁሉም ምልክቶች የቫይታሚን ዲ እጥረት ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ:: ምክንያቱም በርካት በሽታዎችም ተመሳሳይ ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላልና ነው::

አንዳንድ ሰዎች ላይ  የቫይታሚን ዲ እጥረት  በከፍተኛ ሁኔታ ሲከሰት የጸጉር መሳሳት እና መነቃቀል ሊከሰትባቸው ይቻላል::

 

ለቫይታሚን ዲ እጥረት የሚጋለጡ እነማን ናቸው?

ለፀሐይ ብርሃን ተጋላጭነታቸው የተገደበ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው፣ በቂ ቫይታሚን ዲ ከምግብ የማያገኙ ሰዎች፣ ወይም ስር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ቫይታሚን ዲ ከአንጀት ወደ ደም በትክክል እንዳይገባ በማድረግ እጥረትን ይፈጥራሉ:: የኩላሊትና ጉበት በሽታዎች መኖር ቫይታሚን ዲ በትክክል እንዳይመረት ያደርጋሉ:: ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች ከሌላው በተለዬ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው::

 

ቫይታሚን ዲ እንዴት ይዘጋጃል?

ሰውነት  ቫይታሚን ዲ በራሱ ሲያዘጋጅ  ጉበትን እና ኩላሊትን ይጠቀማል:: የፀሐይ ጨረር  በራሱ ቫይታሚን ዲ መያዝ አይችልም:: ነገር ግን የአንድ ጤናማ ሰው ቆዳ  የፀሐይ ጨረር ሲነካው ቫይታሚን ዲን በቆዳው ላይ ያዘጋጃል:: በቆዳው ላይ የተሠራው ቫይታሚን ዲ በደም ሥር  ወደ  ጉበት እና ኩላሊት ይሄድና በድጋሚ ተብላልቶ ወደ አንጀት በመሄድ ሰውየው ከተመገበው ምግብ ውስጥ ካልሲየም የተባለ ብረታማ ንጥረ ነገር ወደሰውነቱ እንዲመጠጥ ያደርጋል::

ካልሲየም ዋነኛ ሥራው አጥንትን ማጠናከር ነው:: በዚህ ምክንያት ከሰውነት ክፍሎች ውስጥ ከፍተኛውን ካልሲየም የሚይዘው አጥንት ነው:: ለምሳሌ ከአጥንታችን ወስጥ ይህ ካልሲየም የተባለው ንጥረ ነገር ሙሉ በሙሉ ቢወጣ የአጥንት መልፈስፈስ ያጋጥማል::

ካልሲየም አጥንትን ከማጠናከር ባሻገር  ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት:: የጡንቻ እንቅስቃሴ፣ የልብ ምት፣ የሰውነት ማብልያዎች ሁሉ ካልሲየም ሳይጠቀሙ በአግባቡ መሥራት አይችሉም::

የቫይታሚን ዲ እጥረት ሲኖር ይህ ብረታማ ንጥረ ነገር ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ  ሳይብላላ በአይነ ምድር ከሰውነት ይወገዳል:: ይህ እንዳይደርስበት  በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች  የሚገኘውን ካልሲየም ሰውነታችን እያወጣ ይጠቀማል:: ሆኖም  ሰውነት የራሱን ካልሲየም መጠቀም ከጀመረ ቀስ በቀስ የአጥንት መሳሳትን ያስከትላል::

 

ቫይታሚን ዲ ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት?

የአንድን ሰው የቫይታሚን ዲ እጥረት ያለበት መሆኑን ለማወቅ በደም ውስጥ ያለውን የቫይታሚን ዲ መጠን መመርመር  ይገባል:: በአንድ ጤናማ ሰው ላይ በሚወሰድ የአንድ ሚሊ ሊትር የደም መጠን ከ30 እስከ 100 ናኖ ግራም ቫይታሚን ዲ መኖር አለበት:: የቫይታሚን ዲ መጠን ከ20 ወይም ከ15 ናኖ ግራም በታች ከሆነ ሰውየው የቫይታሚን ዲ ማስተካከያ መድኃኒቶችን መውሰድ አለበት::

የቫይታሚን ዲ መጠን የሚለካው ኢንተርናሽናል ዩኒት (international unit) በሚባል ልኬት ነው:: አንድ ሚሊግራም ቫይታሚን ዲ እንክብል (ሳፕልመንት) ከ40 ሺህ ኢንተርናሽናል ዩኒት ጋር እኩል ነው::

ከአንድ ዓመት በታች ያሉ ሕጻናት በቀን  400 ኢንተርናሽናል ዩኒት ወይም  ማይክሮ ግራም  ያስፈልጋቸዋል:: ከአንድ አመት እስከ 70 ዓመት ላሉ ሰዎች በቀን 600 ኢንተርናሽናል ዩኒት ወይም አንድ ነጥብ አምስት ማይክሮ ግራም መውሰድ አለባቸው:: ከ70 ዓመት በላይ ለሚገኙ ዕድሜያቸው ከፍ ላለ ሰዎች ደግሞ በቀን 800 ኢንተርናሽናል ዩኒት ወይም ሁለት ማይክሮ ግራም ያስፈልጋቸዋል::

አንድ ሰው በየቀኑ ልብስ ሳይለብስ በጠዋት ፀሐይ ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ቢሞቅ በቂ ቫይታሚን ዲ ለማግኘት በጣም ተፈጥሯዊ መንገድ ይሆንለታል::

ሕፃናትን ደግሞ ከተወለዱ ከሁለት ሳምንት ጀምሮ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ የጠዋት ጸሐይ ማሞቅ አስፈላጊ ነው:: ታዲያ ሕፃናትም ሆነ አዋቂዎች ፀሐይ ሲሞቁ ምንም አይነት የሰውነት ቅባት መጠቀም እና ልብስ መሸፈንም  የለባቸውም::

በተጨማሪም የቫይታሚን ዲ እጥረትን ለማስተካከል የዓሳ ዘይት፣ የከብት ጉበት እና የእንቁላል አስኳል መመገብ ይመከራል:: እንዲሁም ቫይታሚን ዲ ተጨምሮባቸው በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችንም መመገብ ይመከራል::

በሌላ በኩል የቫይታሚን ዲ ከመጠን በላይ በሰውነት ውስጥ መኖር የኩላሊትን ሥራ እንደሚያውክ ልብ ሊባል ይገባል:: በሰውነት ውስጥ የደም ቧንቧዎችን እና የልብ “ቫልቮችን” ጨምሮ የልብ ድካም እና አልፎ ተርፎም ሞትን ያስከትላል:: ከፍተኛ መጠን ያለው ቫይታሚን ዲ በሰውነት ውስጥ መኖር የካልሲየም ክምችት (hypercalcaemia) እንዲኖር ያደርጋል:: ይህም ኩላሊትን እና ልብን ይጎዳል::

 

ጤና አዳም

ቫይታሚን ዲ እንክብል በባዶ ሆድ አይወሰድም፡፡

ቫይታሚን ዲ  በስብ የሚሟሟ በመሆኑ ጤናማ ቅባት ያለቸውን ምግቦች ተመግቦ መውሰድ ይመከራል፡፡

ከፍተኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ ቫይታሚን ዲ መወሰድ የለበትም፡፡ ከ30 እስከ 1 ሰዓት ረፍት ካደረጉ በኋላ ቢወሰድ ይመከራል፡፡

የቫይታሚን ዲ እንክብል ደረቅ እና ቀዝቃዛ ቦታ መቀመጥ አለበት- እንዲሁም ለጸሐይ ብርሃን መጋለጥ የለበትም፡፡

ቫይታሚን ዲ እንክብል ሲወስዱ የጤና ባለሙያ አማክረው መሆን አለበት፡፡

ምንጭ ፡- ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሄልዝ (National Institutes of Health)፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 30  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here