የትራፊክ ደህንነት

0
122

የልጆች የትራፊክ ደህንነት ግንዛቤ የትምህርት ብቻ ሳይሆን የህይወት መትረፍ ጉዳይ ነው። ህጻናት እንደ አዋቂዎች የርቀትና የፍጥነት መጠንን የመገመት ብቃት ስለሌላቸው በመንገድ ላይ ለሚፈጠሩ አደጋዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው። በመሆኑም መሰረታዊ የትራፊክ ደንቦችን ማስተማርና በተግባር ማሳየት የእያንዳንዱ ወላጅ እና መምህር ቀዳሚ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

ህጻናት መንገድ ሲሻገሩ ሁልጊዜም “ቁም፣ ተመልከት፣ አዳምጥ” የሚለውን መርህ እንዲከተሉ ማሳሰብ ያስፈልጋል። ወደ ግራና ወደ ቀኝ በሚገባ መመልከት፣ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ መቆማቸውን ማረጋገጥ እና የእግረኛ ማሻገሪያ (ዘብራ) ባለባቸው ቦታዎች ብቻ መሻገርን መልመድ ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በመንገድ ዳርቻ ላይ አለመጫወት እና ከቆሙ መኪናዎች በስተጀርባ ወይም መሃል ድንገት አለመውጣትን በልጅነታቸው ሊገነዘቡት የሚገባ ትልቅ ትምህርት ነው።

ከንድፈ ሃሳብ ትምህርት ባለፈ፣ አዋቂዎች በመንገድ ላይ የሚያሳዩት ጥንቃቄ ለልጆች ትልቁ መማሪያ ነው። እኛ ራሳችን የትራፊክ መብራቶችን ስናከብር እና በእግረኛ መንገድ ስንጓዝ ልጆቻችንም ይህንን መልካም ልማድ ይወርሳሉ። በትምህርት ቤቶች እና በመኖሪያ አካባቢዎች የሚደረጉ የደህንነት ግንዛቤ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ዛሬ ለልጆቻችን የምንሰጠው ጥንቃቄ እና እውቀት፣ ነገ በሰላም ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ዜጎችን ለማፍራት ዋስትናችን ነው።

የትራፊክ ደህንነት መመሪያዎች

  • መንገድ ከመሻገር በፊት መቆም፦ ወደ አስፋልት መንገድ ከመውጣት በፊት ሁልጊዜ በእግረኛ መንገድ ዳር ላይ መቆም ያስፈልጋል። በድንገት ወደ መንገድ መሮጥ በፍጹም የተከለከለ ነው።
  • ግራና ቀኝን መመልከት፦ መጀመሪያ ወደ ግራ፣ ቀጥሎ ወደ ቀኝ፣ ከዚያም ደግሞ እንደገና ወደ ግራ መመልከት። መኪና አለመምጣቱን ካረጋገጡ በኋላ ብቻ መሻገር ይገባል።
  • ጆሮን አጽድቶ ማዳመጥ፦ አይን የማያየውን የመኪና ድምፅ ጆሮ ሊሰማው ይችላል። የሚመጣ መኪና ወይም የጥሩምባ ድምፅ መኖሩን በጥንቃቄ ማዳመጥ አስፈላጊ ነው።
  • የእግረኛ ማሻገሪያን (ዜብራ) መጠቀም፦ መንገድ ሲሻገሩ ሁልጊዜ ነጭ መስመር ያለበትን የእግረኛ ማሻገሪያ መጠቀም። መስመሩ በሌለበት ቦታ መሻገር አደገኛ ነው።
  • የትራፊክ መብራቶችን ማወቅ፦ የቀይ፣ የቢጫ እና የአረንጓዴ መብራቶችን ትርጉም መረዳት። በተለይ የእግረኛ መሻገሪያ ምልክቱ “አረንጓዴ” ሲሆንና መኪናዎች መቆማቸውን ካረጋገጡ በኋላ ብቻ መሻገር።
  • በመንገድ ላይ አለመጫወት፦ አስፋልት መንገድ ወይም የመኪና ማቆሚያ ስፍራ የጨዋታ ቦታ አይደለም። ኳስ ሲጫወቱ ወደ መንገድ ቢወጣ ሮጦ ከመከተል ይልቅ ትልቅ ሰው እንዲያመጣ መጠየቅ ይመከራል።
  • ከቆሙ መኪናዎች ጀርባ አለማለፍ፦ የቆመ መኪና ድንገት ወደ ኋላ ሊንቀሳቀስ ስለሚችል፣ ከመኪናው ጀርባ መቆም ወይም ማለፍ በጣም አደገኛ ነው።
  • በእግረኛ መንገድ (Platform) ላይ መጓዝ፦ ሁልጊዜ ከመኪና መንገድ ወጣ ብሎ የተሰራውን የእግረኛ መንገድ መጠቀም። የእግረኛ መንገድ ከሌለ ደግሞ የሚመጡ መኪናዎችን ፊት ለፊት እያዩ በግራ በኩል መጓዝ።

ምንጭ፡- ኪድስ ኢንሳይክሎፒዲያ

ተረት

      ሊዮ እና ኩሉ

ከዕለታት አንድ ቀን፣ በአንድ ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ውስጥ ኩሉ የሚባል በጣም ፈጣን ዝንጀሮ ይኖር ነበር። ኩሉ ከአንዱ የዛፍ ቅርንጫፍ ወደ ሌላው ሲዘል እንደ ንፋስ ይፈሳል፤ ነገር ግን አንድ መጥፎ ልምድ ነበረው። ኩሉ ማንኛውንም ነገር ቶሎ ቶሎ መጨረስ እንጂ በጥራትና በማስተዋል መስራት አይወድም ነበር። በዚያው ጫካ ውስጥ ደግሞ ሊዮ የሚባል በጣም ታጋሽና አስተዋይ አንበሳ ይኖር ነበር። አንድ ቀን የጫካው ንጉስ ለእንስሳቱ ሁሉ አንድ ትልቅ ውድድር አዘጋጀ። ውድድሩም በጫካው መጨረሻ ላይ ካለው ትልቅ ወንዝ ማዶ የሚገኘውን ብርቅዬ የወርቅ ፍሬ ቀጥፎ መመለስ ነበር።

ውድድሩ እንደተጀመረ ኩሉ ዝንጀሮ “እኔ እኮ ፈጣን ነኝ፤ ገና ሰዎቹ ሳይነሱ ደርሼ እመለሳለሁ” ብሎ በከፍተኛ ፍጥነት ሮጠ። በመንገዱ ላይ የሚያጋጥሙትን አዝመራዎች እየረገጠ፣ ትናንሽ እንስሳትን እየገፋ፣ ብቻ ቀድሞ ለመድረስ በጣም ቸኮለ። ሊዮ አንበሳ ግን ሳይቸኩል ጉዞውን ጀመረ። በመንገዱ ላይ የወደቁ እንስሳትን እየረዳና በጭቃ የተከደኑ መንገዶችን በጥንቃቄ እየመረጠ በዝግታ ተጓዘ። ኩሉ ግማሽ መንገድ ላይ ሲደርስ በከፍተኛ ፍጥነት ስለሮጠ በጣም ደከመው። “ማንም አይቀድመኝም” በሚል መታበይ በአንድ ትልቅ ዛፍ ስር ተኝቶ አረፈ፤ ሳያውቀውም ጥልቅ እንቅልፍ ወሰደው።

ሊዮ ግን ሳይቆም ጉዞውን ቀጠለ። በመንገዱ ላይ ኩሉ ተኝቶ ቢያየውም ዝም ብሎ አለፈው። ወንዙ ጋ ሲደርስ ውኃው በጣም ይጮኽና ያስፈራ ነበር። ኩሉ ቢሆን ኖሮ በችኮላ ዘሎ ለመግባት ሲሞክር በውኃ ይወሰድ ነበር፤ ሊዮ ግን በትዕግስት ዙሪያውን ተመልክቶ የወደቀ ትልቅ እንጨት አገኘና በእርሱ ላይ ተረማምዶ ተሻገረ። ፍሬውን ቀጥፎ ሲመለስ ኩሉ ገና ከእንቅልፉ እየተነሳ ነበር። ኩሉ በድንጋጤ “እንዴ! አንተ እንዴት ቀደምከኝ? እኔ እኮ ካንተ እፈጥናለሁ!” ብሎ ጠየቀው። ሊዮም በፈገግታ እንዲህ አለው፦ “ኩሉ ሆይ፣ ፈጣን መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። ዋናው ቁምነገር ትዕግስት መያዝ፣ መንገድን ማስተዋል እና ሥራን ሳይሰለቹ እስከ መጨረሻው መግፋት ነው” አለው። ከዚያ ቀን ጀምሮ ኩሉ ዝንጀሮ መቸኮልን ትቶ ነገሮችን በትዕግስት መሥራትን ተማረ።

ሞክሩ

  1. እግሮች አሉት ግን አይራመድም፣ ምግብ ይቀርብበታል ግን አይበላም?
  2. ሁልጊዜ ወደ ላይ እንጂ ወደ ታች የማይሄደው ምንድን ነው?
  3. ጥርሶች አሉት ግን አይነክስም?

 

መልስ

  1. ጠረጴዛ
  2. እድሜህ/ሽ
  3. ማበጠሪያ

ነገር በምሳሌ

-”ከቆመ ይልቅ የሄደ ያገኛል”

– ዝም ብሎ ከመቀመጥ ይልቅ ጥረት የሚያደርግና የሚንቀሳቀስ ሰው ውጤታማ ይሆናል።

-”ዝምታ ወርቅ ነው”-ሳያስቡ ከመናገር ይልቅ ዝም ብሎ ማዳመጥና ማስተዋል ትልቅ ዋጋ አለው።

-”ዛሬ የምታነበው መጽሐፍ፣ ነገ ለምትሆንበት ማንነት መሰላል ነው!”-እውቀት ለወደፊት ህይወት ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ያሳያል፡፡

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here