የሺህ ምሰሶዎች ብርሐን

0
126

በመላው ዓለም ስር የሰደደ የማኅበረሰብ ኋላቀር አስተሳሰብ፣ ሴቶችን ያገለለ እና መብቶቻቸውን ያላከበረ አድሏዊ አመለካከት ለመከላከል ሴቶች ትግል የጀመሩት   ከ115 ዓመታት በፊት ነው:: በወቅቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል መሸከም አቅቷቸው አሠራሩን የተቃወሙ ሴቶች የእኩልነት መብታቸው እንዲከበርም ባልተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር።

መብታቸውን ለማስከበር ትግል የጀመሩ በሺዎች የሚቆጠሩ በልብስ ስፌት የተሰማሩ ሴት ሠራተኞች እ.አ.አ በየካቲት 1908 በኒውዮርክ ከተማ ያደረጉት እንቅስቃሴ ደግሞ በታሪክ ተጠቃሽ ነው፤ ሠራተኞቹ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በከተማዋ ውስጥ በመዘዋወር የሥራ ሁኔታቸው ማሻሻያ እንዲደረግበት በመጠየቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ ለተቃውሞ ወጡ::

ሴት ሠራተኞች በቀን ከ12 እስከ 14 ሰዓታት ሥራ ያሳልፉ ነበር:: ለዚህ አድካሚ ሥራም ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር  የጡረታ መብታቸው አይከበርም፤ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብትም አልነበራቸውም::

በወቅቱም በኒውዮርክ ከተማ የመብታቸውን መገፈፍ መቀበል ያልፈለጉ 15 ሺህ ሴቶች ለሥራቸው ተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ምቹ የሥራ ቦታ፣ ተገቢ የሥራ ሰዓት ማስተካከያ፣ በዋናነት ደግሞ መምረጥም ሆነ መመረጥ እንዲፈቀድላቸው አደባባይ ወጡ::

የሴቶች ትግል በቀጠለበት እ.ኤ.አ ነሐሴ 1910 ኮፐንሀገን ውስጥ ዓለም አቀፍ ሶሺያሊስቶች ሁለተኛ አጠቃላይ ኮንፈረንስ ተካሂዶ ነበር፤ ከዚህ ቀደም ብሎ የዓለም አቀፍ ሴት ሶሺያሊስቶች ኮንፈረንስ መደረጉ ደግሞ ለሴቶች ትግል መጠናከር ከፍተኛ ድርሻ ነበረው። በስብሰባውም በተወሰነ ደረጃ በአሜሪካ ሶሻሊስቶች በመነሳሳት ጀርመንን ወክለው ክላራ ዜትኪን፣ ካቴ ዱንከር፣ ፓውላ ታይዴ እና ሌሎችም ዓመታዊ የሴቶች ቀን እንዲወሰን ሀሳብ አቀረቡ።

በጉባኤ ላይ በተለይ ክላራ ዜትኪን የተባሉት ጀርመናዊት የሶሻሊስት አራማጅ ፖለቲከኛ በዓሉ በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ እንዲከበር ሀሳብ አቀረቡ:: በወቅቱም ከዐሥራ ሰባት ሀገራት የተውጣጡ አንድ መቶ ተሳታፊ ሴቶችም ሀሳቡን ተቀበሉ። ይህንንም ተከትሎ ኦስትርያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ በዓሉን በ1911 በማክበር ፈር ቀዳጅ ሆኑ።

የበዓሉን መከበር ተከትሎም ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በሩሲያ ሦስት አራት ቀናት ሲቀረው  የአበባ ስጦታ ይለዋወጣሉ:: በቻይና ደግሞ በመንግሥት አስተዳደር በመፈቀዱ አብዛኛው ሴቶች የግማሽ ቀን እረፍት ያገኛሉ::  ጣሊያንም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ሴቶች ምሞሳ የተሰኘውን በቢጫና ሮዝ ቀለማት ያሸበረቀ አበባ በገፀ በረከትነት ያገኛሉ። በአሜሪካ ደግሞ መጋቢት ወር በሙሉ  “የሴቶች ታሪካዊ ወር”  የሚል ዕውቅና ተሰጥቶታል።  የፕሬዝዳንቱ ቢሮም ለሴቶች ስኬትና ድል በየዓመቱ ዕውቅና ይሰጣል።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሴት ደራሲያን የተፃፉ መጻሕፍትን ስጦታ በማበርከት፣ ስለ ሴቶች መብት እና የፆታ እኩልነት በማስተማር፣ የሚወዷቸውን በሴቶች የተዘጋጁ  ፊልሞችን በመመልከት እና በሌሎችም ሴቶችን በሚያበረታቱ ተግባራት እንደሚከበር ከቢቢሲ እና ከሂስትሪ ዶት ኮም የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል::

እ.አ.አ በ1908 መብታቸውን ለማስከበር አደባባይ የውጡ ሴቶች ለዛሬዎቹ መንገድ በማሳየት መሰረት የጣሉ ተምሳሌቶች ስለመሆናቸው ታሪክ ይዘክራቸዋል:: ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዘንድሮም በዓለም ለ115ኛ፤ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ “የ50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለፀገች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ አካባቢዎች በመከበር ላይ ነው:: በዓሉንም ከ100 ዓመት በፊት ለሴቶች መብት መከበር  ፋና ወጊ የነበሩ ሴቶችን ከመዘከር ባሻገር የእነርሱን ፈለግ ማስቀጠል በተለያዩ ተግባራት ሲከበራ ቆይቷል::

በአማራ ክልልም  የክልሉ ሴቶች ፣ ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዓሉን አስመልክቶ ከሕዝብ ግንኙነት፣ ከመገናኛ ብዙኃን  መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት ተደርጓል:: በውይይቱም ቀደምት ለመብታቸው የታገሉ ሴቶች በዓሉ በመላው አለም እንዲከበር ማድረጋቸው አሁን ላይ መሰረት ሆኖ ለውጥ ማምጣቱን ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::   ለአብነት በክልሉ ባሉ ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ሥር  ካሉት 22 መምሪያዎች  የ15ቱ ኃላፊዎች ሴቶች መሆናቸው ተጠቁሟል::

ሴቶች ታማኝ፣ ቅን፣ ጠንካራ…ስለመሆናቸውም የውይየቱ ተሳታፊዎች ምስልርነታቸውን ሰጥተዋል:: ይህ ውጤትም የ50 ዓመታት የዓለም አቀፉ ጉዞ፣ ቀደምቶቹ የጣሉት መሰረት ውጤት እንደሆነ ተሳታፊዎቹ አስተያየት ሰጥተዋል::

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው  በየዓመቱ የሚከበረው  ዓለም ዓቀፉ የሴቶች ቀን  ዘንድሮ ከአዳራሽ ውጭ እንደሚከበር ጠቁመዋል:: ኃላፊዋ እንዳብራሩቱ በዕለቱ በየደረጃው የሚገኙ ሴት የከፍተኛ ተቋማት ምሁራን በተለያዩ መስኮች ሴቶች ያከናወኑትን ሥራ በአካል ተገኝተው ይጎበኛሉ:: ከጉብኝታቸው በኋላም መልካም ተሞክሮዎች እንዲሰፉ፣ ጉድለታቸውን የሚሞላ ድጋፍ እንዲያደርጉ ይጠበቃል:: በክልሉ የተገነቡ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለሴቶች የፈጠሩትን የሥራ እድል መገምገም የበዓሉ አንዱ ተግባር ነው::

እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለጻ በአሉን ምክንያት በማድረግ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ያመረቷቸው በባሕር ዳር፣ ደብረ ብርሐን፣ ወልድያ እና ጎንደር ከተሞች በተዘጋጀው  ኤግዚቢሽን እና ባዛር አቅርበዋል:: ከዚህ ባሻገር የገበያ ትስስርም ይፈጠርላቸዋል:: በሀገሪቱ ሰ51 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሴቶች የልማት እና የቁጠባ ባህላቸውን በማጠናከር የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድም  መመቻቸቱን ወ/ሮ ብርቱካን አስገንዝበዋል::

በቀጣይ በሴቶች የተከናወኑ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት፣ የሴቶችን ግንዛቤ የሚያሳድጉ መረጃዎችን በማጋራት መገናኛ ብዙኃን የድርሻቸውን እንዲወጡ ቢሮ ኃላፊዋ ጠይቀዋል::

ማናት

ክላራ ዜትኪን

ክላራ በሌፕዚግ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላ በጀርመን  ከሙኒስት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተሳታፊ ነበሩ:: ለሴቶች መብት መከበር ያደረጉት ከፍተኛ ትግል ደግሞ ስማቸው ዛሬም ድረስ እንዲታወስ አድርጓል::

ክላራ በሌፕዚግ የሴቶች የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ከሩሲያ አብዮተኛ ጋር በጀመሩት ፍቅርና ትዳር ምክንያት ሀገር ጥለው ተሰደዋል:: በሲዊዘርላንድና ፓሪስ በነበራቸው የስደት ጊዜ ከበርካታ ዓለም አቀፍ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አራማጆች ጋር የመገናኘት እድል አግኝተዋል::

ወደ ጀርመን በመመለስ የአንድ የሶሻሊስት ጋዜጣ አርታኢ ሆነው አገልግለዋል፤ እ.ኤ.አ በ1907 ዓለም አቀፉን የሶሻሊስት ሴቶችን ጉባኤ ከሌሎች አጋሮቿ ጋር በመሆን አቋቁመዋል::

የሌኒን ጓደኛ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ክላራ የአንደኛውን የዓለም ጦርነት በመቃወም ሴቶችን አስተባብረው እ.ኤ.አ በ1915 በበርን ዓለም ፈቀፍ ውይይት አካሂደዋል፤ እ.ኤ.አ በ1919 ደግሞ የጀርመን ኮሙኒስት ፓርቲን ተቀላቅለዋል:: የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በመሆንም አገልግለዋል::

የሴቶችን መብት መከበር አስመልክቶ በርካታ ንግግሮችን አሰምተዋል፤ በንግግራቸውም ለውስን መብቶች ከመጮህ ይልቅ የሴቶችን መብት ተጭኖ የያዘው የካፒታሊዝም ሥርዓት እንዲወድቅ መሰራት እንደሚገባ ሰብካዋል::

በሚያደርጉት  ትግልም መጠነኛ ለውጦችን በራሳቸው ዘመን ማጣጣም ችለዋል:: እ.ኤ.አ በ1908 በጀርመን ሴቶች መምረጥ እንዲችሉ አድርገገዋል፤ በመጀመሪያው የሴቶች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይም የዓለም አቀፍ የሴቶች ቢሮ ዋና ፀሀፊ ሆነው አገልግለዋል::

እ.ኤ.አ ከ1921 በኋላ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት በሞስኮ ነበር፤ ከሦስት ዓመታት በኋላ ሌኒን መሞቱን ተከትሎ የክላራ እንቅስቃሴ እየቀነሰ መጣ፤ ተፅዕኗቸውም እየቀነሰ ሄደ:: በዘመናቸው የፃፏቸው ጽሑፎች ተሰባስበው በሦስት ተከታታይ ቅፅ ታትመዋል::

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here