የአማራ ክልል ግብርናን ከባህላዊው ማረሻ ሞፈር እና ቀንበር አላቆ ወደ ኢንዱስትሪ ማገርነት ለመለወጥ የተቀረጸው የ25 ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ፣ የክልሉን ምጣኔ ሀብት የሚቀይር ግዙፍ የሽግግር ዕቅድ ስለመሆኑ ታምኖበት በሥራ ላይ ይገኛል:: ይህ ዕቅድ በዋናነት የመስኖ አብዮትን፣ የግብርና ክላስተርን እና ሜካናይዜሽንን እንደ መውጫ መንገድ በመጠቀም አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ ለማምረት ከሚያስችለው ዝናብ ጠባቂነት ወጥቶ ሦስት ጊዜ እንዲያመርት የሚያስችል እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል:: በተለይም በትራክተር እና በዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዘ የንግድ ተኮር ግብርናን ዕውን ለማድረግ የተዘረጋው የብድር አቅርቦት ሥርዓት ለዘመናት የቆየውን የሰው ጉልበት ጥገኝነት በቴክኖሎጂ ለመተካት የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ታምኖበታልል::
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በባህላዊ የምርት አያያዝ 30 በመቶ የምርት ብክነት ይከሰታል:: ዘመናዊ መውቂያ ማሽኖችን በመጠቀም ደግሞ ብክነቱን ወደ አምስት በመቶ ዝቅ ማድረግ ይቻላል:: ይህም ለምግብ ዋስትና እና ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝ ግብዓት ለማቅረብ ወሳኝ ነው::
የዕቅዱ ዋነኛ ምሰሶ የግብርና ክላስተር ልማት ሲሆን ይህም አርሶ አደሮች በተበታተነ ማሳ ላይ ከማምረት ወጥተው ተመሳሳይ ሰብሎችን በጋራ እና በስፋት እንዲያለሙ የሚያስችል ነው። በተጨማሪም እንደ ትራክተር እና ምርጥ ዘር ያሉ ግብዓቶችን በጋራ ለመጠቀም ያግዛል::
አርሶ አደሮች ማሳቸውን በወቅቱ በማለስለስ፣ የግብርና ግብዓቶችን በጊዜው በመውሰድ እና የባለሙያ ምክርን በተግባር በመተርጎም ለስኬታማ የመኸር ወቅት ዝግጅት እንዲያደርጉ ይጠበቃል:: ይህ የተቀናጀ ጥረት ግብርናውን ከባህላዊ አሠራር በማውጣት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስችላላል::
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሶሊበን ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ቤዛ ዓለሙ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል:: ዘንድሮም ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በትራክተር አሳርሰዋል። በትራክተር ማረስ የሰብል ተባይን ለመቀነስ፣ ማሳውን በቀላሉ ለማለስለስ እና ምርታማነትን ለመጨመር እንዳገዣቸው አረጋግጠዋል:: ቴክኖሎጂው የአርሶ አደሮችን ጉልበት ይታደጋል፤ ጊዜ ቆጣቢ ነው፤ ከአንድ የእርሻ ማሳ የሚያገኙት ምርት በእጥፍ እንዲጨምር በማድረግ የኑሮ ደረጃቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸውም ነው የተናገሩት::
የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ማግኘት ጥላሁን በበኩላቸው ለ2018/19 የምርት ዘመን የእርሻ ሥራቸውን ቀድመው በመጀመር እና ለግብዓት መግዣ የሚሆን ገንዘብ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል:: ባለፈው ዓመት ካላቸው አራት ሄክታር መሬት ውስጥ በሁለቱ ላይ ብቻ 35 ኩንታል ዳጉሳ እና 60 ኩንታል በቆሎ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ቀድሞ እርሻ መጀመር የሰብል ተባይን ለመቀነስ እና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል::
በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ “ከበሬ እርሻ በመላቀቅ ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽን አሠራርን በመከተል ምርታማነትን እንጨምር!” በሚል መሪ ቃል የትራክተር ሜካናይዜሽን ፌስቲቫል ተካሂዷል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስማረ አንዳርጋቸው በዚህ ወቅት እንደገለጹት ወረዳው ሰፊ ለም የሚታረስ መሬት ያለው በመሆኑ ይህንን ጸጋ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ውጤታማነትን ማረጋገጥ ይገባል። ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያም የመለዋወጫ አቅርቦት ችግሮችን በቅርበት በመከታተል እና በመወያየት ለመፍታት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ከወረዳው ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው እንደገለጹት፣ ለ2018/19 የምርት ዘመን አርሶ አደሮች ትራክተር ተጠቅመው ምርታማነትን እንዲያሳድጉ ለማድረግ በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች 100 ትራክተሮችን ገዝቶ ለማሰራጨት ታቅዷል። በአስተዳደሩ በመኸር እርሻ ከሚሸፈነው 408 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 265 ሺህ ሄክታር የሚሆነውን በትራክተር ለማሳረስ ግብ ተቀምጧል። ይህ የሜካናይዜሽን ስምሪት ጊዜን፣ ጉልበትን እና ወጪን የሚቆጥብ በመሆኑ አርሶ አደሮች ወደ በጋ እርሻም እንዲገቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው ግብርናውን ከኋላ ቀር የበሬ እርሻ በማላቀቅ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ሜካናይዜሽን ጊዜን እና የሰው ኀይልን ከመቆጠብ ባለፈ፣ የእርሻ ሥራ ጥራትን በማሻሻል እና የምርት ብክነትን በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው:: አንድ ትራክተር ብቻ በቀን ከአምስት ሄክታር በላይ የማረስ አቅም እንዳለውም አረጋግጠዋል::
እንደ አቶ አጀበ ማብራሪያ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሁለት ሺህ 726 ትራክተሮች ይገኛሉ:: ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ስድስት መቶ 19 ትራክተሮች፣ 10 ኮምባይነሮች፣ ከአምስት መቶ 55 በላይ የበቆሎ መፈልፈያዎች፣ ስድስት መቶ 12 ትሬሸሮች እና ከስድስት ሺህ በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች ለአርሶ አደሮች ተሰራጭተዋል። ይህ አቅርቦት ግብርናው ከኑሮ ደጋፊነት ባለፈ ከተረጅነት ለመላቀቅ፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ እና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ነው። በተለይም በምዕራብ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም እንዲሁም ሰሜን ሸዋ ዞኖች የተሻለ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ እንዳላቸው አቶ አጀበ ጠቁመዋል።
አነስተኛ መሬት ያላቸውን አርሶ አደሮች በክላስተር የማደራጀት ስልት ደግሞ አርሶ አደሩ እንደ ትራክተር እና ኮምባይነር ያሉ ማሽኖችን በጋራ እንዲጠቀም ዕድል እንደፈጠረለት ነው አቶ አጀበ የተናገሩት:: በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ እርሻ እየለማ ይገኛል::
በሌላ በኩል ደግሞ ቢሮው ለ2018/19 የምርት ዘመን አስፈላጊውን ግብዓት የማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው:: በዚህም በበጀት ዓመቱ ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆነው ወደ ክልሉ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አቶ አጀበ ጠቁመዋል:: በአሁኑ ወቅት ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በዩኒየኖች እጅ መድረሱም ተጠቁሟል። በምርጥ ዘር አቅርቦት ረገድም ከታቀደው 230 ሺህ ኩንታል ውስጥ 131 ሺህ ኩንታሉን የማባዛት እና የመሰብሰብ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በተለይም በምዕራብ አማራ አካባቢዎች የመኸር እርሻ የተጀመረ ሲሆን በክልል ደረጃም ከአምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለመሸፈን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው::
የአማራ ክልል ፕላን ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) የክልሉን ግብርና መዋቅራዊ ሽግግር አስመልክቶ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግብርና አሁንም 66 በመቶ የሥራ ስምሪት ድርሻ ቢኖረውም ከባህላዊው የሞፈርና ቀንበር አስተራረስ እንዳልወጣ ተናግረዋል:: ግብርናው በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ 52 በመቶ ድርሻ ቢኖረውም አሁንም እውቀትን ሳይሆን ጉልበትን የሚጠይቅ በመሆኑ የተማረውን የሰው ኀይል እና ሴቶችን ያገለለ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል። ግብርናው በማሽነሪ የታገዘ እና እውቀት ተኮር ቢሆን ግን ሴቶች በምርት ሂደቱ ውስጥ በስፋት እንዲሳተፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ እና ምርታማነትን በሄክታር፣ በመሬት እና በነፍስ ወከፍ ለማረጋገጥ ኮሜርሻል (ንግድ ተኮር) ግብርና እና የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴዎች እንደ ዋና መፍትሔ ተቀምጠዋል። በስትራቴጂው መሠረት ከ25 ዓመታት በኋላ የክልሉ የግብርና ምርታማነት በሄክታር 69 ኩንታል ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም የሀገር ውስጥ እና የውጭ የግል ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ የብድር እና ሥልጠና ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፣ የግል ባለሀብቶች በማይገቡባቸው ዘርፎች ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በአስገዳጅነት ገብተው እንዲያለሙ ይደረጋል ነው ያሉት። በተጨማሪም አርሶ አደሮች ወደ ባለሀብትነት እንዲያድጉ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን በሙያ ቅያሪ እና ወደ ከተማ በሚገባው ሕዝብ ምክንያት በአንድ ሰው የነበረው የማሳ መጠን ከ0.78 ወደ 2.1 ሄክታር ያድጋል ተብሎ ታቅዷል።
አሁን ያለው የእርሻ ይዞታ ሳይቀየር ኩታ ገጠም አሠራርን መተግበር ሌላኛው የዘመናዊ እርሻ አማራጭ መሆኑን ዶ/ር ደመቀ ገልጸዋል። ይህ አሠራር በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ተመሳሳይ ሰብሎች በስፋት እንዲመረቱ ዕድል የሚሰጥ፣ አርሶ አደሩን ለማሠልጠን እና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በር የሚከፍት መሆኑንም ጠቁመዋል:: በዚህም የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል። ለእነዚህ ዕቅዶች ስኬታማነት በርካታ የማስፈጸሚያ ስልቶች ተቀምጠዋል። የኤክስቴንሽን ሥራን ማስተካከል፣ የግብዓት አቅርቦትን በጥናት ማሻሻል፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ የተማረ የሰው ኀይል መመደብ እና የቴክኖሎጂ ጥገና አገልግሎትን በቅርበት ማመቻቸት ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪ የምርምር ተቋማትን ማጠናከር፣ የገበያ ትስስርን ማሳለጥና ለባለሀብቶች የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት ግብርናውን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት ግቡን እንዲመታ የሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት መሆናቸው ተመልክቷል።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


