ከሰሞኑ እንደ አዲስ በፈነዳው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ዓለማችን ከፍተኛ ስጋት ላይ ትገኛለች:: ጦርነቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው:: የአየር እና የሚሳኤል ጥቃቶች እንዲሁም በተወካይ ኃይሎች (ሄዝቦላሕ፣ ሃውቲ) በኩል የሚካሄዱ በመሆናቸው ክልሉን ወደ ሰፊ ግጭት እየመሩት ነው::
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ በጥቃቱ ተገድለዋል:: በምላሹም ኢራን በበርካታ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ላይ ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ትልቅ ውርጅብኝ አካሂዳለች::
የኢራን ኒውክሊየር ፕሮግራም፣ በክልሉ ውስጥ የምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች እና የእስራኤል ደኅንነት ጉዳይ ዋና የግጭቱ መነሻ ምክንያቶች ናቸው:: አሜሪካ ደግሞ እንደ እስራኤል ቅርብ አጋር በፖለቲካዊ እና በወታደራዊ ድጋፍ ተሳትፎ እያደረገች ነው:: ይህ ሁኔታ ክልሉን በቀላሉ ሊነድ የሚችል የጭድ ክምር አድርጎታል::
እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ በቀጣናው (በጋዛ ሰርጥ) በፊትም ቢሆን እስራኤል እና ሐማስ ባደረጉት ጦርነት በዐሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል:: ሕፃናትና ሴቶች ዋነኛ የጉዳቱ ሰለባዎች ናቸው:: በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም ከቤታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖራሉ:: የምግብ፣ የውኃ እና የመድኃኒት እጥረቱም ከባድ ነው::
በሊባኖስ ውስጥ ደግሞ በሔዝቦላህ እና እስራኤል መካከል የሚካሄዱ ግጭቶች የክልሉን አደጋ አባብሰውት ቆይተዋል:: በሶሪያ ውስጥም የተለያዩ የአየር ጥቃቶች ተመዝግበዋል:: ታዲያ ይህ ሁሉ ቀውስ ሳይስተካከል ነበር ቀጣናው ወደ አዲስ ጦርነት ያመራው::
ይህ ግጭት በቀጣናው ብቻ አይቆምም:: የነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ የንግድ መንገዶች መዘጋት እና የፖለቲካ ውጥረት መጨመርን በማስከተል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅእኖ እያሳደረ ነው::
ተንታኞች እንደሚሉት ግጭቱ ከቀጠለ ወደ ሰፊ ክልላዊ ጦርነት ሊለወጥ ይችላል:: ነገር ግን ዲፕሎማሲ እና የዓለም ግፊት ከተጠናከረ ባለበት ሊቆም ይችላል::
በተደጋጋሚ እንደሚባለው በጦርነቱ ተጎጅ የሚሆኑት ንጹሃን እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም:: ይህ ቀውስ በአካባቢው ብቻ የሚቆይ አይደለም፤ ዓለም አቀፍ ደኅንነትን እና ኢኮኖሚውንም በቀጥታ የሚነካ ነው:: ንጹሃን ደግሞ የችግሩ ቀዳሚ ተጠቂ ናቸው::
ታሪካዊ ዳራ
የእስራኤል እና የኢራን የቀድሞ ግንኙነታቸው መጥፎ አልነበረም:: እስራኤል እ.አ.አ በ1948 ስትመሠረት ኢራን በዚያን ጊዜ በንጉሥ መሃመድ ሬዛ ፓህላቪ እየተመራች ነበር:: ግንኙነታቸውም መልካም የሚባል ነበር:: የንግድ እና የደኅንነት ትብብርም ነበራቸው:: በዚህም ኢራን ለእስራኤል ነዳጅ ትሸጥ ነበር::
ግንኙነታቸው መሻከር የጀመረው እ.አ.አ በ1979 የኢራን እስላማዊ አብዮት ከተካሄደ በኋላ ነው:: አብዮቱ ሁሉንም ነገር ቀየረው:: አዲሱ የእስላማዊ መንግሥቱ መሪ ሩሆላህ ኻሜኒ (Ruhollah Khamenei) እስራኤልን “ሕጋዊ ሀገር አይደለችም” ብሎ አወጀ:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢራን እና እስራኤል ጠላት ሆኑ::
ኢራን እስራኤልን የሚቃወሙ ቡድኖችን ማለትም በሊባኖስ ያለውን የሔዝቦላህ (Hezbollah) እና በጋዛ ያለውን ሐማስ (Hamas) ታጣቂ ቡድኖችን መደገፍ ጀመረች::
በተጨማሪም ኢራን የምታካሂደው የኒውክሌር ፕሮግራም ሁለቱ ሀገራት በአይነቁራኛ እንዲተያዩ አድርጓቸዋል:: እ.አ.አ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ እስከ ዛሬ ድረስ እስራኤል የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራምን እንደ ህልውና አደጋ ትመለከታለች:: ብዙ ጊዜ ሁለቱ ሀገራት በሶሪያ እና በሌሎች ሀገሮች በተዘዋዋሪ መንገድ ጦርነት (proxy war) አካሂደዋል::
ወቅታዊው ሁኔታ
አሜሪካና እስራኤል በኢራን ላይ ለሚያደርሱት የተቀናጀ ጥቃት በባሕረ ሰላጤው ሀገራት ውስጥ በሚገኙ የዋሺንግተን ወታደራዊ ይዞታዎችና ሌሎች ዒላማዎች ላይ የአጸፋ ጥቃት እየፈጸመች የምትገኘው ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን ዘግታለች:: የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳስታወቀው “በዚህ ሰርጥ ለማለፍ የሚሞክር ማንኛውም መርከብ በእሳት ይጋያል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል:: የኢራን እርምጃ ዓለምአቀፍ የኢነርጂ አቅርቦትን አደጋ ላይ የጣለ ሲሆን በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ መናወጥን ሊፈጥር እንደሚችል ከወዲሁ ተሰግቷል::
የሰርጡ መዘጋት የዓለምን በተለይም የአፍሪካን ህልዉና አደጋ ላይ ይጥላል እየተባለ ነው:: በባሕር ሰርጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየቶችንም ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተገለጸው:: ይህም የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል::
የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር ይፋ ባደረገው መረጃ በሰርጡ በ2023 ብቻ በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳለፈ የሚገመት ሲሆን ይህም በዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይጓጓዛል ማለት ነው:: በሰርጡ ከዓለም ነዳጅ ዘይት 20 በመቶዉ እና ከፈሳሽ ጋዝ አንድ ሦስተኛው ይተላለፍበታል::
የኢራቅ የነዳጅ ሚኒስቴር በበኩሉ የሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ በመስተጓጎሉ እና ወደ ባሕረ ሰላጤው የሚገቡ የነዳጅ ማመላለሻ መርከቦች እጥረት በመኖሩ የድፍድፍ ዘይት ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲጨምር በማድረጉ ቁልፍ በሆነ የነዳጅ ማውጫ ውስጥ ምርትን እንደሚያቆም አስታውቋል::
የጀርመኑ ዶቼቨሌ እንደዘገበው አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ኢራን ጥቃቷን ወደ ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ማስፋቷን አውግዘዋል:: አሜሪካ እና እስራኤል በጋራ በኢራን ላይ የሚያካሂዱት ድብደባ ላይ ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል::
አልጀዚራ በበኩሉ ሩሲያ አሜሪካ እና እስራኤል የአረብ ሀገራትን ወደ ጦርነት ለመጎተት እየሞከሩ ነው ስትል ሁለቱን ሀገራት መውቀሷን ዘግቧል:: የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “አሜሪካ እና እስራኤል ሆነ ብለው ኢራንን በአንዳንድ የአረብ ሀገራት ዒላማዎች ላይ የበቀል ጥቃት እንድትፈጽም ቀስቅሰዋታል፤ ይህም በሰው እና በቁሳቁስ ላይ ጉዳት አድርሷል፤ ይህም ሩሲያን አሳዝኗል” ነው ያለው::
የአውስትራሊያው ኤቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው አንድ ሳምንት ባስቆጠረው ጦርነት ወደ 12 የሚጠጉ ሀገራት በግጭቱ ተጎድተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል:: እናም ጦርነቱ በመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ እየተስፋፋ ይገኛል:: የኔቶ የአየር መከላከያ ወደ አየር ክልሏ የሚያመራውን የኢራን ባለስቲክ ሚሳኤል ካወደመ በኋላ ተርኪዬም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በግጭቱ የተጠቃች የመጨረሻዋ ሀገር ሆናለች:: የሀገሪቱ ባለስልጣናት እንዳሉት ሚሳኤሉ የተጠለፈው የአሜሪካ አየር ኃይሎች ባሉበት በተርኪዬ ኢንሲርሊክ ቤዝ አቅራቢያ ነው:: የኔቶ ቃል አቀባይ አሊሰን ሃርት “ኢራን በተርኪዬ ላይ ያነጣጠረችውን ጥቃትን እናወግዛለን:: ኔቶ ተርኪዬን ጨምሮ ከሁሉም አጋሮች ጋር በፅናት ይቆማል” ሲሉ ተናግረዋል::
ኔቶ ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ድርድር እንዲያካሂዱ ሞክሮ ነበር አልተሳካም እንጂ:: ሁሉም ወገኖች ወደ ተጨማሪ ቀውስ ከሚመሩ እርምጃዎች እንዲቆጠቡም ተናግሯል::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር እንዳሉት እየተካሄደ ያለው ግጭት በክልሉ በሚገኙ የ12 ሀገራት ሲቪሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው:: በኢራን፣ ሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ በፍልስጤም ግዛት፣ በእስራኤል፣ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች (UAE)፣ በባህሬን፣ በኳታር፣ በኩዌት፣ በሳዑዲ አረቢያ እና በሌሎችም ሲቪሎች እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል::
ኃላፊው ሰላማዊ ዜጎች በየአካባቢው ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ጠቁመው ንጹሃን ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል:: ጥቃቶቹ መኖሪያ ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን እየመቱ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት::
በግጭቱ ምክንያት በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው ጉዳት በኢራን ከፍተኛው ነው ተብሏል:: መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የዜና ወኪል በግጭቱ እስካሁን ከ1ሺህ በላይ ንፁሀን ዜጎች መሞታቸውን ገምቷል:: ከሞቱት መካከል ቢያንስ 165 ያህሉ የተፈፀሙት በደቡባዊ ሚናብ ከተማ በሚገኝ የሴቶች ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት ነው ሲል ደግሞ የኢራን መንግሥት ሚዲያ ዘግቧል:: 77 ሰዎች ደግሞ በሊባኖስ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት ተገድለዋል:: የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ ከሊባኖስ ወደ ሶሪያ የሚሻገሩ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 10ሺህ 629 መድረሱን አሳውቋል::
የኢራንን መንግሥት ጠቅሶ ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ከ180 በላይ ሕጻናትን ጨምሮ በሀገሪቱ ከ1ሺህ በላይ ንፁሀን ዜጎች ተገድለዋል:: በአሜሪካ በኩል ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስድስት የአሜሪካ ወታደሮች ሲሞቱ በእስራኤል በኩል ደግሞ 11 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል:: የሚቀጥሉት ሳምንታት ድርጊቶች የክልሉን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ይሆናሉ::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


