የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የሰሜን ኢትዮጵያ ተራሮች በጠዋት ጸሀይ ሲገረጡ ዓለም በታሪኳ አይታው የማታውቀው ያልተመጣጠነ ፍልሚያ በአድዋ ተራሮች ስር ተዘጋጅቶ ነበር:: በወታደራዊ ሳይንስ ስሌት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አሸናፊው የታወቀ ነበር:: ጣሊያን አውሮፓውያን የደረሱበትን የጦር ሳይንስ (ሎጂስቲክስ) ዘመናዊ ትጥቆች፣ ጠመንጃዎችን እና መድፎችን ታጥቃ መጥታለች:: በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጦር አብዛኛው በባዶ እግሩ የዘመተ፣ ያረጀ ጠመንጃና ባህላዊ ጋሻ የያዘ ገበሬ ነበር::
ታዲያ በወታደራዊ ሳይንስ “የማይቻለው” ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ? ታዋቂው ጀርመናዊ ፈላስፋ ፍሬድሪክ ኒቼ አንድ የማይሞት አባባል አለው:: “የመኖር ምክንያቱን (‘ለምን’ን) ያወቀ ሰው፣ ማንኛውንም ፈተና (‘እንዴት’ን) መቋቋም ይችላል” የሚል:: የአድዋ ጦርነት የመሳሪያና የስልት ጦርነት አልነበረም፤ የ”ምክንያት” (የዓላማ) እና የስነ ልቦና ፍልሚያ እንጂ!
በስነ-ልቦና እና በአመራር ጥበብ ዙሪያ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነው ሳይመን ሲኔክ “Start With Why” (በምክንያት ጀምር) በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ታላላቅ ድሎች የሚመነጩት “ምን” ከማድረግ ወይም “እንዴት” ይደረጋል ከሚል ሳይሆን “ለምን” እንደምናደርገው ከማወቅ ነው ይላል::
የጣሊያን ወታደሮች ወደ አፍሪካ የመጡበት ዋና ምክንያት የቅኝ ግዛት ካርታን ማስፋት፣ ሀብት መዝረፍ እና የፖለቲካ ዝና ማትረፍ ነበር:: ይህ ምክንያት ለክብራቸው እንጂ ለህልውናቸው ወሳኝ አልነበረም::
ኢትዮጵያዊያን ወደ ጦርነቱ የገቡበት ምክንያት ግን የሞትና የሽረት ነበር። “ነጻነታችንን፣ ክብራችንን፣ መሬታችንን እና ቤተሰባችንን ላለማስደፈር” የሚል እጅግ ጠንካራ፣ ወደኋላ የማያስመልስ፣ እና ከራስ ጥቅም የዘለለ ነበራቸው::
ጆርጅ ፍሪትዝ ሃርዲንጅ በርክሌይ “The Campaign of Adowa and the Rise of Menelik” በተሰኘው የታሪክ መጽሐፉ ላይ የጣሊያን ጦር ከቴክኖሎጂ ልዕልናው ጋር በአንድ ቀን ጦርነት ሙት እና ቁስለኛ ሆኖ መደምሰሱ፤ ጦርነት በመሳሪያ ብቻ ሳይሆን ከጀርባው ባለው የሞራል አቅም እንደሚወሰን አረጋግጧል ብሎ ጽፏል:: ጠንካራ “ለምን” (ምክንያት) የሌለው ጦር ፈተና ሲበዛበት ቶሎ ይሰበራል::
በ1914 እ.ኤ.አ ሰር ኧርነስት ኢንዱራንስ የተሰኘችውን መርከብ ይዞ ወደ አንታርክቲካ ባደረገው የባህር ላይ ጉዞ መርከቡ በበረዶ ተሰበረች:: 28ቱ የባህር ላይ ተጓዦች በዓለም ላይ እጅግ ቀዝቃዛ በሆነው እና ምንም ምግብ በሌለበት በረዶ ላይ ለወራት ቆዩ:: እነዚህ ሰዎች በህይወት የተረፉት በ”እንዴት” (በመርከብ ቴክኖሎጂ) ሳይሆን በ”ለምን” ነበር:: ሻክልተን በሰዎቹ ውስጥ “በህይወት ወደ ቤተሰቦቻችን እንመለሳለን” የሚል ጠንካራ ዓላማ ስለዘራባቸው የማይቻለውን ብርድ እና ረሀብ ተቋቋሙ::
የኢትዮጵያ አርበኞችም ለወራት በባዶ እግራቸው አቋርጠውት የመጡት ርቀት፣ የምግብ እና የስንቅ እጥረት ያላቆማቸው የጉዟቸው ምክንያት (ነጻነት) ከድካማቸው ስለገዘፈ ነበር:: ቪክቶር ፍራንክል “ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ” በተባለው የስነ-ልቦና መጽሐፉ እንዳረጋገጠው ተስፋ እና ትርጉም ያለው ሰው አካላዊ ስቃይን የመቋቋም አቅሙ ከሌላው ሰው በብዙ እጥፍ ይበልጣል::
በ1954 ሙዛፈር ሸሪፍ የተባለ የስነ-ልቦና ባለሙያ ባደረገው ታዋቂ ጥናት እርስ በርስ የሚጠላሉ እና የሚጣሉ ቡድኖችን አንድ ለማድረግ መፍትሄው “የጋራ የላቀ ግብ” መስጠት እንደሆነ አረጋግጧል። አንድ ትልቅ የጋራ አደጋ ወይም አላማ ሲመጣ ትናንሽ ልዩነቶች ይረሳሉ::
ከአድዋ በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ በንጉሥ ተክለሃይማኖት፣ በራስ መንገሻ፣ በንጉሥ ሚካኤል እና በአጼ ምኒልክ መካከል የፖለቲካ ሽኩቻዎች ነበሩ:: ነገር ግን የሀገር ሉዓላዊነት የሚለው የላቀ ምክንያት ሲመጣ ሁሉም ኢጓቸውን (የኔ የሚሉትን) ጥለው ግጭታቸውን ረስተው በአንድ ዕዝ ስር ተሰለፉ:: የምክንያት ጉልበት ጠላትን ብቻ ሳይሆን የራስን ጦር ቁርሾም ያክማል!
የአድዋ ድል የታሪክ መጽሐፍ ላይ ብቻ ተዘግቶ የሚቀር ሳይሆን ዛሬ በእያንዳንዳችን የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ልንጠቀመው የሚገባ የሥነልቦና መሳሪያ ነው::
የዛሬው ጠላታችን ጣሊያን አይደለም። የዛሬው አድዋችን (ጦርነታችን) ድህነትን ማሸነፍ፣ መጥፎ ልማድን መስበር፣ ትምህርትን መጨረስ፣ ሱስን ማሸነፍ፣ ወይም ትልቅ ራዕይን ማሳካት ነው:: እኛም የራሳችንን አድዋ ለማሸነፍ ከአባቶቻችን ልንማራቸው የሚገቡ ብልሃቶች አሉ::
የኢትዮጵያ አርበኞች ዘመናዊ መሳሪያ የለንም፤ በቂ ስንቅ የለንም፤ መንገዱ ሩቅ ነው ብለው ሰበብ አልደረደሩም:: ማድረጊያ ምክንያታቸው ከሰበባቸው ገዝፎ ነበር:: እኛም “ካፒታል የለኝም፣ ጊዜ የለኝም፣ አልተማርኩም” የሚለውን ሰበብ ትተን የምንሰራበትን ትልቅ ምክንያት መፈለግ አለብን::
መጀመሪያ “ለምን” እንደምንሰራው ማወቅ ጥሩ ነው:: ጠንካራ ምክንያት ካለን መንገድ (እንዴት መድረስ እንዳለብህ) በሂደት ይከፈታል:: አባቶቻችን ጣሊያንን እንዴት እንደሚያሸንፉ ከመነሻው የውጊያ ቀመር አልነበራቸውም:: ለምን ማሸነፍ እንዳለባቸው ግን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር:: እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ የመጠጥ ውኃ ምንጩን በመያዝ የሰሩት የጦር ስልት የመነጨው እጅግ ጠንካራ ከሆነ የማሸነፍ ፍላጎት ነው::
ስኬት ለራስ ዝና እና ብር ማግኘት ብቻ ከሆነ፣ ትንሽ ፈተና ሲመጣ እንተወዋለን:: ነገር ግን ጥረታችን ቤተሰብህን ከድህነት ለማውጣት፣ ማህበረሰብህን ለመለወጥ ወይም ሀገር ለማሳደግ ከሆነ (ልክ አባቶቻችን ለኛ ብለው ደማቸውን እንዳፈሰሱት)፣ በውስጣችን የማይነጥፍ ሞተር ይፈጠራል::
አድዋ ታሪክ ብቻ አይደለም፤ አድዋ ሥነ-ልቦና ነው። አድዋ “የምክንያት ጉልበት” ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና ተራራን እንዴት እንደሚያንቀጠቅጥ የተረጋገጠበት ህያው የዓለም ቤተ-ሙከራ ነው::
“የአድዋ ጀግኖች ልጆች ነን!” ስንል፣ በስም እና በባንዲራ ብቻ ሳይሆን የነሱን የአእምሮ ጽናት እና የምክንያት ልዕልና በህይወታችን ስንተገብር ጭምር ነው:: መሳሪያ ሳይኖራቸው ነጻ ሀገር ላቆዩልን አባቶች ክብር ስንል፣ እኛ የተሟላ አቅም እያለን በሰበብ ተተብትበን ህልማችንን መቅበር የለብንም ማለት ነው::
ዛሬውኑ የህይወታችንን ጠንካራ ምክንያት እንፈልግ:: ከዚያም የራሳችንን አድዋ ያለ ሰበብ በድል እንወጣ::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


