ግብርናው ከእጅ ወደ አፍ እንዲሻገር የድርሻችንን እንወጣ!

0
115

ግብርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት ሲሆን 65% ኢትዮጵያዉያን ህይወታቸዉን እንደሚመሩበት የአረንጋዴ ትብብር በአፍሪካ ወይም አግራ የተሰኘዉ ተቋም ያወጣዉ ሪፖርት ያመላክታል። የአገሪቱን አንድ ሦስተኛ ጠቅላላ ምርትም እንደሚሸፍን የተቋሙ መረጃ ያሳያል፤ ቢሆንም ይህ ግዙፍ ዘርፍ አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ ከመባል ደረጃ አልተሻገረም።

የአማራ ክልል ሰፊ እና ለም የሚታረስ መሬት ያለው በመሆኑ ይህንን ጸጋ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ውጤታማነትን ማረጋገጥ ይገባል። ግብርናዉን ከባሕላዊው ማረሻ ፣ሞፈር እና ቀንበር አላቆ ወደ ኢንዱስትሪ መርነት መለወጥ ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ የ25 ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ፣ የክልሉን ምጣኔ ሀብት የሚቀይር ግዙፍ የሽግግር ዕቅድ ስለመሆኑ ታምኖበት በሥራ ላይ መዋሉ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነዉ፡፡

ግብርናውን ከኋላ ቀር የበሬ እርሻ በማላቀቅ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ የተሰጠዉ ትኩረት አበረታች ተግባር ነው፤ ይህንኑ ትኩረት ማስቀጠል ደግሞ የሁላችንም ድርሻ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እና ድጋፍ ልንሰጠዉ ይገባል።

የግብርናው ዘርፍ  በክልሉ ኢኮኖሚ ውስጥ 52 በመቶ ድርሻ እንዳለዉ ቢታወቅም ዛሬም ድረስ ዕውቀትን ሳይሆን ጉልበትን የሚጠይቅ በመሆኑ የተማረውን የሰው ኀይል እና ሴቶችን ያገለለ ሆኖ መቆየቱን የክልሉ ፕላን ቢሮ መረጃ ጠቁመዋል። ይህንን የተማረ እና ሴቶችን ያላማከለ ዘርፍ ለሁሉም ያመች ዘንድ ግብርናው በማሽነሪ የታገዘ እና ዕውቀት ተኮር እንዲሆን፣ ሴቶችም በምርት ሂደቱ ውስጥ በስፋት እንዲሳተፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ዘመናዊ የግብርና አሠራሮችን መከተል እና መተግበር ለነገ የማይባል ቁልፍ ተግባር ነዉ።

የክልሉን ግብርና ከባሕላዊው ማረሻ፣ ሞፈር እና ቀንበር አላቆ ወደ ኢንዱስትሪ መርነት ለመለወጥ የተቀረጸው የ25 ዓመቱ ስትራቴጂካዊ ፍኖተ ካርታ፣ የክልሉን ምጣኔ ሀብት የሚቀይር ግዙፍ የሽግግር ዕቅድ ነው፤ ለተግባራዊነቱም የሁሉንም ሴክተር ድጋፍ እና ትብብርን የሚፈልግ በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን እንወጣ።

ለግብርናዉ ስኬታማነት የመስኖ አቢዮትን፣ የግብርና ክላስተርን (ኩታ ገጠም አመራረትን) እና ሜካናይዜሽንን እንደ መውጫ መንገድ በመጠቀም አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት እና ከዝናብ ጠባቂነት ወጥቶ ሦስት ጊዜ እንዲያመርት የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።  አርሶ አደሩ በትራክተር እና በዘመናዊ መሣሪያዎች የታገዘ የንግድ ተኮር ግብርናን ዕውን ለማድረግ ያግዘዉ ዘንድ የብድር አቅርቦት ሥርዓትን ማዘመን፣ ለዘመናት የቆየውን የሰው ጉልበትን በቴክኖሎጂ መተካት እና አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሟላት ልዩ ትኩረትን የሚፈልጉ ዐበይት ተግባራት ናቸው፡፡

ከዚህ ባሻገርም አርሶ አደሩ ዘመናዊ መውቂያ ማሽኖችን እንዲጠቀም በማድረግ የምርት ብክነትን እንዲቀንስ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝ ግብዓት ለማቅረብ ያስችል ዘንድ  አርሶ አደሮች በተበታተነ ማሳ ላይ ከማምረት ወጥተው ተመሳሳይ ሰብሎችን በጋራ እና በስፋት እንዲያለሙ  እንደ ትራክተር እና ምርጥ ዘር ያሉ ግብዓቶችን በጋራ እንዲጠቀሙ ማገዝ ይገባል። ይህ የተቀናጀ ጥረትም ግብርናውን ከባሕላዊ አሠራር በማውጣት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስችላል፡፡

ግብርናዉን ለማዘመን እና ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ በቂ የሰው ኀይል መመደብ፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂን ማቅረብ፣ የምርምር ተቋማትን ማጠናከር፣ የገበያ ትስስርን ማሳለጥና ለባለሀብቶች የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት ግብርናውን ለማዘመን የሚደረገውን ጥረት ግቡን እንዲመታ የሚያስችሉ ቁልፍ ተግባራት ናቸዉና ለተግባራዊነቱ እንረባረብ።

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here