ይህ ነው ምኞቴ…

0
144

ይህ ነው ምኞቴ እኔ በሕይወቴ፣

ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ…

ይህ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ጊዜ ሲቀነቀን የነበረ ሀገራዊ መዝሙር ነው፡፡

የካራማራ ጦርነት ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ኃይል እንዳትደፈር የታላቅ ጀግንነት ገድል የተጻፈመበት እና እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት የተከፈለበት የታሪክ ምዕራፍ ነው። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከሐምሌ 1969 እስከ መጋቢት 1970 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ባካሄዱት በዚህ አስከፊ ጦርነት በግምት ከ60 ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ የምስራቅ ጦር ግንባሮች ሀገራቸውን ለማዳን ሲሉ ተሰውተዋል። ይህ ታላቅ ድል በወቅቱ የነበረውን የኃይል ሚዛን በመቀልበስ የሀገርን አንድነት ያስጠበቀ በመሆኑ የታሪክ ባለሙያዎች እና እንደ ዳዊት አስታጥቄ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ድሉ በመንግሥት ደረጃ እንደ አድዋ ሁሉ ታላቅ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ሊከበር እንደሚገባው በአጽንኦት ያሳስባሉ።

የካራማራ ጦርነት መንስኤ ጥንታዊ መሰረት ያለው ሲሆን በተለይም በ1952 ዓ.ም የጣሊያን እና የእንግሊዝ ሶማሊላንድ ግዛቶች ነጻነታቸውን ካገኙ በኋላ የተፈጠረው “ታላቋን ሶማሊያ” የመመሥረት ህልም ዋነኛው መነሻ ነበር። የሶማሊያ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ የያዟቸውን የሶማሊኛ ተናጋሪ ግዛቶች በሙሉ በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብ በማቀድ የይገባኛል ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ። ይህ ምኞት የኦጋዴን ቆላማ ምድርን ብቻ ሳይሆን እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ያሉትን የሀረርጌ፣ የባሌ፣ የሲዳሞ እና የአርሲ ክፍለ ሀገራትን የሚያጠቃልል ነበር። ከግዛት ማስፋፋት ባለፈም የዋቤና የገናሌ ወንዞችን መነሻ የሆኑትን ደጋማ ቦታዎች በመቆጣጠር ለሶማሊያ ግብርና እና መጠጥ ውሃ አስተማማኝ ዋስትና ለማግኘት የታለመ ስትራቴጂካዊ ወረራ ነበር ሲል አፈንዲ ሙተቂ “የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጦርነት” በሚለው መጽሐፉ ያስረዳል፡፡

ጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ በ1962 ዓ.ም በመንፈቅለ መንግሥት ስልጣን ከያዙ በኋላ ሶማሊያ ከሶቪየት ህብረት ጋር በፈጠረችው ወታደራዊ ወዳጅነት እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን በገፍ የታጠቀ ግዙፍ ሰራዊት መገንባት ቻለች። ወረራው በይፋ ከመጀመሩ በፊት የምዕራብ ሶማሊ ነጻ አውጪ ግንባር (ም.ሶ.ነ.ግ) እና የሶማሊ አቦ ነጻነት ግንባር (ሶ.አ.ነ.ግ) ሸማቂዎችን በማስቀደም በደጋማው የሀረርጌና የባሌ ክፍለ ሀገራት ሰርጎ የመግባት ስራ ተሰርቶ ነበር። በወቅቱ ኢትዮጵያ በውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ እና በከተሞች ይካሄድ በነበረው የነጭና የቀይ ሽብር ግጭት ተዳክማ በነበረበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በሐምሌ 15 ቀን 1969 ዓ.ም ሰራዊታቸው በሙሉ ኃይሉ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጡ።

በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረው የኃይል ሚዛን እጅግ የተራራቀ ነበር። ሶማሊያ በዘመናዊ ታንኮች፣ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና በቢ.ኤም ሮኬቶች በላቀ ደረጃ ተደራጅታ በነበረችበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የነበራት ትጥቅ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ያገለገሉ አሮጌ መሳሪያዎች ነበሩ። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገውን የታሪካዊ የእናት ሀገር ጥሪ ተከትሎ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀትና ልጆቹን ለጦርነት በመላክ በአንድነት ቆመ። በ”ታጠቅ” ማሰልጠኛ የሰለጠኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሚሊሻ ሰራዊት አባላት ከመደበኛው ጦር ጋር በመቀላቀል ወደ ምስራቅ ግንባር በመዝመት ተወዳዳሪ የሌለው ጀግንነት አሳይተዋል።

ወሳኙ የካራማራ ድል የተመዘገበው የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ሲሆን ይህ ስፍራ ከሀርጌሳ የሚነሳን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል እጅግ ስትራቴጂካዊ ተራራማ ቦታ ነው። በጀነራል እሸቱ መኮንን፣ በኃይሌ ተስፋ ሚካኤል እና በሌሎች ጀግና አዛዦች ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ ከሶቪየት ህብረት በተገኙ አዳዲስ መሳሪያዎችና በኩባ ወታደሮች ድጋፍ የታገዘ ጥቃት በመሰንዘር ወራሪውን የዚያድ ባሬ ጦር ዳግመኛ እንዳያንሰራራ አድርጎ ቀጥቅጦታል። ይህ ድል ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ ለሀገራቸው ሉዓላዊነት የቆሙበት ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ በመሆኑ ትውልዱ የጀግኖቹን አባቶቹን ውለታ በማስታወስ ታሪኩን ሊዘክረውና ሊያከብረው ይገባል።

በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የታየው የዲፕሎማሲ ሽግግር እና ወታደራዊ ስልት ጦርነቱን ከመቀልበስ ባለፈ የዓለም አቀፍ ኃይሎችን አሰላለፍ የቀየረ ክስተት ነበር። ሶማሊያ ወረራውን በጀመረችበት ወቅት በምስራቁ ጎራ (ሶቪየት ህብረት) ከፍተኛ ድጋፍ የነበራት ቢሆንም ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም የዲፕሎማሲ አቅጣጫዋን ከአሜሪካ ወደ ሶቪየት ህብረት በማዞር የኃይል ሚዛኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀየር ችላለች።

ሊቀመንበር መንግሥቱ በየመን ከተደረገው ውይይት በኋላ ለመሳሪያ ጥየቃ ወደ ሶቪየት ህብረት ተጓዙ። ሆኖም የክሬምሊን መንግሥት በቀላሉ ፊት አልሰጣቸውም። ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው ምክንያት ሶቪየት ህብረት ከሶሻሊስቷ ሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ተራድኦ ስምምነት የነበራት መሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ሶቪየቶች በኢትዮጵያ በመካሄድ በነበረው ለውጥ ላይ ጥርጣሬ የነበራቸው መሆኑ ነው። በ1968 መጨረሻ ሊቀመንበር መንግሥቱ ወደ ቻይና በሚሥጥር ሲያመሩ ግን ያላሰቡት እድል ገጠማቸው። ቻይናም ለሁለት ክፍለ ጦር የሚበቃ ቀላል መሳሪያ በእርዳታ መልክ እንደሰጠች ጓድ ፍቅረሥላሴ አብዮቱ እና ትዝታዬ በሚለው መጽሃፋቸው ላይ አስፍረዋል። እንደ ቻይና ሁሉ ከሶቪየት መሪዎች ጋር የማይጣጣሙት የዩጎዝላቪያው መሪ ጆሲፍ ብሮዝ ቲቶም የኢትዮጵያ አርበኞች ከዩጉዝላቪያ ጓዶች ጋር የነበራቸውን የጋራ የትግል ወኔ በማስታወስ 70 አሜሪካ ሰራሽ ታንኮችንና እጅግ በርካታ ቀላል መሳሪያዎችን ከበቂ ጥይቶች ጋር አበረከቱ።

የሶቪየት ህብረት መሪዎች መጀመሪያ ላይ በሁለቱ የሶሻሊስት ሀገራት መካከል የነበረውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ቢሞክሩም፣ ዚያድ ባሬ የሰላም ጥሪውን ውድቅ በማድረጋቸው እና የሶቪየት አማካሪዎችን ከሀገራቸው በማባረራቸው ምክንያት ሞስኮ ሙሉ ድጋፏን ለኢትዮጵያ ለመስጠት ወሰነች። ይህ የዲፕሎማሲ ድል ኢትዮጵያ እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን T-54 እና T-55 ታንኮችን፣ የሚግ-21 እና ሚግ-23 ተዋጊ ጄቶችን እንዲሁም ታዋቂውን የቢ.ኤም (ካትዩሻ) ሮኬት መተኮሻዎችን እንድታገኝ በር ከፍቷል።

ከዲፕሎማሲው ጎን ለጎን የተከተለው ወታደራዊ ስልት እጅግ የተቀናጀና በዘመናዊ የጦር ጥበብ የተመራ ነበር። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ገና በጦርነቱ መጀመሪያ የሶማሊያን አየር ኃይል በመምታት የአየር የበላይነትን መቆጣጠሩ ለምድር ጦሩ ትልቅ መተማመንን ፈጥሯል። በተለይም በጄኔራል አርናልዶ ኦቾዋ የሚመራው የኩባ ወታደራዊ ግብረ ኃይል ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በመቀናጀት የፈጠሩት ስልት የሚደነቅ ነበር። በወቅቱ የተነደፈው ዋናው የጥቃት ስልት ሶማሊያ በከፍተኛ ጥበቃ በያዘችው የካራማራ ግንባር በኩል ፊት ለፊት መጋፈጥ ሳይሆን፣ በስተጀርባ በኩል በሄሊኮፕተሮች ታንኮችን እና ከባድ መሳሪያዎችን በማጓጓዝ ጠላትን ካልጠበቀበት አቅጣጫ መምታት ነበር። ይህ “የአየር ወለድ ታንክ ዘመቻ” ተብሎ የሚታወቀው ስልት የሶማሊያን ጦር ክፉኛ ግራ ያጋባና የመከላከያ መስመሩን እንዲበጣጠስ ያደረገ ወሳኝ እርምጃ ነበር።

የካራማራ ድል የተበሰረው ከላይ በተጠቀሱት የተቀናጁ ጥቃቶች ውጤት ነው። የኢትዮጵያ ጦር እና የኩባ ክፍለ ጦሮች በጅግጅጋ እና በካራማራ ተራራ ላይ የነበረውን የጠላት ምሽግ በከባድ መሳሪያዎችና በአየር ድብደባ ካዳከሙ በኋላ እግረኛው እና ሜካናይዝድ ጦሩ በከፍተኛ ወኔ በመንቀሳቀስ ስልታዊ ቦታዎቹን ተቆጣጥሯል። የሶማሊያ ጦር በደረሰበት ከፍተኛ ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት መሣሪያዎቹን እና ቁሳቁሶቹን ጥሎ ወደ ድንበር ለመሸሽ ተገዷል። ይህ የካራማራ ድል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማረጋገጡም በላይ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ወታደራዊ ሳይንስ ተቀናጅተው እንዴት ታላቅ ውጤት እንደሚያመጡ ለትውልድ ትልቅ ትምህርት ጥሎ አልፏል።

 

ሳምንቱ በታሪክ

የዮሐንስ 4ኛ መስዋዕትነት

የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ መስዋዕትነት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ልብ የሚነካ እና የጀግንነት ጥግ የታየበት ክስተት ነው። ንጉሡ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም በመተማ ጦርነት ላይ ለሀገራቸው ሲሉ ሕይወታቸውን የሰጡት በከፍተኛ ወኔ እና ለአገር በመቆርቆር ነበር።

በወቅቱ የሱዳን መሃዲስት ጦር (ደርቡሾች) በኢትዮጵያ በኩል ወረራ ፈጽመው ጎንደርን አቃጥለውና ጥፋት አድርሰው ነበር። አፄ ዮሐንስ ይህን የጠላት ድፍረት ለመመከት እና ሀገሪቱን ከወረራ ለማዳን ግዙፍ ሰራዊት አስከትለው ወደ መተማ ዘመቱ። ጦርነቱ መጋቢት 1 ቀን ሲጀመር የኢትዮጵያ ሰራዊት እጅግ በላቀ ሁኔታ ጠላትን እያሸነፈና ድል እየቀናው ነበር።

ንጉሡ እንደ ተራ ወታደር በጦርነቱ ግንባር ቀደም ሆነው እየተዋጉ ሳለ፣ ድል ሊቀናቸው ጥቂት ሲቀረው በጠላት ጥይት ክፉኛ ቆሰሉ። በወቅቱ የነበረው የታሪክ ዘገባ እንደሚያሳየው፣ ንጉሡ መቁሰላቸውን ለሰራዊቱ እንዳይነገር እና የሰራዊቱ ወኔ እንዳይሰበር ለማድረግ ሞክረው ነበር። ሆኖም ግን ቁስሉ ከባድ ስለነበር በዚያው ሌሊት ወደ ማረፊያቸው ተወስደው ሕይወታቸው አልፏል።

የንጉሡ መስዋዕትነት ልዩ የሚያደርገው፣ በጦርነቱ መሃል ቆስለው ሳለ ስለ ራሳቸው ሳይሆን ስለ ሀገራቸውና ስለ ሰራዊቱ መጨነቃቸው ነው። “ለኢትዮጵያ እና ለሃይማኖቴ ስል ደሜን አፈስሳለሁ” የሚለው ቃላቸውን በተግባር አሳይተዋል። ንጉሡ ከሞቱ በኋላ ሰራዊቱ በመሪው ሞት ደንግጦ ወደ ኋላ በማፈግፈጉ፣ በድል ተጀምሮ የነበረው ጦርነት በመሪ መስዋዕትነት ተጠናቀቀ።

 

ጎርቫቾቭ ተመረጠ

መጋቢት 2 ቀን 1977 ዓ.ም ሚካኤል ጎርባቾቭ የሶቪየት ሕብረት ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ በመሆን ተመረጡ። ይህ ክስተት በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፦

በመጀመሪያ፣ ጎርባቾቭ ወደ ስልጣን እንደመጡ “ግላስኖስት” (ግልጽነት) እና “ፔሬስትሮይካ” (መልሶ መገንባት) የተባሉ አዳዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን አስተዋወቁ። ይህ እርምጃ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተዘግቶ የነበረውን የሶቪየት ሥርዓት ለውጥ እንዲያስተናግድ አድርጓል።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህ ሁነት በዓለም ላይ ለረጅም ዓመታት የዘለቀው “የቀዝቃዛው ጦርነት” (Cold War) ማብቂያ መጀመሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ጎርባቾቭ ከምዕራባውያን ጋር የነበረውን ውጥረት ለማርገብ እና የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን ለመቀነስ ያደረጉት ጥረት የዓለምን ሰላም ቀይሯል።

በመጨረሻም፣ የእርሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት እና ያመጡት ለውጥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የበርሊን ግንብ እንዲፈርስ እና የሶቪየት ሕብረት እንድትበታተን ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ በምስራቅ አውሮፓና በዓለም ዙሪያ የነበረውን የኮሚኒዝም ስርጭት እና የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። ስለሆነም መጋቢት 2 ቀን በዓለም ፖለቲካ ውስጥ የአንድ ትልቅ ጎራ መፍረስ እና የአዲስ ዓለም ስርአት መፈጠር መነሻ ተደርጎ የሚታሰብ የታሪክ ሁነት ነው።

 

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here