ሰሞኑን በኢትዮጵያውያን የቲክቶክ እና የዩቲዩብ መንደር አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። የዳዊት መኮንን “አንቺ ነይማ (ቆየሽኮ)” የተሰኘው ሙዚቃ አዲስ እና ዘመናዊ መልክ ይዞ ብቅ አለ። ዘፈኑ በሰዓታት ውስጥ በሺዎች፣ ቀጥሎም በሚሊዮኖች ታየ፤ ቫይራል ሆነ። አድማጭ “ዳዊት መኮንን ዘፈኑን በአዲስ መልክ ሪሚክስ አድርጎ ሰራው እንዴ?” ብሎ ተገረመ። ድምፁ የዳዊት ነው፤ ስሜቱ ይመሳሰላል።
አንድ ታዳጊ ልጅ በኮልታፋ ድምጹ እየዘፈነ ነው። ነገር ግን እውነታው አስደንጋጭ ነበር። ይህ ሙዚቃ በዳዊት መኮንን አልተዘፈነም፤ በማንኛውም የሙዚቃ ስቱዲዮ ውስጥም አልተቀረፀም፤ ሙሉ በሙሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) “የድምፅ መባዛት” (Voice Cloning) ቴክኖሎጂ አማካኝነት ኮምፒውተር የፈጠረው “የማስመሰል” ስራ እንጂ። ይህ ክስተት ብዙዎችን ሲያስደስት፣ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ግን ከፍተኛ ድንጋጤን የፈጠረ የ”ማንቂያ” ደወል ሆኗል።
ከጥቂት ወራት በፊት “Heart on My Sleeve” የተሰኘ የውጭ ሙዚቃ በታዋቂዎቹ ድሬክ እና ዘ ዊክንድ ድምፅ በ “AI” ተሰርቶ ዓለምን ሲያነጋግር ነበር። እኛ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን የሰማነው እንደ ሩቅ ሀገር ዜና ነበር። ዛሬ ግን ያ ቴክኖሎጂ ድንበራችንን ጥሶ፣ የቅጅ መብት ህጋችንን ንቆ፣ የከያኒዎቻችንን ድምፅ ያለፍቃድ እየተጠቀመ ይገኛል። የዳዊት መኮንን ክስተት መነሻ እንጂ መድረሻ አይደለም። በቅርቡ የተለያዬ ስያሜ በተሰጣቸው የዩቱዩብ ቻናሎች ከአንጋፋ እስከ ወጣት፣ ከሴት እስከ ወንድ የብዙዎቹ ኢትዮጵያዊያን ዘፋኞች ሙዚቃ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እየተሰራ ነው። የድምጻዊያንን ስም ዘርዝረን አንጨርሰውም።
የችግሩ ግዝፈት ያለው እዚህ ላይ ነው። አንድ ድምጻዊ ልዩ የድምፅ ቀለሙን (Vocal Identity) ለመገንባት፣ የራሱን ማንነት በህዝብ ዘንድ ለማሳወቅ አሥርተ ዓመታት ይፈጅበታል። ዛሬ ግን አንድ ተራ የኮምፒውተር እውቀት ያለው ግለሰብ፣ የዚያን ዘፋኝ ድምፅ ለ“AI” በመመገብ (Prompt በማድረግ) ብቻ፣ ድምጻዊው በጭራሽ አስቦት በማያውቀው የፖለቲካ፣ የዘረኝነት ወይም የብልግና ግጥም ላይ ድምፁን ጭኖ ሊያስዘፍነው የሚችልበት አስፈሪ ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህ የፈጠራ ስርቆት ብቻ ሳይሆን፣ የማንነት ስርቆትም ነው።
ኤ አይ አሁን ያለው የግንዛቤ ደረጃ 45 በመቶ ነው። ገና ወደ ሰው የንቃት ደረጃ ያድጋል። የኢትዮጵያን ቋንቋዎች እየተናገረ ነው። በደንብ መልመድ ነው የቀረው። ምናልባት ዘፈኖች ላይ አንዳንድ ቃላትን ያጥብቃል፤ ያላላል፤ አያጠብቅም፤አያላላም። በሒደት ግን እንደ እኛ ጥንቅቅ አድርጎ ያወራል። አፉን በፈታበት እንግሊዝኛ ቋንቋ ግን ፍጹም ከሰው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ የማይክል ጃክሰንን ዘፈን በኤ አይ ስንሰማው ከቀደመው ዘፋኝ ጋር ተመሳሳይ ነው።
በዋናነት ሦስት ታላላቅ የኤ አይ ፈጠራዎች ኢንዱስትሪውን እየናጡት ይገኛሉ። የመጀመሪያው የድምፅ መባዛት (Voice Cloning) ይባላል። የአንድን ታዋቂም ሆነ ተራ ዘፋኝ ድምፅ ወስዶ፣ እሱ በጭራሽ ዘፍኖት በማያውቀው ሌላ ሙዚቃ ላይ መጫን እና ማስዘፈን መቻሉ። ለምሳሌ ሸዋንዳኝ ኃይሉ የመልካሙ ተበጀን ዘፈን ሲዘፍን ሙዚቃ ተሰርቷል። እዚህ ላይ አንድ ዘፋኝ በኤ አይ ድምጽ የቀድሞ ዘፈኑን ሲጫዎትም እንሰማለን። አሁን በሀገራችን ሙዚቃዎች የገባው ወረርሽኝ ይሄ ነው።
ሁለተኛው የሙዚቃ ማቀናበር (Generative Music) ነው። ጥቂት የጽሁፍ መመሪያዎችን (Prompts) ለኮምፒውተር በመስጠት ብቻ፤ ሙሉ ዜማ፣ ሪትም እና ግጥም ያለው ሙዚቃ በሰከንዶች ውስጥ ማውጣት። ጋዜጠኛ እና ገጣሚ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ይህን ቀደም ብሎ ጀምሮታል። አዲስ ዜማ፣ ግጥም ድምፅ ያለው ዘፈን በኤ አይ ሰርቶ ለአድማጭ በማድረስ ቀዳሚ ነው።
ሌላው የቀጥታ ድምፅ ማስተካከያ (Real-time AI Audio Processing) የሚባለው ነው። ዘፋኞች በኮንሰርት ላይ በቀጥታ ሲዘፈኑ ድምፃቸውን በቅጽበት እጅግ ማራኪ አድርጎ የሚያስተካክል ቴክኖሎጂ ተፈጥሯል።
ይህ የቴክኖሎጂ ማዕበል ዓለም አቀፉን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ በሁለት ጎራ ከፍሎታል። እንደ ዩኒቨርሳል ሙዚቃ ግሩፕ (UMG) ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች እና አንጋፋ ድምፃዊያን “ማሽኖች የዘፋኞችን የፈጠራ ባለቤትነት እየጣሱ ነው፤ ዘፋኞች ለዓመታት የገነቡትን ድምፅ በነፃ እየሰረቁት ነው” ብለው ይከራከራሉ። እንደ ቢልቦርድ (Billboard) ጥናት ከሆነ፣ የሙዚቃ ገበያው የኤ አይ አጠቃቀምን በፍጥነት መቆጣጠር ካልቻለ መፈራረሱ አይቀርም።
በሌላ በኩል “ይህ የፈጠራ መሳሪያ ነው። ወጣቱ እና አማተር ዘፋኞች ውድ የስቱዲዮ ክፍያ ሳይከፍሉ አዳዲስ ድምፆችን በቤታቸው እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል” የሚሉ አሉ። የዳዊት መኮንንን ኤ አይ ዘፈን በቲክቶክ እያጋራ የሚዝናናው ወጣት የዚህ ጎራ ተወካይ ነው።
ምንም እንኳን ኤ አይ ዜማን፣ ሪትምን እና ግጥምን በሰከንዶች ውስጥ አቀናብሮ ማውጣት ቢችልም፣ ሙዚቃ ግን ከቀመር ስሌት በላይ ነው። ሙዚቃ የሰው ልጅ ስሜት፣ ሃዘን፣ ደስታ እና መንፈስ መግለጫ ነው። ማሽን የዳዊትን ድምፅ ሊኮርጅ ይችላል፤ ነገር ግን ዳዊት መኮንን ያንን ዜማ ሲያወጣ ከውስጥ ያመነጨውን ስሜት ሊሰጠን አይችልም። ከዚህም ባለፈ፣ የባህል ዜማዎቻችንን (ቅኝቶቻችንን) በማሽን እየኮረጁ ማባዛት የሙዚቃችንን ትክክለኛነት ከመበረዙም በላይ፣ የዜማ ደራሲያንን፣ የሙዚቃ አቀናባሪዎችን እና የጀርባ አቀንቃኞችን ስራ አደጋ ላይ ይጥለዋል።
የዚህ ቴክኖሎጂ ጥቅም ከፍተኛ ነው። የሙዚቃ ስቱዲዮ ኪራይ እና ውድ የሙዚቀኛ ክፍያ ለማይችሉ አዲስ የጥበቡ ሰዎች ትልቅ በር ይከፍታል፤ አዳዲስ የሙዚቃ ስልቶችም እንዲፈጠሩ ያደርጋል። በሌላ በኩል ግን ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የሙዚቃን ጥራት ሊያወርድ፣ በውስጡ ያለውን እውነተኛ የሰው ልጅ ስሜት ሊያጠፋው እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የብዙ የጀርባ አቀንቃኞችን፣ የዜማ እና ግጥም ደራሲያንን ስራ አደጋ ላይ በመጣል ስራ አጥ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ኤ አይ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገና በጅማሮ ላይ ቢሆንም መዘዙ ግን ከወዲሁ ማንዣበብ ጀምሯል። በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ ዋና ዋና ተጽዕኖዎች የሚከተሉ ናቸው።
ኢትዮጵያ የብዙ ባህላዊ ዜማዎች ባለቤት ናት። ኤ አይ እነዚህን የባህል ዜማዎች፣ የመሳሪያ ድምፆች (እንደ ማሲንቆ፣ ክራር፣ ዋሽንት) በማስመሰል ሲሰራ የባህሉን ትክክለኛነት (Authenticity) ሊበርዘው እና ታሪካዊ እሴቱን ሊያሳጣው ይችላል።
በሌላ በኩል በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራዎቻቸውን ማውጣት ላልቻሉ አነስተኛ በጀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጠቢባን፣ በቤታቸው ሆነው ከፍተኛ ጥራት ያለው የሙዚቃ ዝግጅት በኤ አይ ታግዘው ለመስራት ሰፊ እድል ያገኛሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ያለው ማህበረሰብ የተለያየ አቋም አለው። ወጣቱ ትውልድ ለቴክኖሎጂው ክፍት በመሆኑ በኤ አይ አዳዲስ ሙዚቃዎችን መፍጠር እና መጫወት እንደ ትልቅ መዝናኛ አይቶታል። በተቃራኒው አንጋፋ ድምፃዊያን እና ሙዚቀኞች ድምፃቸው፣ ዜማቸውና ለዓመታት የገነቡት ስራ በህገ-ወጥ መንገድ ማሽኖች ሲጠቀሙበት በማየት ክስ እስከመመስረት የሚደርስ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሳዩ ነው።
የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ከዚህ የኤ አይ አብዮት ማምለጥ አይችልም። ወደፊት መጓዝ ብቻ ነው አማራጩ። የወደፊቱ የሙዚቃ ሁኔታም የሚከተለውን መልክ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የኤ አይ ሙዚቃን የሚቆጣጠር ጠንካራ ህግ እየተረቀቀ ነው። የአንድ ሰው ድምፅ ልክ እንደ ቤት ወይም መኪና የንብረትነት መብት የሚሰጥበት እና ያለፈቃድ ከተጠለፈ በህግ የሚያስቀጣበት ዘመን ይመጣል።
ማሽንም ሰውን ሙሉ በሙሉ አያጠፋም። ይልቁንስ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ስሜት እና የኤ አይ ቴክኖሎጂ ተጣምረው የሚሰሩበት፣ ሰው እና ማሽን የሚተባበሩበት (Human-AI Collaboration) የላቀ የሙዚቃ ዘመን ይመጣል።
ዲጂታል እና በኤ አይ የተሰሩ ሙዚቃዎች በየቦታው በነፃ ሲሞሉ፣ ሰዎች “እውነተኛ የሰው ልጅ ዘፋኝ” በአካል ሲዘፍን ለማየት ያላቸው ጉጉት ይጨምራል። በመሆኑም የቀጥታ ኮንሰርት ትኬት ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ሙዚቃን አያጠፋውም፤ ነገር ግን ሙዚቃን የምንፈጥርበትን፣ የምንሰማበትን እና የምንሸጥበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪም ከዚህ የቴክኖሎጂ ማዕበል ውጭ ሊሆን አይችልም።
መረፊያ
ቅኔ
በጨለማ ስሄድ ማነህ ይለኛል ሰው
ተልኬ አይደለም ወይ የምመላለሰው
ተልኬ- ሕብረ ቃል
ሰም- መልእክት አድርስ ተብየ
ወርቅ- አቻየ/ልኬ ከሆነች ሴት
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


