በቅርብ ያለው ሩቅ

0
150

አንድ ስኬታማ አሜሪካዊ የኢንቨስትመንት ባንከር (የገንዘብ ባለሙያ) ለእረፍት ወደ አንዲት ፀጥታ የሰፈነባት የሜክሲኮ የባህር ዳርቻ መንደር ይሄዳል:: በዚያም አንድ አሳ አጥማጅ በትንሽ ጀልባው ጥቂት ትልልቅ አሳዎችን ይዞ ወደ ዳርቻው ሲወጣ ይመለከታል::

ባንከሩም “እነዚህን አሳዎች ለማጥመድ ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?” ሲል ይጠይቀዋል:: አሳ አጥማጁም “ጥቂት ሰዓታት ብቻ” ብሎ ይመልሳል:: ባንከሩ በመገረም “ታዲያ ቀኑን ሙሉ ምን ትሰራለህ?” ይለዋል::

አሳ አጥማጁም ፈገግ ብሎ “ረፋድ ላይ እነቃለሁ፤ ትንሽ አሳ አጠምዳለሁ፤ ከልጆቼ ጋር እጫወታለሁ፤ ከባለቤቴ ጋር እረፋድ ላይ እተኛለሁ:: ማታ ማታ ደግሞ ወደ መንደር ወጥቼ ከጓደኞቼ ጋር እየተዝናናሁ ጊታር እጫወታለሁ:: ሙሉ እና ደስተኛ ህይወት አለኝ” አለው::

ባንከሩ በንቀት ፈገግ ብሎ “እኔ የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ነኝ፤ ልረዳህ እችላለሁ:: ብዙ ሰዓት አሳ ማጥመድ አለብህ:: በምታገኘው ትርፍ ትልቅ ጀልባ ትገዛለህ:: ቀስ እያልክም ብዙ ጀልባዎች  ይኖሩሃል:: በመጨረሻም ወደ ኒውዮርክ ሄደህ ትልቅ ኩባንያ ትከፍታለህ:: ሚሊየነር ትሆናለህ” አለው::

አሳ አጥማጁም “ይህን ሁሉ ለማድረግ ስንት ጊዜ ይፈጅብኛል?” አለው:: ባንከሩ “ከ15 እስከ 20 ዓመታት” አለው:: “ከዚያስ?” ጠየቀ አጥማጁ:: ባንከሩም በደስታ ስሜት “ዋናው ደስታ እዚያ ላይ ነው! ሀብታም ስትሆን ጡረታ ትወጣና ወደ አንዲት ትንሽ የባህር ዳርቻ መንደር ትሄዳለህ:: ረፋድ ትነቃለህ፤ ትንሽ አሳ ታጠምዳለህ፤ ከልጅ ልጆችህ ጋር ትጫወታለህ፤ ማታ ከጓደኞችህ ጋር ጊታር ትጫወታለህ!” አለው:: አሳ አጥማጁም ግራ በመጋባት “ታዲያ አሁን እየኖርኩ ያለሁት ህይወት እሱ አይደለም እንዴ?” ብሎት መንገዱን ቀጠለ:: ይህ ታሪክ የሚያስተምረን የሰው ልጅ ዕድሜውን ሙሉ ሲያሳድደው የሚኖረው ደስታ አብዛኛውን ጊዜ እጁ ላይ የሚገኝ መሆኑን ነው::

የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ እና ባፈጣጠሩ ደስታን ፈላጊ ሆኖ ነው ወደዚች ዓለም የመጣው:: የስነ ልቦና ጠበብት እንደሚሉት የሰው ልጅ ከመከራ እና ከህመም እየሸሸ ወደ ደስታ እና ምቾት እንዲያዘነብል ሆኖ የተዋቀረ ፍጡር ነው:: ህይወትን የማቆየት (ለመኖር) ውስጣዊ ስሜታችን ከደስታ ጋር የተቆራኘ ነው:: ስንመገብ፣ ስንዋደድ፣ ሲሳካልን አእምሯችን ደስታን በመስጠት ይሸልመናል። ይህ ሽልማት ደግሞ ድርጊቱን ደጋግመን እንድንሰራውና በህይወት እንድንቀጥል ያደርገናል::

ደስታ በአእምሮ ሳይንስ መነጽር ሲታይ ረቂቅ መንፈሳዊ ስሜት ብቻ ሳይሆን በአእምሯችን ውስጥ የሚፈጠሩ ኬሚካላዊ ሂደቶች ውጤት ነው:: ሳይንሱ የደስታ ኬሚካሎችን በዋናነት በአራት ይከፍላቸዋል (DOSE በሚል ምህፃረ ቃል ይታወቃሉ)::

ቀዳሚው ዶፓሚን ነው:: ይህ የሽልማት ኬሚካል ነው:: አንድን ግብ ስናሳካ፣ ፈተና ስናልፍ፣ ወይም ማግኘት የፈለግነውን ነገር ስናገኝ አእምሯችን ዶፓሚን ያመነጫል:: ይህ ኬሚካል “ጎበዝ! አሁንም ቀጥል” የሚል ስሜት ይሰጠናል::

ሁለተኛው ኦክሲቶሲን  ይባላል:: የፍቅር፣ የመተሳሰብ እና የመተማመን ሆርሞን ነው:: ከምንወደው ሰው ጋር ስንተቃቀፍ፣ እናት ልጇን ስታጠባ፣ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ ግንኙነት ስንፈጥር ይመነጫል:: ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 85 ዓመታት ያደረገው “የአዋቂዎች ህይወት ጥናት” እንዳረጋገጠው ለረዥም ዘመን ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርገን ዋናው ነገር  ጥሩ እና ጤናማ ማህበራዊ ግንኙነት ነው::

ሦስተኛው ሴሮቶኒን  ነው:: መረጋጋትን፣ ኩራትን እና በራስ መተማመንን የሚሰጥ ኬሚካል ነው:: ሰዎች ስራችንን ሲያደንቁልን፣ ማህበረሰቡ ሲያከብረን ሴሮቶኒን ይመነጫል::

አራተኛው ኢንዶርፊን  ይባላል:: የተፈጥሮ ማስታገሻችን ነው:: ስፖርት ስንሰራ፣ ከልባችን ስንስቅ፣ ወይም አካላዊ ድካም ሲያጋጥመን ህመምን ለመቋቋም እና ጥሩ ስሜት እንዲሰማን አእምሯችን የሚያመነጨው ኬሚካል ነው::

በኒውሮሳይንስ መሰረት ደስተኛነት ማለት የእነዚህ አራት ኬሚካሎች ጤናማ ውህደት እና ሚዛን መጠበቅ ማለት ነው:: ከሳይንሱ ባሻገር የሰው ልጅ ማሰብ ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ፍልስፍና የደስታን ትርጉም ሲመራመር ኖሯል::

ታዋቂው ግሪካዊ ፈላስፋ አርስቶትል ደስታን “ዩዳይሞኒያ” (Eudaimonia) በሚል ቃል ይገልፀዋል። ለእሱ ደስታ ማለት ጊዜያዊ ፈንጠዝያ ወይም ስሜት ሳይሆን ትርጉም ያለው ህይወት መኖር፣ በጎነትን መላበስ እና የራስን አቅም አውጥቶ መጠቀም ነው:: አርስቶትል “ደስታ የህይወት ትርጉም እና ዓላማ፣ የሰው ልጅ ህልውና ሙሉ መጨረሻ ነው” ብሏል::

ኤፒከረስ የተባለው ፈላስፋ የደስታ መሰረት “ከህመም ነጻ መሆን እና የአእምሮ ሰላም ማግኘት ነው ብሎ ያምናል:: ብዙዎች ኤፒከረስን የሥጋዊ ደስታ አራማጅ አድርገው ያስቡታል፤ እሱ ግን “ደስታ ማለት ውስብስብ ነገሮችን ማስወገድ፣ ከጓደኞች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እና በቀላል ህይወት መርካት ነው” ይላል::

በስቶይሲዝም ፍልስፍና ደስታ ማለት ከውጭ የሚመጣብንን ነገር (ሀብት፣ ዝና፣ በሽታ) መቆጣጠር ባንችልም ለእነዚህ ነገሮች የምንሰጠውን ምላሽ ግን መቆጣጠር ስንችል የሚመጣ የውስጥ ሰላም ነው::የዚህ ፍልስፍና አራማጆች  ሴኔካ እና ማርከስ ኦሪሊየስ የሚያምኑት በዚህ ነበር:: ሴኔካ “እውነተኛ ደስታ አሁን ባለን ነገር መደሰት እና ስለ ወደፊቱ በጭንቀት አለመጠበቅ ነው” ይላል::

ሀብት፣ ዝና እና ስኬት የደስታ የመጨረሻ ጥግ ይመስሉናል:: ዝነኞች የህይወት ታሪካቸውን በፃፉባቸው መጽሐፍት ይህን አመለካከት ይሰብሩታል::

የሆሊውድ ሜጋ ስታር ዊል ስሚዝ በህይወቱ ያሰበውን ሁሉ፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ሽልማት አግኝቷል:: ሆኖም በመጽሐፉ ላይ እንዲህ ይላል “በዓለም ላይ ያለውን ሁሉ ነገር አሳክቼ፣ ነገር ግን ውስጤ ባዶነት ተሰምቶኝ መሬት ላይ ተኝቼ ያለቀስኩበት ጊዜ አለ:: ውጫዊ ስኬት የውስጥ ቀዳዳን ሊደፍን አይችልም:: ደስታ ከራስ ጋር ሰላም ከመፍጠር እንጂ ከውጭ ከሚመጣ ጭብጨባ አይገኝም::”

ዝነኛው የፊልም  ተዋናይ ማቲው ማኮናሄ  ግሪን ላይትስ በሚለው  ደስታን (Happiness) እና ሀሴትን (Joy) ይለያየዋል:: “ደስታ የአንድ የተወሰነ ውጤት ምላሽ ነው:: ‘ይህን ሳገኝ ደስተኛ እሆናለሁ’ ካልን፣ ያንን ነገር እስክናገኝ ደስተኞች አንሆንም:: ሀሴት (Joy) ግን እያደረግን ባለው ነገር ሂደት ውስጥ የምናገኘው ቋሚ እርካታ ነው:: ስለዚህ በውጤት ላይ የተመሰረተ ደስታን ሳይሆን፣ የህይወት ትርጉም የሆነውን ሀሴትን መምረጥ አለብን” ይላል::

ዝነኛዋ የሚዲያ ሰው ኦፕራ ዊንፍሬይ ዋት አይ ኖው ፎር ሹር በሚለው መጽሐፏ  የደስታ ሚስጥር ምስጋና እንደሆነ ታስረግጣለች:: “ስላለህ ነገር የምታመሰግን ከሆነ ሁልጊዜ ተጨማሪ ነገር ይኖርሃል:: ነገር ግን በሌለህ ነገር ላይ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ ፈጽሞ በቂ ነገር አይኖርህም:: እውነተኛ ደስታ የሚጀምረው አሁን ባለህበት ሁኔታ አመስጋኝ ስትሆን ነው” ብላለች::

ሳይንቲስቶች ብሪክማን እና ካምቤል ያጠኑት ጥናት እንደሚያሳየው የሰው ልጅ የተለየ ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ሲያጋጥመው (ለምሳሌ ሎተሪ ሲደርሰው ወይም አደጋ ደርሶበት አካል ጉዳተኛ ሲሆን) ለጊዜው የደስታው መጠን ወደ ላይ ይወጣል ወይም ወደ ታች ይወርዳል:: ነገር ግን ከጥቂት ወራት በኋላ ሁሉም ሰው ወደ ቀድሞው መደበኛ የደስታ መጠኑ ይመለሳል:: ይህ ማለት አዲስ መኪና ወይም ቤት ስንገዛ የሚኖረው ደስታ ጊዜያዊ ነው:: ልክ በትሬድሚል (በስፖርት ማሽን) ላይ እንደሚሮጥ ሰው ብንሮጥም ያለንበት ቦታ ላይ ነን:: ስለዚህ የቁስ ደስታ ጥግ የለውም:: ሁሌም አዲስ ነገር እንፈልጋለን::

የደስታ ጥግ ሁልጊዜ ፈገግ ማለት እና ችግሮችን መካድ አይደለም:: በስነ ልቦና “ቶክሲክ ፖዘቲቪቲ” የሚባለው ጽንሰ ሀሳብ አለ:: ተፈጥሯዊ የሆኑትን እንደ ሀዘን፣ ቁጣ እና ብስጭት ያሉ ስሜቶችን አፍኖ በማስቀረት “ሁሌም ደስተኛ መሆን አለብኝ” ብሎ ማሰብ አደገኛ መሆኑን ይገልጻል:: ጤናማ ደስታ ማለት ህመምን አምኖ መቀበል መቻል ነው::

ታዋቂው የስነ ልቦና ሊቅ ካርል ዩንግ “የደስታ ቃል ትርጉሙን የሚያጣው በሀዘን ሚዛን ካልተስተካከለ ነው” ይላል:: የደስታ ጥግ ሊታወቀን የሚችለው የሀዘንን ጥልቀት ስንረዳ ብቻ ነው:: መከራ እና ፈተና በሌለበት ዓለም ውስጥ እውነተኛ የደስታን ጣዕም ማወቅ አይቻልም::

ደስታ ነገ እዚያ ማዶ ሄደን የምናመጣው ሳይሆን ዛሬ እዚሁ የምንኖረው ነው:: ከራስ ጋር በሚደረግ ሰላም ውስጥ ደስታ ይገኛል::

የደስታ ጥግ ቁሳቁስ ማከማቸት ሳይሆን ባለን ነገር ማመስገን እና በህይወት ፈተናዎች ውስጥም ተስፋ አለመቁረጥ ነው:: የሰው ልጅ ለደስታ ተፈጥሯል፤ ደስታውም የሚገኘው በሚያደርገው ጉዞ ላይ እንጂ በሚደርስበት የመጨረሻ ግብ ላይ ብቻ አይደለም:: ደስታ መንገድ ነው፤ እናም የሚያስፈልገው በጉዞው መደሰት ነው::

 

(አቢብ አለሜ)

በኲር የመጋቢት 7  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here