“ነገ ኑ”ን ያስቀረዉ ማዕከል

0
180

በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማትን አሠራር ለማዘመን እና የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ ከባለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ በርካታ ርምጃዎች እተወሰዱ ነው። እነዚህ ሥራዎች በዋናነት ዲጂታላይዜሽን፣ የሰው ኀይል ብቃት እና የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ይህም የመንግሥት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እና የሰውን ግንኙነት በመቀነስ ለሙስና ያለውን ዕድል ከማጥበብ ባለፈ ፍጥነትን ለመጨመር ያለመ ነው፡፡ በተለይ ተቋማትን ከወረቀት ንክኪ ነፃ ወደ ሆነ እና በውጤት ወደ ሚለካ አሠራር ለማሸጋገር እየተተገበሩ ካሉ የለውጥ ሥራዎች መካከል የመሶብ አንድ ማዕከል ተጠቃሽ ነው፡፡

የመሶብ ማዕከል ይህንን ዓለም አቀፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ፍልስፍና ወደ ሀገር በቀል አሠራር በመቀየር ሲተገበር በአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፉ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣትን ግቡ በማድረግ ነው፡፡ እንደ ኢስቶኒያ፣ ሲንጋፖር እና ህንድ ሁሉ የመረጃ ቅንጅትን እንደ ዋና ስልት በመጠቀም የተለያዩ ተቋማት መረጃዎቻቸውን እንዲያጋሩ በማድረግ ተገልጋዩ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላው የሚንከራተትበትን አሰልቺ አሠራር ለማስቀረትም በር የከፈተ ዓለም አቀፍ የአሠራር ሥርዓት ሆኖ ይነሳል፡፡

በአማራ ክልልም ዘመናዊው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተገንብቶ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ሥርዓቱ የተንዛዛ ቢሮክራሲን በማስቀረት ዜጎች ቀልጣፋ እና ዲጂታል አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ታቅዶ የቀረበ ነው።

የባለጉዳዮችን ምልልስ እና የቆይታ ጊዜን ሙሉ በሙሉ ያስቀረ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሰልፍ መቆጣጠሪያ እና የዲጂታል ግብረ-መልስ መስጫ መሣሪያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ የአገልግሎት ሰጪዎችን ብቃት ለመመዘን እና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ ማሻሻያ ለማድረግ አስችሏል። ይህ አሠራር በሩዋንዳ ኢሬምቦ /Irembo/ የተሰኘው የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥትን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ዜጎች በአስተዳደሩ ላይ ያላቸውን እምነት በመገንባት  ውጤት አስመዝግቧል።

በባሕር ዳር ከተማም በቅርብ አገልግሎት መስጠት በጀመረው የመሶብ አገልግሎት ነዋሪዎች እንደ ሩዋንዳ ዜጎች  ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ለዚህም  የሽምብጥ ክፍለ ከተማ /ቀበሌ 13 /ነዋሪዋ የወይዘሮ ጥሩዬ አዘነ ምስክርነት ትልቅ ማሳያ ነው።  ወይዘሮ ጥሩዬ የንግድ ግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN number) ለማውጣት ወደ መሶብ የአማራ ክልል አንድ ማዕከል ሲያመሩ ቀድሞ በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ልምድ ምክንያት በስጋት እና በጥርጣሬ ነበር። በተለይም በአራስነት ወቅት  ሕፃን ከቤታቸው ትተው መምጣታቸው እንዲሁም ቀደም ሲል ባለቤታቸው በተመሳሳይ ጉዳይ የገጠማቸውን እንግልት ማስታወሳቸው ጭንቀታቸውን አክብዶት ቢቆይም በተቋሙ ውስጥ የገጠማቸው እውነታ ግን ከጠበቁት በላይ ሆኖ እንዳገኙት ተናግረዋል፡፡

ገና ከበር ጀምሮ በመረጃ ሰጪዎች ለጉዳያቸው ተገቢው አቅጣጫ በፍጥነት መሰጠቱ እና በሠራተኞች ዘንድ የሚታየው መልካም አቀባበል በሌሎች ተቋማት የሚታየውን የከፋ ፊት እና የተዛባ መረጃ አሰጣጥን የሰበረ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ወይዘሮ ጥሩዬ መስክረዋል። ምንም እንኳ አልፎ አልፎ በሚያጋጥም የኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት የሲስተም መዘግየቶች ቢኖሩም የሠራተኞቹ ትሕትና እና ግልጽነት ተገልጋዮች በትዕግስት እንዲጠባበቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ በእንክብካቤ እና በክብር ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ለሌሎች የመንግሥት ተቋማትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ተቋማት አሠራራቸውን ዘመናዊ እና ለሰው ልጅ ክብር የሚሰጥ እንዲያደርጉ ወይዘሮ ጥሩዬ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ተማረ አቤ እንደገለጹት ማዕከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የሚስተዋሉ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ የተቋቋመ የመፍትሔ አካል ነው። ቀደም ሲል የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በሥልጠና እና በስብሰባ ብቻ ሊታረም ያልቻለ እና የሕዝቡን እንግልት፣ ውጣ ውረድ እንዲሁም ቅሬታ እያባባሰ የመጣ በመሆኑ ችግሮቹን በጥናት በመለየት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል ማሰባሰብ እና አሠራሮችን ማዘመን የግድ መሆኑ ታምኖበት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በዚህም  መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ጥናቶች እየተደረጉበት እና እየተፈተሹ የመጣ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ያለባቸው፣ ተገልጋይ የሚበዛባቸው፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር የተንሰራፋባቸው እንዲሁም ቅሬታ የሚበዛባቸው ተቋማት ተለይተው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ የማዕከሉ ዋነኛ ዓላማ የተገልጋይን እንግልት መቀነስ እና አገልግሎቶችን ተያያዥነት ባላቸው ተቋማት መካከል ማቀናጀት በመሆኑ በአሁኑ ወቅት 14 የፌዴራል እና የክልል ተቋማት ወደ አንድ ማዕከል እንዲሰባሰቡ ተደርገዋል። መሶብ ባለፉት ስድስት ወራት ሥራ ሲጀምር 47 ዓይነት አገልግሎቶችን ይዞ የነበረ ቢሆንም በተገልጋዮች ፍላጎት፣ በማዕከሉ እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ እና ሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን  ጥናት መሠረት አገልግሎቶቹ በየጊዜው እየተጨመሩ መጥተው በአሁኑ ወቅት 61 መድረሳቸውን አስታውቀዋል። እስካሁንም ከ33 ሺህ በላይ አገልግሎት ፈላጊዎች ከማዕከሉ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ነው ያሉት፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ የእርካታ ደረጃም የተሻለ እና አበረታች መሆኑን ነው ኃላፊው ያስታወቁት፡፡ የማዕከሉ አገልግሎት ስኬት የሚለካው አገልግሎቱ በሚወስደው አጭር ጊዜ እና በተገልጋዩ እርካታ በመሆኑ መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ተቀርጾለታል። ይህ ማለት ማንኛውም አገልግሎት የሚወስደው ጊዜ እና የሚያስፈልገው መስፈርት አስቀድሞ በግልጽ ስለሚታወቅ ሠራተኞች በራሳቸው ፍላጎት ጉዳይን የማዘግየት ዕድል እንደማይኖራቸው አቶ ተማረ አስገንዝበዋል፡፡

ለእያንዳንዱ አገልግሎት ዝርዝር መለኪያ/ስታንዳርድ/ መውጣቱ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ይበልጥ ቀልጣፋ አድርጎታል። በአካልም ሆነ በበይነ መረብ (ኦንላይን) የሚሰጠው ይሄው አገልግሎት ተገልጋዩን ከተደጋጋሚ ቀጠሮ እና ካላስፈላጊ ወጪ ከመታደጉ ባለፈ በአንድ ተቋም ብቻ መቋጫ ለማያገኙ ጉዳዮች የተቀናጀ መፍትሔ በመስጠት ላይ ይገኛል ነው ያሉት አቶ ተማረ።

መሶብ የአገልግሎት “ነገ ኑ” ቀጠሮን ያስቀረ፣ አገልግሎት ፈላጊውም የፈለገውን አገልግሎት አግኝቶ አመስግኖ የሚወጣበት እንዲሆን ማድረግ የማዕከሉ ርእይ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ መሶብ በተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ግንባር ቀደም/ሞዴል/ የሆነው በበርካታ ምክንያቶች ሲሆን ማዕከሉ ላይ ያሉ ባለሙያዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በሚጠብቅ ሁኔታ ማብቃት መቻሉን አቶ ተማረ ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ በዕድሜ ወጣት፣ ለቴክኖሎጂ ቅርብ እና በባህሪያቸው ምስጉን የሆኑ እንዲሁም የብቃት ምዘና ያለፉ ባለሙያዎች የማዕከሉ ተቀዳሚ ተመራጭ መሆናቸው እና በተከታታይ የተሰጡ ሥልጠናዎች ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሌሎች ተቋማትም “እኛም እንደ መሶብ” የሚል ተነሳሽነትን ወስደው ለአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል እንዲሠሩ አርአያ መሆኑንም አቶ ተማረ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን የሪፎርም ድጋፍ እና ክትትል ዳይሬክተር አቶ እንዳላማው ይታይህ በበኩላቸው  የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲመሰረት መነሻ የሆነው ቀደም ሲል በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ስር የሰደዱ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ማዕከሉ ወደ ሥራ መግባቱ አገልግሎቱን የተቀናጀ እና ግልጽ በማድረግ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር የነበሩ አጋጣሚዎችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያስቀረ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ተገልጋዮች ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም ሲመላለሱ የነበረውን እንግልት እና ረጅም ወረፋ በማስቀረት በአንድ ማዕከል የተቀናጀ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉንም ለፋይዳው ማሳያ አድርገው ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡ ይህም አገልግሎቶቹ በአካል፣ በኦንላይን እና በአጭር የስልክ ጥሪ በኩል የሚሰጡ በመሆናቸው ተገልጋዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲያስፈጽሙ፣ ጊዜ እና ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ እንዲሁም ርቀት ሳይገድባቸው ፍትሐዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ አድርጓል ነው ያሉት።

ማዕከሉ በየሳምንቱ የተገልጋዮችን ግብረመልስ የሚሰበስብበት የራሱ የክትትል ስርዓት እንዳለውም አቶ እንዳላማው ጠቁመዋል፡፡ ተገልጋዮችም አገልግሎቱ እጅግ አርኪ ከመሆኑ የተነሳ እስከ ቀበሌ እና ክፍለ ከተማ ድረስ እንዲስፋፋ አስተያየት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም የአገልግሎቱን የእርካታ ደረጃ በሚፈለገው ልክ ማድረስ የማዕከሉ ግብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ወደ ሌሎች ተቋማት ለማስፋፋት፣ የሠራተኞችን የአቀባበል እና የደንበኞች አያያዝ ክህሎት በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን እና በዲጂታል የማገዝ ሥራዎች እንደ ዋነኛ የወደፊት አቅጣጫ መቀመጣቸውንም ከአቶ እንዳላማው ለመረዳት ተችሏል፡፡

የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በዘፈቀደ የሚመራ ሳይሆን በራሱ አዋጅ፣ ደንብ እና መመሪያዎች ላይ የተመሰረተ ግልጽ አሠራር ያለው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም አገልግሎቱን ወደ ማዕከሉ የሚያስገባው በጥናት ላይ ተመስርቶ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡ አንድ ተቋም አገልግሎቱን ወደ ማዕከሉ ካስገባ በኋላም በራሱ ፍላጎት የመመለስ ሥልጣን እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ካለው ሂደት ለመረዳት እንደሚቻለው ከማዕከሉ የወጣ አገልግሎት የሌለ ሲሆን፣ ይልቁንም አዳዲስ አገልግሎቶች በየጊዜው እየተጨመሩ እና በዲጂታል ሲስተም እየተደገፉ ይገኛሉ። አልፎ አልፎ ሲስተሙ ተገንብቶ እስኪያልቅ ድረስ በቢሮ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቢኖሩም አንዴ ወደ ሲስተም ከገቡ በኋላ ግን አገልግሎቶቹ በማዕከሉ በኩል ብቻ መሰጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ነው አቶ እንዳላማው ማረጋገጫ የሰጡት፡፡

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የመጋቢት 7  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here