አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ የዓለም ዓይንና ጆሮ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ነው:: ምክንያቱም ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እያንዳንዱን የዓለም ሕዝብ ይነካልና ነው::
የካቲት 28 2018 ዓ.ም አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃት የኢራኑ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኔይን ሕይዎት ከነጠቀ በኋላ የሆርሙዝ ባሕርን መተላለፊያን ኢራን ዘግታዋለች:: የሆርሙዝ ሰርጥ ደግሞ 20 በመቶ የዓለማችን ነዳጅ የሚተላለፍበት ወሳኝ መስመር ነው::
በሆርሙዝ ሰርጥ ኢራን እርምጃ እወስዳለሁ በማለቷ የመርከብ ጉዞ ተቋርጧል:: ይህ ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ዳፋ ቢኖረውም ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ላይ ግን ችግሩ የከፋ ይሆናል:: ሀገራቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለባቸው:: በዚህ ላይ ነዳጅን ከውጭ ሀገራት የሚያስገቡ በመሆኑ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ እንደሚታመን የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ይፋ አድርጓል::
በአውሮፓ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አበዳሪ ተቋማትም የሚፈጥርባቸውን ግሽበት ለማካካስ የወለድ ዋጋን ሊጨምሩ ይችላሉ:: ይህም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካን ሀገራት ችግር ያባብሰዋል ነው ያለው::
የነዳጅ ዘይት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ዶላር በላይ በበርሜል መሸጥ ጀምሯል:: እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ መረጃ ከሆነ የነዳጅ ዋጋ በዚህ ሁኔታ ለወራት የሚቀጥል ከሆነ ወደ 200 ዶላር ሊያሻቅብ ይችላል:: ይህም በገቢ እና ወጪ (በኢምፖርት እና ኤክስፖርት) ምርት ላይ ከባድ ተጽእኖ ያደርሳል:: ምክንያቱም የመርከብ ትራንስፖርት ለአፍሪካ ትልቅ ፈተና በመሆኑ ነው:: ይህም ለዶላር ዋጋ መናር መንስኤ ይሆናል::
ኢራን የዓለም እጅግ ወሳኝ የነዳጅ ነጥብ ተብሎ የሚታሰበውን ለሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ ያላት ቅርበት የሀገሪቱን ተጽእኖ ከፍ ያደርገዋል፤ ሀገሪቱ ታዲያ ሰርጡን መዝጋቷ ዓለም አቀፋዊ ምጣኔ ሀብታዊ ዳፋው የከፋ እንደሚሆን ነው ተንታኞች ያስጠነቀቁት::
እንደ አሜሪካ ኢነርጂ መረጃ አስተዳደር (ኢ አይ ኤ) ዘገባ ኢራን ከመካከለኛው ምሥራቅ ሩብ ያህሉን እና በዓለም 12 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን የዓለም ትልቅ የነዳጅ ክምችት አላት:: ይህም በኦፔክ አራተኛዋ ትልቅ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገር ያደርጋታል:: እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ አምራቾች መካካል አንዷ ናት:: ነገር ግን በዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ምክንያት ምርቷ ውስን ሆኖ ቆይቷል::
ኢራን የምዕራባዊያንን ማዕቀብ የምታልፍበት መንገድ አግኝታ አሁን 90 በመቶ የሚሆነውን ዘይት ወደ ቻይና ትሸጣለች::
እ.አ.አ በ2023 የኢራን የነዳጅ ኩባንያዎች ከተጣራ ነዳጅ ኤክስፖርት 53 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የአሜሪካ ኢነርጂ መረጃ አስተዳደር አስታውቋል::
የሆርሙዝ ሰርጥ ለምን አሳሳቢ ሆነ?
የሆርሙዝ ባሕር የፋርስ ባሕረ ሰላጤን ከኦማን ባሕረ ሰላጤ እና ከአረብ ባሕር ጋር የሚያገናኝ ዋና የነዳጅ ማጓጓዣ መንገድ ነው:: በኢራን እና በኦማን መካከል ይገኛል:: በአካባቢው እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኩዌት እና ኢራቅ ባሉ ሀገራት የሚመረተው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለገበያ የሚቀርበው ከፍተኛ መጠን ያለው ድፍድፍ ዘይት በባሕር መስመሩ ይተላለፋል::
ታዲያ ከኢራን ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ እና ለዓለም ኢኮኖሚ ሌላ አስደንጋጭ ነገር እያመጣ ነው:: እንደሚታወቀው ድፍድፍ ዘይት ዋነኛ የኢኮኖሚ ክፍል ነው:: ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ መጨመር የሌሎች ሸቀጦችን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምግብ የሚውለው አንድ አምስተኛው ዘይት እና ከፍተኛ መጠን ያለው ጋዝ የሚተላለፈው በባሕሩ ዳርቻ ላይ ነው:: ያለው የትራፊክ ፍሰትም ረዘም ያለ መስተጓጎል ያስከትላል::
የዓለም ገንዘብ ድርጅት እንዳስታወቀው በዓመት አምስት በመቶ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር በዋና ዋና ኢኮኖሚዎች ላይ የአንድ ነጥብ አንድ በመቶ አማካይ የዋጋ ግሽበት ይጨምራል:: ይህም ከፍ ያለ የዋጋ ንረትን በማስተል ሸማቾችን ይጎዳል:: እንዲሁም ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ንረትን ለመግራት የወለድ ምጣኔን ከፍ እንዲያደርጉ ምክንያት ይሆናል:: ይህም የኢኮኖሚ ዕድገቱን የበለጠ ወደኋላ ያስቀራል::
አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው:: የጥቃቱ ማዕበል በመካከለኛው ምሥራቅ ዙሪያ የነዳጅ እና የጋዝ ማምረቻዎችን እንዲዘጉ አድርጓል:: ሳዑዲ አረቢያ ትልቁን የሀገር ውስጥ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዋን አራምኮን በኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ዘግታለች:: ከዓለም ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝ አምራቾች መካከል አንዱ የሆነው የኳታር ኢነርጂ የኤል ኤን ጂ ምርትን በማቆሟ የጋዝ ዋጋ ጨምሯል::
ግጭቱ የኃይል እና የማዳበሪያ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል:: በድሃ ሀገሮች የምግብ እጥረትን የስከትላል:: በተጨማሪም እንደ ፌዴራል ሪዘርቭ ባሉ ማዕከላዊ ባንኮች ላይ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል::
የነዳጅ አምራች ሀገራት (OPEC+) ቡድን ገበያውን ለማረጋጋት ከሚያዚያ ጀምሮ ምርትን ለማሳደግ ከሰሞኑ ባካሄዱት ስብሰባ ተስማምተዋል::
እንደ የአሜሪካ የኢነርጂ አስተዳደር መረጃ የአሜሪካ ቤንዚን አማካኝ ዋጋ ከአንድ ሳምንት በፊት በጋሎን ከሦስት ዶላር በታች ነበር፤ አሁን ላይ ወደ ከሦስት ነጥብ አምስት ዶላር ከፍ ብሏል::
በሕንድ ውስጥ መንግሥት ለቤት ጋዝ አቅርቦቶች ቅድሚያ ስለሚሰጥ ምግብ ቤቶች ሊዘጉ እንደሚችሉ እያስጠነቀቀ ነው:: ታይላንድ ለሲቪል ሠራተኞች የባሕር ማዶ ጉዞን አቋርጣለች:: የፊሊፒንስ መንግሥት ለአንዳንድ የመንግሥት ኤጀንሲዎች ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ በሳምንት ለአራት ቀናት ብቻ ሥራ እንዲሠሩ ይፋ አድርጓል:: ቬትናምም ሰዎች ከቤት ሆነው እንዲሠሩ እያበረታታች ነው::
የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ባልደረባ እና የ2024 እ.አ.አ የኖቤል መታሰቢያ ሽልማትን በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ተሸላሚ የሆኑት ሳይመን ጆንሰን “የሆርሙዝ መስመር እንደገና መከፈት እንዳለበት በማሳሰብ “በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ዘይት የሚተላለፍበት መንገድ ነው:: በዓለም ላይ ይህን ክፍተት ሊሞላ የሚችል ምንም ትርፍ አቅም የለም” ነው ያሉት::
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሞኑ ባወጣው መረጃም የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ መዘጋት የነዳጅ እና የሸቀጦች ዋጋ እንዲያሻቅቡ ያደርጋል:: መረጃው እንደሚለው 20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ዘይት በዚህ ማነቆ ውስጥ ያልፋል:: በመሆኑም መስተጓጎሎች ካጋጠሙ ወዲያውኑ በተጣራ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ያስከትላል:: ይህ ትራንስፖርትን ምግብን ጨምሮ በአህጉሪቱ ላይ የዋጋ ንረትን ያስከትላል::
የኢነርጂ ደኅንነት ስጋቶችንም ይፈጥራል፤ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወደብ ለሌላቸው ሀገራት የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ከባድ ተጽዕኖን ያስከትላል::
የነዳጅ እጥረት የግብርና ምርትን በተለይም የሜካናይዝድ እርሻ እና የማዳበሪያ ትራንስፖርትን ሊያስተጓጉል ይችላል:: የአምራች ኢንዱስትሪዎች በተለይም በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚሠሩትን የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ይጨምርባቸዋል::
የአቪዬሽን ዘርፉም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይወድቃል:: በአጠቃላይ ጫናዎቹ ተደማምረው የኢኮኖሚ ዕድገትን ሊያዘገዩ እና የልማት ስትራቴጂን ሊያዳክሙ እንደሚችሉ ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ያመላከተው::
ይህ በእንዲህ እያለ ቢቢሲ ባወጣው መረጃ አሜሪካ፤ በሆርሙዝ ወሽመጥ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ 16 የባሕር ላይ ፈንጂ አጥማጅ መርከቦችን ጨምሮ በርካታ የኢራን ባሕር ኃይል መርከቦችን ማውደሟን አስታውቃለች::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢራን ለወዳጅ ሀገራት የሆርሙዝ ሰርጥን ክፍት እንደምታደርግ አስታውቃለች፤ በሌላ በኩል አሜሪካ ሰርጡን በጉልበት እንደምታስከፍተው ነው ያስታወቀችው:: “ተወደደም ተጠላም ሰርጡን ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም ክፍት እንደርገዋለን:: ለዚህም አማራጮችችን እያየን ነው” ሲል ያስታወቀው የአሜሪከው ወታደራዊ የመረጃ ማዕከል ነው::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


