የቤልጂየማውያንን ለምለሟን ኮንጎ በቅኝ ግዛት የመያዝ ፍላጎት ያነሳሳው ሄነሪ ሞርተን ስታንሌይ የተባለ አንድ ግለሰብ ነበር። እ ኤ አ በ1869 ዓ.ም በኮንጎ ጫካዎች ገብቶ የጠፋውን ዴቪድ ሊቪንግስተን የተባለን ሚሲዮን (መልዕክተኛ) እና አሳሽ እንዲፈልግ የ28 ዓመቱ ወጣት ጋዜጠኛ ስታንሌይ ወደ ኮንጎ ይላካል።
ስታንሌይ እግሩ የኮንጎን አፈር እንደረገጠ የደጋግ ኮንጓውያንን ወዳጅነት አግኝቶ ቤተኛ ሆነ፡፡ እየተላመደ ሲሄድ ግን የመጣበትን ዓላማ እስኪረሳ ድረስ በኮንጎ ድንግል የተፈጥሮ ውበት እና ተዝቆ በማያልቅ ሀብት ቀልቡ ተሰረቀ። የኮንጎን ከራስ እስከ እግሯ የሞላውን የተፈጥሮ ሀብቷን አስተዋለ። ጥቅጥቅ ደኗ፣ ከርሰ ምድሯ ያረገዛቸው የትየለሌ ውድ ማእድናት አማለሉት፤ ዋጋቸውን በረብጣ ዶላሮች ሲያሰላው ራሱን ያዘ፤ እናም አእምሮው ኮንጎን ለአውሮፓ ከበርቴዎች አጫርቶ ሊከብርባት አሴረ።
እንግሊዝን ለመደለል ቢሞክርም አልተሳካም። በመቀጠል ፊቱን ወደ ቤልጂየሙ ንጉሥ ሊዮፖልድ አዞረ። በኮንጎ ተፋሰስ አካባቢ በተፈጥሮ ሀብት የተሞላ ነፃ ለም መሬት መኖሩን በመንገር አማለለው። ንጉሡም ምራቁን እስኪውጥ ድረስ በመጎምዠት ተስማማ፤ በዚያውም ስታንሌይን ወኪል አድርጎ ተዝቆ በማያልቅ ደመወዝ ቀጠረው። የቤልጂየሙ ንጉሥ ዳግማዊ ሊዮፖልድ የሀገሩን የንግድ ድርጅቶች ወደ ኮንጎ እንዲሄዱ ጎተጎታቸው።
ስታንሌይ አስቀድሞ ከሀገሬው ሕዝብ ጋር አያሌ ስምምነቶችን እና ውሎችን መፈራረም ችሏል። ገራገር ኮንጓውያን፣ በእነዚህ ስምምነቶች አማካይነት መሬታቸውን እንደዋዛ ለባእድ አሳልፈው መስጠታቸውን እና በራሳቸው ላይ የባርነት ቀንበር መጫናቸውን ልብ አላሉትም። ስታንሌይ ወለል አድርጎ በከፈተላቸው በር ኮንጎ የገቡት የቤልጂየም የንግድ ኩባንያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የኮንጎን ሀብት ማፈስ ጀመሩ፤ ንጉሥ ሊዮፖልድ የገንዘብ ካዝናው በሀብት ተጨናነቀ። ከጅምሩ በሀብት ልቡ የሰከረው ንጉሥ ከሁለት አስርት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ሀገሪቱን በግል ንብረትነት ይዞ ቀጥቅጦ ገዛት፣ ሀብቷን ዘረፈ፣ ሕዝቧን በዘበዘ፡፡ ሲጥግብም ለቤልጅየም መንግሥት የቅኝ ግዛት ዳረጎት አድርጎ አስተላለፋት፤ ለተጨማሪ ብዙ አስርት ዓመታት ማቀቀች። ሆኖም ለዓመታት በተደረገ ትግል በፓትሪስ ኤምሪ ሉሙምባ መሪነት እና በሌሎች ታጋይ ልጆቿ ተጋድሎ የ80 ዓመታት የቅኝ ግዛት ቀንበር ተሰባበረ፡፡
በኮንጎ ውስጥ ቢያንስ 250 የሚሆኑ የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን ወደ 250 የሚጠጉ ቋንቋዎችንም ይናነገራሉ። የባንቱ (Bantu) ቋንቋዎች በብዛት የሚነገሩ ሲሆን 80% የሚሆነው ሕዝብ ይጠቀምባቸዋል። ፈረንሳይኛ የሀገሪቱ የሥራ ቋንቋ ሲሆን በንግድ፣ በሕግ በፖለቲካ እና በትምህርታዊ ጉባኤዎች ላይ ያገለግላል። ከፈረንሳይኛ በተጨማሪ ኮንጎ አራት ብሔራዊ ቋንቋዎች አሏት፤ እነሱም፦ ኪኮንጎ (Kikongo)፣ ሊንጋላ (Lingala)፣ ስዋሂሊ (Swahili) እና ትሺሉባ (Tshiluba) ሲሆኑ እነዚህም እንደ ክልላዊ መገናኛ ቋንቋዎች ያገለግላሉ።
ኮንጎ እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ፣ በመላው ዓለም በሚገኙ ሙዚየሞች (ቤተ መዘክሮች) ውስጥ በሚታዩ ጥንታዊ ቅርጻ ቅርጾች ትታወቃለች። የጥበብ ዘይቤዎች ብዝሃነት እና የምርቶቹ ብዛት ኮንጎን ልዩ የጥበብ ሀብት ማዕከል እና ከባህላዊ ጥበባት አንጻር በጥቁር አፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም ያደርጋታል።
በአፍሪካ አህጉር እምብርት ላይ የምትገኘው የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በውስጧ በያዘችው ግዙፍ ሀብት ሁልጊዜም የዓለምን ትኩረት ስትስብ ትኖራለች። ተፈጥሮ የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ማዕድን ሁሉ በአንድ ምድር ላይ አከማችታ የሰጠቻት ምድር ናት።
ዓለማችን ከአካባቢ ብክለት ለመውጣትና ወደ ታዳሽ ኃይል ለመሸጋገር በምታደርገው ጥረት ውስጥ ኮንጎ ዋነኛዋ ተዋናይ ናት። በተለይም የኤሌክትሪክ መኪናዎች (EVs) እና ዘመናዊ ስልኮች ባትሪ ለማምረት ወሳኝ የሆነው ኮባልት 70 በመቶው የሚመረተው በኮንጎ ነው። ያለ ኮንጎ ኮባልት የአፕል፣ የቴስላ እና የሳምሰንግ ፋብሪካዎች ሥራቸውን ሊቀጥሉ አይችሉም። ከኮባልት በተጨማሪ ለኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አነስተኛ የኤሌክትሪክ ፍሰት መቆጣጠሪያ የሚሆነው ኮልታን (Coltan) 80 በመቶው የዓለም ክምችት የሚገኘው ኮንጎ ውስጥ ነው።
ኮንጎ ከ24 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ጥቅም ላይ ያልዋለ የማዕድን ክምችት እንዳላት ይገመታል። ይህ ቁጥር ከአሜሪካ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ጋር የሚስተካከል ነው። ወርቅ፣ አልማዝ፣ መዳብ እና አሁን ደግሞ ለአረንጓዴ ኢነርጂ (ኃይል) ወሳኝ የሆነው ሊቲየም በብዛት ይገኙባታል። ሆኖም ይህ ግዙፍ ሀብት ለኮንጎ ሕዝብ የፈጠረው ዕድል ከችግሩ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ ነው።
የኮንጎ የማዕድን ዘርፍ በሁለት እጅግ የተራራቁ ጎራዎች የተከፈለ ነው። በአንድ በኩል ዘመናዊ ማሽነሪዎችንና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ካፒታል የያዙ የውጭ ኩባንያዎች ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ “አርቲዛናል ማይኒንግ” የሚባለውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በባዶ እጃቸው የሚቆፍሩበት ዘርፍ አለ።
በዚህ በሰው ጉልበት ላይ የተመሰረተ ቁፋሮ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተሰማሩ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ይገኙበታል። እነዚህ ዜጎች ያለምንም የደህንነት መጠበቂያ በጠባብና በማንኛውም ሰዓት ሊናዱ በሚችሉ ጉድጓዶች ውስጥ ገብተው ማዕድን ያወጣሉ። የሚገርመው ግን በዓለም ገበያ በአስር ሺዎች የሚሸጠው ማዕድን ለእነዚህ ቆፋሪዎች በቀን ከሁለት ዶላር የማይበልጥ ገቢ ነው የሚያስገኝላቸው። በተጨማሪም በምሥራቃዊ ኮንጎ የሚገኙ አማፂ ቡድኖች እነዚህን የማዕድን ቦታዎች በመቆጣጠር ለጦር መሣሪያ መግዣና ለግጭት መቀስቀሻነት ይጠቀሙባቸዋል። ይህ ሁኔታ “የደም ማዕድናት” (Blood Minerals) የሚለውን አሳዛኝ ስም ለሀገሪቱ ሀብት ሰጥቶታል።
ለመሆኑ “አረንጓዴ ሳንባ” የምንለው ምንድን ነው?
የኮንጎ ፀጋ በማዕድን ብቻ የተገደበ አይደለም። ሀገሪቱ ከአማዞን ደን ቀጥሎ የዓለም ሁለተኛው ትልቁ የዝናብ ደን ባለቤት ናት። አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ የኮንጎ ተፋሰስ ደን (Congo Basin) “የዓለም ሁለተኛው ሳንባ” በመባል ይታወቃል። ደኑ በዓመት ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በመምጠጥ የምድርን ሙቀት ለመቀነስና የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ወደር የሌለው ሚና ይጫወታል።
ይህ ደን የሰው ልጅ እስካሁን ያልደረሰባቸውንና በሌላ የዓለም ክፍል የማይገኙ ብርቅዬ ፍጥረታትን ይዟል። እንደ ኦካፒ (ከቀጭኔና ከሜዳ አህያ የተዳቀለ የሚመስል እንስሳ)፣ የደጋ ጎሪላዎች እና ቦኖቦ የተባሉ ዝንጀሮዎች መኖሪያ ነው። በተጨማሪም ከ10 ሺህ በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች በውስጡ ይገኛሉ። ሆኖም ይህ የተፈጥሮ ሀብት በህገ-ወጥ የዛፍ መቆረጥና በማዕድን ቁፋሮ ምክንያት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠር ሄክታር መሬት እያጣ ይገኛል። የደኑ መጥፋት ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት ትልቅ መርዶ ነው።
የኮንጎ ወንዝ በውሃ መጠኑ በዓለም ሁለተኛው ቢሆንም በውስጡ የያዘው የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ግን ወደር የለውም። በወንዙ ላይ የሚገኙት የኢንጋ ፏፏቴዎች ብቻ ቢለሙ 100 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይችላሉ። ይህ ኃይል መላውን አፍሪካ አልፎም አውሮፓን በኤሌክትሪክ የማጥለቅለቅ አቅም አለው። ሆኖም የሚገርመው ሀቅ ኮንጎ ይህን ሁሉ አቅም ይዛ 90 በመቶው ሕዝቧ ዛሬም ድረስ በጨለማ ውስጥ መኖሩ ነው።
ይህ የሀብትና የድህነት ተቃርኖ የሚመነጨው ከመሠረተ ልማት እጥረት፣ ከሙስና እና ከረዥም ዓመታት የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው። ሀገሪቱ ማዕድናቷን በጥሬው ወደ ውጭ በመላክ (Exporting raw materials) እንጂ እሴት በመጨመር (Value addition) ላይ ባለማተኮሯ ከሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ትርፍ ሳታገኝ ቀርታለች።
ምንም እንኳን ፈተናዎቹ ቢበዙም፣ በኮንጎ አዲስ የለውጥ መንፈስ እየታየ ነው። መንግስት ማዕድናትን በጥሬያቸው ወደ ውጭ መላክን ለመቀነስና በሀገር ውስጥ የማጣሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ፖሊሲዎችን እያወጣ ነው። ከዛምቢያ ጋር በመተባበር የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረው እንቅስቃሴ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ አቅም አለው።
በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተቋማት የኮንጎን ደን ለመጠበቅ ለሀገሪቱ የገንዘብ ድጋፍ (Carbon Credits) እንዲሰጡ የሚደረገው ጥረት ደኑን ሳይመነጥሩ ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል መንገድ እየከፈተ ነው።
የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የተፈጥሮ ሀብት ለኮንጎ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ህልውና ወሳኝ ነው። የዓለማችን የቴክኖሎጂ ጉዞና የአየር ንብረት ጤናማነት በኮንጎ ሰላምና ልማት ላይ የተመሰረተ ነው። ኮንጎ ስትለማ አፍሪካ ትለማለች፤ ኮንጎ ስትረጋጋ ደግሞ የዓለም የቴክኖሎጂ ፍሰት የተስተካከለ ይሆናል። በመሆኑም የኮንጎን ሀብት ከ”እርግማን” ወደ “በረከት” ለመቀየር ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት፣ የሰላም መስፈን እና በሰው ኃይል ላይ የሚካሄድ ልማት የግድ አስፈላጊ ነው። ኮንጎ የአፍሪካ ግዙፍ ልብ ናት፤ የዚህ ትርታ መስተካከል አህጉሪቱን ያነቃቃታል።
አጭር እውነታ
የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አጫጭር እውነታዎች፦
- ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ናት፣ በአፍሪካ ትልቁ ከተሞች መካከል አንዱ ናት።
- የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በመሬት መጠን በአፍሪካ ሁለተኛ ትልቅ አገር ናት (ከ አልጄሪያ በኋላ)።
- ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አለባት፣ በአፍሪካ ብዙ ህዝብ ያላት አገሮች መካከል ናት።
- የኮንጎ ወንዝ በአፍሪካ ሁለተኛ ረጅም ወንዝ ሲሆን በውሃ መጠን በዓለም ከፍተኛዎች መካከል ነው። ።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


