ሳንባ ነቀርሳ፦መንስኤዎቹ እና መፍትሔዎቹ

0
262

የሳንባ ነቀርሳ በሽታ መድሃኒትን በአግባቡ የወሰዱ ሰዎች 90 በመቶ ከበሽታው የመፈውስ እድል አላቸው::” ይህን ያሉን በባሕር ዳር ከተማ በጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም እና የሳንባ እና የፅኑ ሕሙማን ሰብ እስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ብሩክ ሙላት ናቸው:: ከዶ/ር ብሩክ  ጋር ስለሳንባ ነቀርሳ በሽታ ምንነት፣ ሕክምናዎቹ እና መፍትሔዎቹ በተመለከተ ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ!

ዶ/ር ብሩክ እንዳሉት የሳንባ ነቀርሳ (tuberculosis TB) በባክቴሪያ የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ነው:: ይህን በሽታ የሚያመጣው ማይኮባክቴሪየም ቱብረክሎሲስ (mycobacterium tuberculosis) የተባለ ባክቴሪያ ነው:: ባክቴሪያው አብዛኛውን ጊዜ ሳንባን የሚያጠቃ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ሌሎች ኣካላትንም ሊጎዳ ይችላል::

የሳንባ ነቀርሳ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው  በእርጥበት አዘል አየር ነው:: በሽታው ያለበት ሰው ሲስል፣ ሲያነጥስ፣ ሲዘፍን፣ ሲያወራ… ከአፉ የሚወጡ የአየር ቅንጣቶች (ኤር ድሮፕሌቶች)  ወደ ጤነኛ ሰው ይተላለፋሉ::

አጋላጭ ምክንያቶች

ባለሙያው እንዳሉት ለሳንባ ነቀርሳ የሚያጋልጡ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ::  ለአብነትም የመጀመሪያው የሳንባ ነቀርሳ የተገኘው በሰውየው አክታ ላይ ከሆነ  የማስተላለፍ አጋጣሚው  ከፍተኛ ይሆናል::

ሳሉ በጣም ከፍተኛ የሆነባቸው ሰዎች ነቀርሳውን ወደ ጤነኛ ሰው የማስተላለፋ  አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው:: አየር በሌለበት ቦታ እርስ በእርስ የመተፋፈግ ሁኔታ ካለም የመተላለፍ አጋጣሚው እየጨመረ ይሄዳል:: ይሁንና እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ተፈጥረው ባክቴሪያው ከሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ በሽታ አያመጣም:: በባክቴሪያው የተጋለጠው ሰው በበሽታው የሚጠቃው  ሌሎች አጋላጭ ምክንያቶች ሲኖሩ ነው::

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የሰዎች የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅም ዝቅተኛ ከሆነ እና ኤች አይቪ  በደማቸው ያለባቸው ከሆኑ ባክቴሪያው በሰውነት ውስጥ ከገባ ከሁለት ሳምንት በኋላ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል:: ከዛ ውጭ ሰውነት ውስጥ ባክቴሪያው እየተራባ ችግር ሳይፈጥር ከሳንባ ውስጥ የመቀመጥ  ዕድል ይኖረዋል:: በዚህም አንዴ ለሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ የታጋለጠ ሰው 10 በመቶ ያህል ሳንባ ነቀርሳው ወደ በሽታ የማደግ አጋጣሚ ይኖረዋል::

ምልክቶቹ

ወደ በሽታ ያደገ ቲቢ ወይም የሳንባ ነቀርሳ የተለያዩ ምልክቶችን ያሳያል:: የመጀመሪያውም ሳል ሲሆን ይሄም ሳሉ አክታ ያለውና የሌለው ሊሆን ይችላል:: የሰውነት ትኩሳት፣ ምግብ ማስጠላት፣ ማታ ላይ ከፍተኛ ላብ መኖር፣ ክብደት መቀነስ እና ድካም መሰማት ተጠቃሾች ናቸው:: የሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ የሳንባን መሸፈኛ አብሮ ሲያጠቃ ደረት ሰቅዞ የሚይዝ ህመም ማምጣትም ሌላው ምልክት ነው::

ሕክምናዎቹ

ዶ/ር ብሩክ እንደገለጹት የሳንባ ነቀርሳ ባጭር ጊዜ የሚታይ ምልክት ብቻ አይደለም የሚያመጣው:: በአብዛኛው  ሁለት ሳምንት እና ከዛ በላይ የሆነ ሳል ይኖረዋል:: ይህንን አይነት ምልክት በሚመጣበት ጊዜ የተለያዩ ምርመራዎች ይደረጋሉ:: እነሱም የደም፣ የአክታ እና የራጅ ምርመራዎች ናቸው:: በእነዚህ ምርመራዎች አንድ ታካሚ የሚያሳየው ምልክት በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት እንደሆነ ከተረጋገጠ ሕክምናዎች ይሰጣሉ:: በዋናነትም ለስድስት ወራት የሚቆይ መድሃኒት ይሰጣል::

ለሳንባ ነቀርሳ በሀኪም የሚታዘዙ መድሃኒቶች በትክክል ከተወሰዱ በኋላ 90 በመቶ ከበሽታው መዳን ይቻላል:: ነቀርሳ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ያጠቃል:: ስለዚህ ከስድስት ወራት በላይ  መድሃኒቱ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ነው ባለሙያው ያብራሩት:: በተለይም ከሳንባ ውጭ የነርቭ እና የአጥንት ነቀርሳ ሲሆን ከስድስት ወር በላይ መድሃኒቱ ይሰጣል:: የሰውነት የበሽታ የመከላከል አቅምን የሚጨምሩ ቫይታሚኖች እና የምግብ እጥረት ካለም አብረው ይሰጣሉ::

የሳንባ ነቀርሳ አይነቶች ከመድሃኒት አንጻር መድሃኒት የተላመዱ እና ያልተላመዱ በሚል  በሁለት እንደሚከፈሉ ነው ባለሙያው ያስረዱት:: መድሃኒት የተላመደ የሳንባ ነቀርሳ የሚባለው የመጀመሪያ ደረጃ መድሃኒቶችን ከእነሱ ውስጥ ለአንዱ ወይም ከአንዱ በላይ(አራት የመጀመሪያ ደረጃ የሳንባ ነቀርሳ መድሃኒቶች አሉ) መቋቋም ሲችል ወይም ባክቴሪያውን ሳይገድል ሲቀር መድሃኒት የተላመደ ቲቢ(የሳንባ ነቀርሳ) ይባላል::

ዶ/ር ብሩክ እንዳብራሩት በአብዛኛው መድሃኒት የተላመደ የሳንባ ነቀርሳ የሚከሰትበት ዋና ምክንያት ከዚህ በፊት የሳንባ ነቀርሳ መድሃኒት በወሰዱ ሰዎች ላይ ነው:: በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚከሰትበት ምክንያት በትክክል መድሃኒቱን ባለመውሰዳቸው፣ በዘፈቀደ የሕክምና ባለሙያ ሳያረጋግጥ መድሃኒት በመውሰዳቸው፣ በሳይንስ ከተጠናው ውጭ በተለያየ የጊዜ ሁኔታ እና መጠን ሲወሰድ መድሃኒት የተለማመደ ሳንባ ነቀርሳ ይከሰታል:: ስለዚህ በሕክምና ባለሙያ የታዘዘ እና የጊዜ ገደቡ የታወቀ መድሃኒት መውሰድ ይገባል::

ሌላው መድሃኒት የተለማመደ የሳንባ ነቀርሳ ታካሚ  ሰው ወደ ጤነኛ ሰው ማስተላለፍ ይችላል:: እንዲሁም የሳንባ ነቀርሳ መድሃኒት ለመጀመሪያ ጊዜ በሚወስዱ ሰዎች ላይ መድሃኒት የተለማመደው የሳንባ ነቀርሳ  ሊከሰት ይችላል:: ሆኖም ይህ ሁኔታ ግን በጣም ያልተለመደና አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው::

መከላከያዎቹ

ባለሙያው እንደሚሉት መድሃኒት የተላመደም ሆነ ያልተላመደ የሳንባ ነቀርሳን የምንከላከለው ታካሚዎች የታዘዘላቸውን መድሃኒቶች በአግባቡ መውሰድ ሲችሉ ነው:: በሚያስሉበት እና በሚያስነጥሱበት ጊዜም አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል::

ከሚስል ሰው አጠገብ  በምንሆንበት ጊዜ አካባቢያችንን ለንጹህ አየር ክፍት ማድረግ፣ መስኮቶችን እና በሮችን መክፈት ተገቢ ነው:: ወላጆች  ሕጻናትን የሳንባ ነቀርሳ መከላከያ ክትባት (BCG) ማስከተብ እንዳለባቸው ዶ/ር ብሩክ አስገንዝበዋል:: ኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኘባቸው  ሰዎችም መድሃኒታቸውን በአግባቡ በመውሰድ እና የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ  በሰውነት ውስጥ ያለውን የሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ ወደ በሽታ እንዳያድግ ማድረግ ይቻላል:: ለተጋላጭ አካላት ደግሞ የሳንባ ነቀርሳ መከላከል የሚባለውን ገና ወደ በሽታ ያላደገውን ቲቢ ወይም ሳንባ ነቀርሳ የሚያጠፋ መድሃኒት መስጠትም ይገባል:: ይህ በተለይ ለኤች አይ ቪ ታካሚዎች የሚደረግ ነው::

የሳንባ ነቀርሳ የሚከሰትበት ሌላው ምክንያት የምግብ እጥረት ነው:: በተቻለ መጠን ሰውነትን የሚያዳብሩ ምግቦችን እንደ እንቁላል፣ ስጋ እና ወትት መመገብ ተገቢ  እንደሆነ ነው ባለሙያው ምክረ ሐሳብ የሰጡት::

የሳንባ ነቀርሳ የጎንዮሽ ጉዳቱ ወይም ሰውነት ላይ የሚያመጣው ችግር ዘርፈ ብዙ ነው እንደሆነም  ዶ/ር ብሩክ ጠቁመዋል:: አንዳንድ የሳንባ ነቀርሳ ችግሮች መድሃኒት በመውሰድ ብቻ የሚድኑ አይደሉም:: ሳንባ ላይ ጠባሳ ትተው ያልፋሉ:: እንዲያውም ሳይታከም የቆየ የሳንባ ነቀርሳ ጉዳቱ እስከ ካንሰር ሊያደርስ ይችላል:: በመሆኑም ማንኛውም ሰው ምለክቶቹን እንዳዬ በፍጥነት ወደ ሕክምና ቦታ ከሄደ በቀላሉ ሊድን ይችላል::

 

ጤና አዳም

የሳንባ ነቀርሳ

  • የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ይታመማሉ፡፡ ሊታከም  እና ሊድን የሚችል በሽታ ቢሆንም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡ ይህም የዓለማችን ቀዳሚ ተላላፊ ገዳይ በሽታ አድርጎታል፡፡

 

  • ቲቢ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ላለባቸው ሰዎች ቀዳሚው የሞት ምክንያት ነው፡፡
  • አብዛኛዎቹ በቲቢ የታመሙ ሰዎች ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ይኖራሉ፡፡
  • ሳንባ ነቀርሳ አብዛኛውን ጊዜ ሳንባን የሚያጠቃ ቢሆንም ኩላሊትን፣ አዕምሮን እና አከርካሪን ሊጎዳ ይችላል፡፡
  • እ.አ.አ. በ2024 በግምት 10 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች በቲቢ በሽታ ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ወንዶች ፣ ሦስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሴቶች እና አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕጻናት ናቸው፡፡
  • እ.አ.አ. በ2024 በአጠቃላይ አንድ ነጥብ 23 ሚሊዮን ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) ሞተዋል፡፡ ታዲያ ከነዚህ ውስጥ 150 ሺህ የሚሆነው ኤች አይ ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
  • እ.አ.አ ከ2000 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቲቢን ለመከላከል የተደረገው ጥረት ወደ 83 ሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎችን ሕይወት መታደግ ችሏል፡፡
  • ሳንባ ነቀርሳን በጊዜው መታከም የበሽታውን ስርጭት ለማስቆም እና የማገገም እድሉን ለማሻሻል ይረዳል።

 

ምንጭ ፡-የዓለም የጤና ድርጅት።

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here