የተፈታኝ ተማሪዎች ቅድመ ዝግጅት

0
127

በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ትምህርት ቀዳሚው ነው፤ ችግሩም ሚሊዮን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ አርቋል፤  ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩትም ተገቢውን ዕውቀት በአግባቡ እንዳያገኙ አድርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ የትምህርት እንቅስቃሴውም መሻሻልን አሳይቷል፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የአንደኛውን ወሰነ ትምህርት በገመገመበት ወቅት ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው፡፡ ቢሮው በተለይ ክልላዊ እና ብሔራዊ ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ነው ያስታወቀው፡፡ እኛም ይህንኑ መነሻ በማድረግ በባሕር ዳር ከተማ ዕውቀት ፋና አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት በመገኘት የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ በአካል በመገኘት ተመልክተናል፤ ከተማሪዎች እና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋርም ቆይታ አድርገናል፡፡

ሐሳባቸውን ያካፈሉን የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዳሉን ለክልላዊ ፈተናው እየተዘጋጁ ነው፤ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን በማንሳትም ይህንን ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

በባሕር ዳር ከተማ በዕውቀት ፋና አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ኤልዳና አበበ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ያስመዘገበችው ውጤት 91 ነጥብ ሰባት በመቶ  ነው፤ ተማሪዋ ይህን ውጤት ለማግኘት ያስቻላት ደግሞ በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት መከታተሏ፣ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀም ማጥናቷ እና ከመምህራን እንዲሁም ከወላጆቿ ያገኘችው ድጋፍ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ከጓደኞቿ ጋር መረዳዳቷ እዳገዛት ነው ያነሳችው፡፡ በቀጣይም ለሚካሄደው የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የተሻለ ዝግጅት እያደረገች መሆኗን ገልጻለች።

ዮሐንስ ቻላቸው ሌላው ሐሳቡን ያካፈለን የዚሁ ት/ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነው፤ ተማሪ ዮሐንስ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት 87 በመቶ ውጤትም አስመዝግቧል። ይሁን እንጂ ይህ ውጤት እንዳላስደሰተው የተናገረው ተማሪው፣ በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ሙሉ አቅሙን በመጠቀም ትኩረት አለመስጠቱን በምክንያነት አንስቷል፡፡ ይህም ቁጭትን ፈጥሮበታል፤ ቁጭቱ ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ለሚወስደው ክልላዊ ፈተና የተሻለ እንዲዘጋጅ ስንቅ እንደሆነው ነግሮናል፤ የቤተሰቡና የመምህራን ድጋፍ እንደማይለየውም አክሏል።

መምህርት ፍቅርተ ገብረመስቀል በት/ቤቱ የሕብረተሰብ ሳይንስ መምህር እና የተማሪዎች አማካሪ ናቸው፤ እርሳቸው  እንደገለጹት ተማሪዎች በቀለም ትምህርት ያላቸው መረዳዳት መልካም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በትምህርት ቤቱ ክበባት የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ በተለይ እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕላቸው ጠንካራ መሆኑ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ የክበባት ተሳትፏቸው ደግሞ ሀሳባቸውን የመግለጽ አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል፤ ለዚህ አብነት ደግሞ ከላይ ሐሳቧን ያካፈለችን ተማሪ ኤልዳና አንዷመሆኗን መምህሯ አንስተውልናል፡፡

ተማሪዋ በተጨማሪም በት/ቤቱ ሚኒ ሚዲያ ክለብ ውስጥ በመሳተፍ ትምህርታዊ መልዕክቶችን ለማቅረብ የምታደርገው ሙከራ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋ እንዲሁም ለጓደኞቿ የምታደርገው ድጋፍ እጅግ አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል።

መምህሯ የተማሪዋን አርዓያነት ቢያነሱም የበርካታ ተማሪዎች መገለጫ እንደሆነም ነው የተናገሩት፤ በተለይ ተፈታኝ ተማሪዎች የተሻለ ዝግጅት እንዲያደርጉ እያገዟቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡

በት/ቤቱ የጀኔራል ሳይንስ መምህር የሆኑት መለሰ ስዩም በበኩላቸው ተማሪዎቹ በክፍል ውስጥ የሚያሳዩት የትምህርት ክትትልና ተሳትፎ ከፍተኛ ነው ብለዋል። በተለይም ለ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ተፈታኞች የማጠናከሪያ ትምህርት ተጠናክሮ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ከማጠናከሪያ ትምህርቱ ጎን ለጎንም የልምምድ ጥያቄዎችን ይሠራሉ፤ በመሆኑም የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ተስፋ አለኝ ብለዋል።

የት/ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ከፍያለው ቃሉ በበኩላቸው፣ ተማሪዎችን በዕውቀት ብቁ ለማድረግና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በት/ቤቱ የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ ርእሰ መምህሩ ማብራሪያ በተለይም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና የሚወስዱ ተፈታኞችን ለማብቃት ከመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ሌሎች የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች (የማጠናከሪያ) ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ቅዳሜ ቀን በተመረጡ መምህራን እና በተመረጡ ትምህርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ወርክሽቶችን በማዘጋጀት ተማሪዎች አንዲሠሩ ይደረጋል፤ ተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን በመስጠትም ተማሪዎችን ለፈተና እያዘጋጁ ነው።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ ከፍያለው ቃሉ እንደነገሩን በትምህርት ዘመኑ 240 የ8ኛ ክፍል እና 236 የ6ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለክልላዊ ፈተና በብቃት ለማስፈተን ዝግጅት እየተደረገ ነው። ውስን የመጻሕፍት እጥረት ቢኖርም በኮፒ በማባዛት እና በት/ቤቱ ቤተ መጻሕፍት በማስቀመጥ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ተደርጓል። ተማሪዎች በቃል የተማሩትን ትምህርት ንድፈ ሀሳብን ከተግባር ጋር በማስተሳሰር ለውጤታማነት እየተጉ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እና የልፋት ውጤታቸውን እንዲያገኙ ደግሞ ከትምህርት ቤቱ ባሻገር ማህበረሰቡና ሌሎች አጋር አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

 

አማርኛ በአማርኛ

ቆፈን – ብርድ

አጎጠጠ – ናቀ

ባጥ – ጣራ

ንዋይ – ገንዘብ

ባተሌ – ታታሪ፣ ለፍቶ አዳሪ

ፍዳ – መከራ።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here