ተስፋ ሰጪዉ መድሃኒት

0
56

ከባድ የሚጥል በሽታ ላለባቸው ልጆች ዘረመል ላይ ተመስርቶ በምርምር የተገኘ “ዞሬቨነርሰን” የተሰኘ መድሃኒት የበሽታውን ድግግሞሽ 91 በመቶ በመቀነስ የታካሚዎቹን ጤንነት ማሻሻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመረጃ ምንጭነት ለህትመት እንዳበቃው ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጡ ተመራማሪዎች የተገኘው መድሃኒት የሚጥል በሽታ የሚከሰትበትን ድግግሞሽ 91 በመቶ መቀነስ አስችሏል::

ከባድ የሚጥል በሽታ የተለያዩ የእለት ተእለት የእንቅስቃሴ ችግሮችን ከማስከተል ባለፈ ለሞት የሚያበቃ መሆኑም ነው የተገለፀው፤ ከዚህ በፊት ለችግሩ መፍትሄ አለመገኘቱንም ጠቁመዋል- ተመራማሪዎቹ::

የጤና ችግሩ መንስኤ ለሰዎች  ከሚያስፈልጉ ሁለት የፕሮቲን ዓይነቶች አንዱ በበቂ መጠን አለመመረቱ መሆኑን የተገነዘቡት ተመራማሪዎቹ ለጤናማ የነርቭ ስርዓት አስፈላጊ የሆነው ፕሮቲን በበቂ መጠን እንዲመረት የሚያስችል መድሃኒት ነው ያዘጋጁት::

መድሃኒቱ ከሁለት እስከ አስራ ስምንት ዓመት እድሜ መካከል ለሚገኙ የጤና ችግሩ ላለባቸው ልጆች ተሰጥቷቸው ውጤቱ መመዝገቡንም አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ::

በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የምርምሩ መሪ ኘሮፌሰር ሄለን ክሮስ፣ የህፃናት የነርቭ ህክምና የክብር አማካሪ አዲሱ መድሃኒት ለከባድ የሚጥል በሽታ የተዳረጉ ልጆችን ጤና በማሻሻል ደስተኛ ህይወት እንዲመሩ ማስቻሉን ገልጸዋል::

ፕሮፌሰር ሄለን ክሮስ የአዲሱ መድሃኒት ግኝት ሁለት ደረጃዎችን ማለፉን እና አሁን ባለበት ለመጨረሻ (ሦስተኛ) ደረጃ ግምገማ መቅረቡን  አስታውቀዋል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 7  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here