ሳቮ ምሥራቅ ብሔራዊ ፓርክ

0
52

ሳቮ ምሥራቅ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምሥራቅ ኬኒያ በቮይ ከተማ አቅራቢያ ታይታ ታቬታ አውራጃ ነው የሚገኘው:: የምስረታ ጊዜው 1948 እ.አ.አ ሲሆን ስፋቱ 13 ሺህ 747 ኪሎ ሜተር ስኩዌር ተለክቷል::

በፓርኩ ቀጣና ሜዳማ የሳር መሬት ይበዛዋል፤ አቲ እና ሳቮ የተሰኙ ወንዞች ተገናኝተው አቲ ሳባ ገላና የተሰኘ ወንዝ ፈጥረው ያረሰረሱታል፤ ቀጣናውን:: በፓርኩ ከዱር እንስሳት በአካል ግዝፈት ካላቸው ዝሆን፣ አንበሳ፣ ጐሽ፣ አውራሪስ እና ጉማሬ መኖራቸው ተረጋግጧል::

አእዋፍን በተመለከተም 50 የተለያዩ ዝርያዎች መገኛ ሲሆን የሶማሌ ሰጐን፣ የታይታ ጭልፊት ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም:: ፓርኩ ቀደምት የማሳይ ኗሪዎች መገኛ ነው:: በአለባበሳቸው ለየት ያሉ የተለየ ወግ እና ልማድ ያላቸው በመሆናቸውም ጐብኚዎችን ሳቢ ናቸው::

በፓርኩ ቀጣና አቦ ሸማኔ የሜዳ ፍየል፣ ሰጐን የመሳሰሉትን አድኖ ለመያዝ የሚያደርገውን የሩጫ ትርኢት መመልከት ለጐብኚዎች አይረሴ ገጠመኝ ነው::

በሳቮ ምሥራቅ ብሔራዊ ፓርክ ከዓመቱ ሰፊው ወቅት ደረቅ እና ሞቃት ዓየር ንብረት ጥቂት ከፍታ ባላቸው ቦታዎች ደግሞ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ነው የሚስተዋልባቸው::

በሳቮ ምሥራቅ ብሔራዊ ፓርክ ከታኅሣሥ እስከ መጋቢት እንዲሁም ከሰኔ እስከ ጥቅምት ያሉት ደረቅ ወራት ናቸው::

ወደ ፓርኩ ለመጓዝ በተሽከርካሪ ከናይሮቢ ሞምባስ 333 ኪሎ ሜትር፣ ከዚያም 173 ኪሎ ሜትር ተጉዞ መድረስ ይቻላል:: በባቡር ከናይሮቢ ሞምባሳ ደርሶ ወደ ፓርኩ ደግሞ በቻርተር አውሮኘላን በመብረር ይደረሳል::

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ዋይልድዎንደር ሳፈሪ፣ ወንደረስ አፍሪካ፤ ሳቮ ናሽናል ፓርክ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 7  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here