የአገልግሎት አሰጣጡ ተጠናክሮ ይቀጥል፤ ወደ ሌሎች ተቋማትም ይስፋፋ!

0
50

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተገንብቶ በአማራ ክልል አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ቀደም ሲል በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲን በማስቀረት ዜጎች በዘመናዊ መሣሪያ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ታቅዶ የተዘጋጀ ነው። እንደታሰበውም ተገልጋዮች ያለውጣ ውረድ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻላቸው ነው፡፡ ተገልጋዮቹ አገልግሎት ፈልገው ወደ ማዕከሉ ሲሄዱ ከበር ጀምሮ በመረጃ ሰጪዎች የሚደረግላቸው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ለጉዳያቸው ተገቢውን ትኩረት በመስጠት፣ አገልግሎቱን የሚያገኙበትን ቢሮ በማመላከት ረገድ በማዕከሉ ሠራተኞች ዘንድ የሚታየው መልካም ተግባር እንዳስደሰታቸው ተገልጋዮች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይደመጣሉ።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ የባለጉዳዮችን ምልልስ እና የቆይታ ጊዜን ለማስቀረት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሰልፍ መቆጣጠሪያ እና የዲጂታል ግብረ-መልስ መስጫ መሣሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ፣ የአገልግሎት ሰጪዎችን ብቃት ለመመዘን እና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ ማሻሻያ ለማድረግ አስችሏል። በዚህም እንግልትን እና መጉላላትን እያሰቡ ወደ ማዕከሉ የሚሄዱ ተገልጋዮች ባልተለመደ ሁኔታ ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘታቸው ደስታቸውን እና ርካታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የማዕከሉ ሠራተኞች ትህትና እና ግልጽነት ተገልጋዮች በትዕግስት እንዲጠባበቁ የሚያደርግ ስለመሆኑም ተገልጋዮች ሲገልጹ ይደመጣሉ።

ቀደም ሲል የነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት በስልጠና እና በስብሰባ ብቻ ሊታረም ያልቻለ እና የሕዝቡን እንግልት፣ ውጣ ውረድ እንዲሁም ቅሬታ እያባባሰ የመጣ በመሆኑ ችግሮቹን በጥናት በመለየት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል ማሰባሰብ እና አሠራሮችን ማዘመን የግድ መሆኑ ታምኖበት ወደ ተግባር ተገብቷል። በዚህም መሠረት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ጥናቶች እየተደረጉበት እና እየተፈተሹ የመጣ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ዝለት ያለባቸው፣ ተገልጋይ የሚበዛባቸው፣ ሙስና እና ብልሹ አሠራር የተንሰራፋባቸው እንዲሁም ቅሬታ የሚበዛባቸው ተቋማት ተለይተው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

ለእያንዳንዱ አገልግሎት ዝርዝር መለኪያ /ስታንዳርድ/ መውጣቱ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ይበልጥ ቀልጣፋ አድርጎታል። በአካልም ሆነ በበይነ መረብ (ኦንላይን) የሚሰጠው ይሄው አገልግሎት ተገልጋዩን ከተደጋጋሚ ቀጠሮ እና ካላስፈላጊ ወጪ ከመታደጉ ባለፈ በአንድ ተቋም ብቻ መቋጫ ለማያገኙ ጉዳዮች የተቀናጀ መፍትሔ በመስጠት ላይ ይገኛል።

መሶብ የአገልግሎት ማዕከል በቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ “ነገ ኑ” ቀጠሮን አስቀርቷል፡፡ ማዕከሉ ወደ ሥራ መግባቱ አገልግሎቱን የተቀናጀ እና ግልጽ በማድረግ ለሙስና እና ለብልሹ አሠራር ይዳርጉ የነበሩ አጋጣሚዎችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለማስቀረት ችሏል፡፡

አገልግሎቶቹ በአካል፣ በኦንላይን እና በአጭር የስልክ ጥሪ በኩል የሚሰጡ በመሆናቸው ተገልጋዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲያስፈጽሙ፣ ጊዜ እና ወጪያቸውን እንዲቆጥቡ እንዲሁም ርቀት ሳይገድባቸው ፍትሐዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ እያደረገ ነው።

ማዕከሉ በየሳምንቱ የተገልጋዮችን ግብረ መልስ የሚሰበስብበት የራሱ የክትትል ሥርዓትም አለው፡፡ የመረጃ ቅንጅትን እንደ ዋና ስልት በመጠቀም የተለያዩ ተቋማት መረጃዎቻቸውን እንዲያጋሩ በማድረግ ተገልጋዩ ከአንድ ቢሮ ወደ ሌላው የሚንከራተትበትን አሰልቺ አሠራርም እያስቀረ ነው፡፡ ይህ በእንክብካቤ እና በክብር ላይ የተመሠረተ አገልግሎት አሰጣጥ  ለሌሎች የመንግሥት ተቋማትም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም ወደ ሌሎች ተቋማት መስፋፋት ይኖርበታል፡፡

በኲር የመጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here