ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ ከሚጠራባቸው እና የገነነ ዝና ካተረፈችባቸው ዘርፎች መካከል አትሌቲክስ በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት ያሸበረቀው ሰንደቅ አላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ማየት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በባዕድ ሀገር ሲያስተጋባ መስማት ለዘመናት የሕዝባችን የጋራ ደስታ እና የማንነት መገለጫ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህ የስፖርት ዘርፍ ለሀገራችን ከሜዳሊያ ቁጥር እና ከስፖርታዊ ፉክክር ባለፈ ጥልቅ የሆነ ሀገራዊ ትርጉምም አለው፡፡ አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የዲፕሎማሲ ልዕልና እና የማህበራዊ ትስስር ምሰሶ በመሆን ለዘመናት አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱ ዘርፍ አትሌቶች ለሀገር ክብር ከመሮጥ ይልቅ የግል ጥቅምን ማሳደድ በግልጽ እየታየ መጥቷል፡፡
በርካታ አትሌቶች ሀገራቸውን ወክለው በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረኮች ላይ መሮጥ ሲገባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያስገኙ የግል የጎዳና ላይ ውድድሮችን፣ የማራቶን እና የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን ሲያሳድዱ በስፋት እያስተዋልን ነው፡፡ ለሀገር ጥሪ ሲደረግላቸው በተለያዩ ምክንያቶች (በተለይም በጉዳት ሰበብ) ጥሪውን ወደ ጎን የሚሉ አትሌቶች ቁጥርም በርክተዋል፡፡
በአትሌቲክስ ብሔራዊ ጥቅም ከሜዳሊያ ብዛት የዘለለ ጥልቅ ትርጉም ያለው ጽንሰ ሀሳብ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል፡፡ ብሄራዊ ጥቅም የሀገርን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይገነባል፡፡ የሕዝቦችን አንድነት እና ትስስርም ያጠናክራል፤ እንዲሁም የሀገር ፍቅር ስሜትን ያነቃቃል፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ሀገርን ወክሎ መሳተፍ እና ማሸነፍ የኢትዮጵያን ስም በአሸናፊነት እና በጀግንነት እንድትታወቅ ያደርጋል፡፡ ታዲያ ይህንን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሚቻለው ደግሞ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ የስፖርት ማህበራት እና መንግሥት በአንድ ልብ ሲሰሩ ብቻ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሰፖርት አሰልጣኙ ታምራት ታደሰ ከአሚኮ በኩር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡
አሰልጣኝ ታምራት “በሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር አትሌቶች ለሀገራቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚያበረታታ ሕግ እና አሰራር መዘርጋት ይገባል፤ ግዴታቸውን በማይወጡት ላይ ደግሞ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ይቻላል” ብሏል፡፡
በታዳጊዎች ስልጠና እና ስነ ልቦና ላይ ቅርብ ክትትል የሚያደርገው አሰልጣኝ ታምራት “አንድ አትሌት በሩጫው ራሱን እና ቤተሰቡን በኢኮኖሚ የመቀየር ዓላማ ቢኖረውም ከዚህ ሁሉ ባሻገር ማወቅ ያለበት ትልቁ ቁምነገር ከምንም በላይ የሚወክላት ሀገር እንዳለችው እና ክብሯን ማስጠበቅ ግዴታው መሆኑን መገንዘብ ነው” ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ማኔጀሮች አትሌቶችን የገንዘብ ማግኛ ማሽን ብቻ እያደረጓቸው መሆኑን አልሸሸገም፡፡
አትሌቶች ለግል ጥቅማቸው ሲሮጡ አቅማቸውን አሟጠው ስለሚጠቀሙ ለሀገር ጥሪ ሲደረግላቸው ማፈግፈግ ይጀምራሉ፡፡ “ይህ ችግር የሚፈተው እኛ አሰልጣኞች ስፖርታዊ ክህሎትን ብቻ ሳይሆን ሀገር ወዳድነትንም አብረን ስናስተምር ጭምር እና ትክክለኛውን መንገድ ስናሳይ ነው፤ ማኔጀሮችም የሀገሪቱን ሕግ ሲያከብሩ ብቻ ነው” ሲል አሰልጣኙ ይናገራል፡፡
ዘርፉ አጭር የውድድር ዘመን ያለው ሙያ እንደመሆኑ መጠን አትሌቶች ሀብት ማፍራት ቢገባቸውም ከግለሰብ በላይ የሆነችውን የሀገራቸውን ጥሪ በአክብሮት መቀበል እንዳለባቸው ግን አሰልጣኙ አልካደም፡፡ አብዛኛዎቹ ማኔጀሮች የውጭ ዜጎች በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ደንታ ይላቸውም፤ ትኩረታቸውም ከሚያገኙት ኮሚሽን ላይ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ማኔጀሮች የሀገሪቱን ብሔራዊ ፌዴሬሽን ሕግ ማክበር እና አትሌቶች በሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዳይሳተፉ የሚያደርጉትን ተጽዕኖ ማቆም እንዳለባቸውም አሰልጣኝ ታምራት ያስረዳል፡፡ አሰልጣኞችም የአካል ብቃት ስልጠናን መስጠት ብቻ ሳይሆን ስነ ምግባርን እና የሀገር ፍቅርን ለታዳጊዎች ማስተማር እንዳለባቸው አሰልጣኝ ታምራት ታደሰ ተናግሯል፡፡
ታሪክ በወርቅ ቀለም የሚጽፈው ለገንዘብ የሮጡትን ሳይሆን በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ ያደረጉትን ነው፡፡ አበበ ቢቂላ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና የመሳሰሉት በክብር የሚታወሱት በባንክ አካውንታቸው ባለው የገንዘብ መጠን ሳይሆን ለሀገራቸው ባመጡት ሜዳሊያ ነው፡፡
የአትሌቶች ጠንክሮ የመስራት፣ የጽናት እና ለሀገር ክብር የመሮጥ ባህል ለወጣቱ ትውልድ ተግባራዊ የሆነ የህይወት ትምህርት ቤት ነው፡፡ አንድ አትሌት በዐስር ሺህ ሜትር ውድድር ላይ ተስፋ ሳይቆርጥ ጥርሱን ነክሶ እና ላቡን ጠብ አድርጎ በመጨረሻዎቹ ሜትሮች ተፎካካሪዎቹን ቀድሞ ሲገባ ታዳጊዎች የሚማሩት ህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በጽናት የማለፍ ስነ ልቦናዊ አቅም ነው፡፡ “ኢትዮጵያዊነት ማለት ተስፋ አለመቁረጥ ነው፤ ላብን ጠብ አድርጎ ሠርቶ ማሸነፍ ጭምር ነው” የሚለውን ለተተኪዎች ያሳያል፡፡ አትሌቶች የሀገራቸውን ማሊያ ለብሰው ከግል ምቾታቸው ይልቅ ለሀገር ክብር ሲደክሙ ማየት ወጣቱ ትውልድ በየትኛውም የሙያ መስክ ቢሰማራ ሀገሩን እንዲያስቀድም እና በቅንነት እንዲያገለግል ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርለታል፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አትሌቶቻችን ድል ሲቀዳጁ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚታየው ልዩ የደስታ ስሜት እና አንድነት አትሌቲክስ ለብሔራዊ መግባባት ያለውን ጉልበት በግልጽ እንደሚያሳይ አሰልጣኝ ታምራት ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያውያን በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት እና በባህል የተለያዩ ሕዝቦች ቢሆኑም አንድ አትሌት የሀገሪቱን ስም ጠርቶ ሪባን ሲበጥስ በመላ ሀገሪቱ እና በውጭ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚፈጠረው የጋራ ደስታ ወደር የለውም፡፡ እናም አትሌቲክስ ማህበራዊ ልዩነቶችን አጥቦ ሕዝቦችን በአንድነት የማስተሳሰር፣ የሀገር ፍቅር ስሜትን የማጠናከር እና ለብሔራዊ መግባባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አሰልጣኙ ያብራራል፡፡
በአትሌቲክሱ ዘርፍ ብሔራዊ ጥቅምን አለማስቀደም እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረክ ያለንን የገጽታ ግንባታ ያቀጭጨዋል፡፡ ድል ስናጣ ባንዲራችን ዝቅ ይላል፤ በዓለም አደባባይ ያለን ተደማጭነትም ይቀንሳል፡፡ ታዲያ በዘርፉ የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር መንግሥት፣ የስፖርት ማህበራት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥብቅ እና አሳታፊ ፖሊሲ ወይም ስትራቴጂ ሊከተሉ ይገባል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማኔጀሮችን አሰራር የሚቆጣጠር ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ቀዳሚው ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አሰልጣኙ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ማኔጀሮች አትሌቶችን በውጭ ውድድሮች ሲያሳትፉ አትሌቶች ለብሔራዊ ግዳጅ በሚጠሩበት ጊዜ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቁ የሚያስገድድ የውል ስምምነትም ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ “በተቻለ አቅም ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶች አላስፈላጊ ውድድር ወይም የገንዘብ ውድድሮች ባያበዙባቸው ጥሩ ነው፤ በጊዜ ወደ ሆቴል ገብተው ሆቴል ላይ ክትትል ቢደረግባቸው” ሲል አሰልጣኙ ይመክራል፡፡
መንግሥትም ኢትዮጵያን ለሚወክሉ እና ስሟን ከፍ አድርገው በዓለም ዓቀፍ መድረክ ለሚያስጠሩ አትሌቶች የሚሰጠውን ማበረታቻ ማሻሻል አለበት- የአሰልጣኙ አስተያየት ነው፡፡ አትሌቶች የሀገር ጥሪ አልቀበልም ሲሉ ፌዴሬሽኑ የሚጥልባቸው ቅጣት ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታልም ነው የተባለው፡፡
አትሌትነት የጉልበት እና የወጣትነት ዘመን ሥራ በመሆኑ አትሌቶች የወደፊት ህይወታቸውን ዋስትና ባለው መልኩ ለመምራት ገንዘብ ማግኘት አለባቸው፤ ስለዚህ የግል ውድድሮችን ሙሉ በሙሉ መተው ሳይሆን ማመጣጠን እና ትክክለኛ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ለችግሩ አንዱ መፍትሄ ተደርጎ ተጠቁሟል፡፡ አትሌቶች እና አሰልጣኞቻቸው ከማኔጀሮች ጋር በመሆን ዓመታዊ የውድድር እቅድ ሲያወጡ ለሀገር አቀፍ ውድድሮች (እንደ ኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና ላሉት) በቂ የእረፍት እና የዝግጅት ጊዜ መመደብ እንዳለባቸውም አሰልጣኝ ታምራት ያስታውሳል፡፡ አትሌቲክስ የኢትዮጵያዊነት ህያው መታወቂያ በመሆኑ መታወቂያው እንዳይደበዝዝ የግለሰብ ስኬት ከሀገር ክብር በታች መሆኑን ለትውልዱ ማስታወስ የሁሉም የጋራ ሀላፊነት ነው፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


