የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች በሰው ልጅ የታሪክ መዝገብ ውስጥ እጅግ ዘግናኝ እና የጦርነትን መልክ የቀየሩ ኩነቶች ናቸው። እነዚህ ጥቃቶች የተፈጸሙት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በነሐሴ 1945 ዓ.ም ሲሆን ዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ያለውን አውዳሚ ኃይል የተረዳችበት አጋጣሚ እንደነበር የአሜሪካ ብሔራዊ አርካይቭ መረጃ ያመላክታል። ጥቃቱ የተፈጸመው በአሜሪካ ነው፡፡ ለዚህም ውሳኔ መነሻ የሆኑት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ምክንያቶች እስከ ዛሬ ድረስ በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ክርክር እየተደረገባቸው ነው።
የጥቃቱ ዋነኛ መንስኤ ተብሎ የሚጠቀሰው ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠቃለል ካለ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። በወቅቱ በፓሲፊክ ውቅያኖስ በኩል የሚካሄደው ውጊያ እጅግ አድካሚና የብዙዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ነበር። አሜሪካ ወደ ጃፓን ምድር በቀጥታ የምድር ጦር ወረራ ብታደርግ፣ የጃፓን ወታደሮች እስከ መጨረሻው የደም ጠብታ የመዋጋት ባህል ስላላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአሜሪካ እና የጃፓን ወታደሮች እንዲሁም ሲቪሎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር። በመሆኑም የአቶሚክ ቦምብን መጠቀም ጃፓንን በፍጥነት እጅ ለማሰጠትና የራሷን ወታደሮች ሕይወት ለመታደግ እንደ አማራጭ ተወሰደ።
ከዚህም በተጨማሪ ጃፓን በሐምሌ ወር 1945 የቀረበላትን የፖትስዳም መግለጫ (Potsdam Declaration) ውድቅ ማድረጓ ለጥቃቱ መፋጠን ምክንያት ሆኗል። ይህ መግለጫ ጃፓን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ እንድትሰጥ፣ ካልሆነ ግን “ፈጣን እና ፍፁም ጥፋት” እንደሚጠብቃት ያስጠነቅቅ ነበር። የጃፓን ወታደራዊ መሪዎች ግን ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለታቸው፣ ፕሬዝዳንት ሃሪ ትሩማን ቦምቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ትእዛዝ አስተላለፉ። በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ ከሶቪየት ህብረት ጋር በነበራት ሽኩቻ፣ የኒውክሌር የበላይነቷን በማሳየት በድህረ-ጦርነት የዓለም ፖለቲካ ላይ ጉልህ ሚና ለመጫወት ፈልጋ እንደነበር የብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒዲያ (መድብለ ጥበብ) መረጃ ያሳያል።
የመጀመሪያው ጥቃት ነሐሴ 6 ቀን 1945 በሂሮሺማ ከተማ ላይ ተፈጸመ። “ሊትል ቦይ” የተሰኘው የዩራኒየም ቦምብ ከ”ኢኖላ ጌይ” (Enola Gay) አውሮፕላን ላይ ተጥሎ በከተማዋ ሰማይ ላይ ሲፈነዳ በቅጽበት ከ70 ሺህ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ጋይተዋል። ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወደ አመድነት የተቀየረች ሲሆን እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በቃጠሎ እና በከፍተኛ የጨረር መጠን ምክንያት የሟቾች ቁጥር 140 ሺህ ደርሷል።
ከሦስት ቀናት በኋላ ነሐሴ 9 ቀን “ፋት ማን” የተባለው የፕሉቶኒየም ቦምብ በናጋሳኪ ላይ ተጣለ። ምንም እንኳን የናጋሳኪ መልክዓ ምድር ተራራማ መሆኑ የጥፋቱን መጠን ቢቀንሰውም ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ወዲያውኑ አልቀዋል።
እነዚህ ሁለት ጥቃቶች ጃፓንን ክፉኛ ያዳከሙና ተስፋ ያስቆረጡ ነበሩ። ጥቃቱን ተከትሎ ሶቪየት ህብረት በጃፓን ላይ ጦርነት ማወጇም ሁኔታውን ይበልጥ አባባሰው። በመጨረሻም ነሐሴ 15 ቀን 1945 የጃፓኑ ንጉሠ ነገሥት ሂሮሂቶ ሀገራቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እጅ መስጠቷን በሬዲዮ አስታወቁ። መስከረም 2 ቀን 1945 ዓ.ም የእጅ መስጠት ስምምነቱ በይፋ ሲፈረም ለስድስት ዓመታት የዘለቀውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አበቃ። ዛሬም ድረስ በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የሚገኙት “የሰላም መታሰቢያዎች” ለዓለም ሕዝብ የኒውክሌር ጦርነትን አስከፊነት የሚያስታውሱ ህያው ምስክሮች ናቸው።
የሂባኩሻ (Hibakusha) ታሪክ እና የጤና ተፅዕኖ
“ሂባኩሻ” ማለት በጃፓንኛ “በቦምብ የተመታ ሕዝብ” ማለት ሲሆን፣ ከአቶሚክ ቦምብ ጥቃቱ ተርፈው በሕይወት የቆዩትን ሰዎች ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች ከአካላዊ ጉዳት ባለፈ ለከፋ ማህበራዊ እና ጤናዊ ቀውስ ተዳርገዋል።
በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ የራዲዮአክቲቭ ጨረር (Radiation) በሰውነታቸው ውስጥ የካንሰር ሕዋሳት እንዲራቡ፣ የደም ካንሰር (Leukemia) እንዲከሰት እና የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅማቸው እንዲዳከም አድርጓል። ከዚህም በላይ በወቅቱ የነበረው ማህበራዊ መገለል ከፍተኛ ነበር፡፡ ብዙዎች “ተላላፊ በሽታ አለባቸው” ወይም “የሚወለዱ ልጆቻቸው አካል ጉዳተኛ ይሆናሉ” በሚል ፍራቻ ትዳር መመሥረት እና ሥራ ማግኘት ይቸገሩ ነበር። ዛሬ ግን እነዚህ ተራፊዎች (ከጥቃቱ የተረፉት) የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በዓለም ላይ እንዲጠፋ የሚታገሉ የሰላም አምባሳደሮች (እንደራሴዎች) ተደርገው ይታያሉ።
የማንሃተን ፕሮጀክት እና የኦፐንሃይመር ሚና
የአቶሚክ ቦምብ የተሠራው “የማንሃተን ፕሮጀክት” በሚባለው እጅግ ሚስጥራዊ በሆነ የአሜሪካ ወታደራዊ መርሃ ግብር ነው። ፕሮጀክቱ የተጀመረው ናዚ ጀርመን ቀድማ የኒውክሌር መሣሪያ ልትሠራ ትችላለች በሚል ስጋት ነበር። ሳይንሳዊ መሪው ጄ. ሮበርት ኦፐንሃይመር ሲሆን በሎስ አላሞስ ላቦራቶሪ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶችን በማስተባበር የመጀመሪያውን ቦምብ ሠርተዋል።
“ትሪኒቲ” የተባለው የመጀመሪያው የሙከራ ፍንዳታ እ.አ.አ. ሐምሌ 16 ቀን 1945 ዓ.ም በኒው ሜክሲኮ በረሃ በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል። ኦፐንሃይመር የፈጠረው መሣሪያ ያስከተለውን ጥፋት ሲመለከት፣ ከጥንታዊ የሂንዱ መጽሐፍ የተወሰደውን “አሁን እኔ ዓለማትን የሚያጠፋ ሞት ሆኛለሁ” የሚለውን ዝነኛ ጥቅስ ተናግሯል። ከጦርነቱ በኋላ ኦፐንሃይመር በፈጠራው ተፀፅቶ ይበልጥ አጥፊ የሆኑ የሃይድሮጅን ቦምቦች እንዳይሠሩ ተከራክሯል።
የጃፓን ትንሳኤ እና የኢኮኖሚ ተአምር
ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ሙሉ በሙሉ ወድማ ነበር። ከተሞቿ ፈርሰዋል፤ ኢንዱስትሪዎቿም ቆመው ነበር። ሆኖም ግን የጃፓን ኢኮኖሚ ተአምር በሚባል ሁኔታ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ተመንድጎ ጃፓንን ወደ ዓለም ኃያልነት መልሷታል።
ይህ ሊሆን የቻለው የዴሞክራሲ ሥርዓት በመዘርጋቷ፣ ወታደራዊ ወጪዋን በመቀነሷ እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በትምህርት ላይ ከፍተኛ የመዋለ ንዋይ ፍሰት በማድረጓ ነው። ጃፓን ከጦርነት ይልቅ በሰላማዊ መንገድ በኤሌክትሮኒክስ፣ በመኪና ምርትና በሮቦቲክስ ዘርፍ ዓለምን መምራት ጀመረች።
ዛሬ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ሙሉ በሙሉ ተገንብተው ዘመናዊ ከተሞች ቢሆኑም፣ የጥፋቱን ታሪክ ለትውልድ ለማስተማር ሲሉ አንዳንድ ፍርስራሾችን (እንደ ሂሮሺማ ፒስ ዶም ያሉ) ሳይነኩ አቆይተዋቸዋል።
ሳምንቱ በታሪክ
የራስ ዳርጌ ሕልፈት
ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ተሰሚነትና ክብር የነበራቸው ታላቅ መሪና የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ የቅርብ አማካሪ ነበሩ። ዳግማዊ ምኒልክ መቅደላ ታስረው በነበረበት ወቅት ራስ ዳርጌም እዚያው እስረኛ የነበሩ ሲሆን በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ምኒልክን በመምከር እና በማስተማር የቅርብ አለኝታቸው ነበሩ።
ዐፄ ምኒልክ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ራስ ዳርጌ የቤተ መንግሥቱ “ቁንጮ” እና የንጉሠ ነገሥቱ ዋነኛ የልብ ወዳጅ ሆኑ። ንጉሡ ማንኛውንም ትልቅ ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት አጎታቸውን ራስ ዳርጌን ያማክሩ ነበር። ራስ ዳርጌ በቅንነታቸው እና በትዕግስታቸው የሚታወቁ ሲሆን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ራስ ዳርጌ የአርሲን ግዛት ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ለመመለስ የተደረገውን እና አራት ዓመታት የፈጀውን አስቸጋሪ ውጊያ በበላይነት መርተዋል። አካባቢውንም ለረጅም ጊዜ አስተዳድረዋል። የዓድዋ ጦርነት በ1888 ዓ.ም ሲታወጅ ዐፄ ምኒልክ ራስ ዳርጌን ወደ ጦር ግንባር ይዘዋቸው አልሄዱም ነበር። ይህ የሆነው ራስ ዳርጌ በዕድሜ በመግፋታቸው ብቻ ሳይሆን ንጉሡ በሌሉበት ወቅት የአዲስ አበባን እና የሀገሪቱን ሰላም በኃላፊነት እንዲጠብቁ “እንደራሴ” ሆነው ስለተሾሙ ነው።
ራስ ዳርጌ መጋቢት 15 ቀን 1892 ዓ.ም በ70 ዓመታቸው አርፈው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ተቀብረዋል። እሳቸው ለኢትዮጵያ አንድነት እና ስኬት የነበራቸው አስተዋጽኦ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ በጉልህ ተጽፎ ይገኛል። ልጆቻቸውም (ለምሳሌ እንደ ደጃዝማች ካሣ ዳርጌ ያሉት) በኋለኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው ሲሉ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” በሚለው መጽሐፋቸው አትተዋል።
የባሪያ ንግድ መታገድ
የብሪታንያ የባሪያ ንግድ ማገጃ ሕግ በዓለም የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የሰው ልጅ ንግድን ለማስቆም የተወሰደ የመጀመሪያው ትልቅ ሕጋዊ እርምጃ ሲሆን በብሪታንያ ፓርላማ የጸደቀው መጋቢት 16 ቀን 1799 ዓ.ም ወይም በፈረንጆቹ መጋቢት 25 ቀን 1807 እ.አ.አ. ነበር። የዚህ ሕግ ዋና ዓላማ በብሪታንያ ግዛቶችና መርከቦች አማካኝነት በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል የሚደረገውን አሰቃቂ የባሪያ ንግድ በሕግ ማገድ ነበር።
ይሁን እንጂ፣ ይህ የ1807ቱ ሕግ የባሪያ ንግድን ወይም መሸጥ እና መግዛትን እንጂ ሰዎችን በባርነት መያዝን ወይም ባርነትን ሙሉ በሙሉ አላገደም ነበር። በወቅቱ በባርነት ተይዘው የነበሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ የወጡት ከ26 ዓመታት በኋላ በ1825 ዓ.ም (1833 እ.አ.አ.) በወጣው ሌላ ተጨማሪ አዋጅ አማካኝነት ነው። ሕጉን ለማስከበርም የብሪታንያ የባህር ኃይል በአፍሪካ የባህር ዳርቻዎች ላይ ጥበቃ በማድረግ የባሪያ መርከቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉና የመርከብ አዛዦችም ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ተደንግጎ ነበር።
ለዚህ ታሪካዊ ሕግ መውጣት እንደ ዊሊያም ዊልበርፎርስ ያሉ ታዋቂ ግለሰቦች ለብዙ ዓመታት በፓርላማ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ትግል አድርገዋል። ይህ የብሪታንያ እርምጃ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትም ተመሳሳይ ሕጎችን እንዲያወጡና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጅ ንግድ እንዲቆም መንገድ የከፈተ ትልቅ ኩነት ሆኖ ተመዝግቧል። በኢትዮጵያም ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ በ1916 ዓ.ም የወጣው የተፈሪ መኮንን አዋጅ ከዚህ ዓለም አቀፋዊ የነፃነት ንቅናቄ ጋር ተመሳሳይ ዓላማ ነበረው ይላል ከብሪታንያ ብሔራዊ የመረጃ ቋት (አርካይቭ) ያገኘነው መረጃ።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


