ጦርነቱ ያስከተለዉ ቀውስ

0
105

በዓለም ታሪክ ላይ ጦርነት እንደ መፍትሔ ተቆጥሮ ብዙ ጊዜ ተካሂዷል፤ እውነታው ግን ጦርነት መፍትሔ ሳይሆን ለሰው ልጅ የሚያመጣው ሰቆቃ፣ ፍርሃት፣ ረሃብ፣ መፈናቀል፣ ዘላቂ ቁስል እና በአጠቃላይ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ነው፡፡

ጦርነት የሚያጠፋው ሕይወትን ብቻ አይደለም፤ ተስፋን ያጠፋል፣ ቤተሰብን ያፈርሳል፣ ሕልምን ባዶ ያስቀራል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነትም የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ፣ በርካቶችን ለአካል ጉዳት እየዳረገ፣ መሠረተ ልማቶችን እያወደመ፣ ሀገራትን ወደኋላ እየጎተተ ቀጥሏል፡፡

አሜሪካ እና እስራኤል እ.አ.አ የካቲት 28 ቀን 2026 (የካቲት 21/2018 ዓ.ም.) ኢራንን ማጥቃት ከጀመሩ በኋላ በኢራን፣ በእስራኤል እና በተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ ግዛቶች  ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ (23ኛ ቀን) ፍንዳታዎች መሰማታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ቴህራን በእስራኤል እና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ በርካታ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ሚሳኤል  በማስወንጨፍ በድሮን ምላሽ እየሰጠች ነው፡፡

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ለዐሥርት ዓመታት ወታደራዊ ካምፖችን ስትቆጣጠር ቆይታለች፡፡ እንደ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ዘገባ አሜሪካ በክልሉ ውስጥ ቢያንስ በ19 ቦታዎች ላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ የሆኑ ሰፊ ወታደራዊ ጣቢያዎች አሏት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ስምንቱ በባሕሬን፣ ግብፅ፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኙ ቋሚ የጦር ሰፈሮች ናቸው፡፡

እ.አ.አ እስከ 2025 አጋማሽ ድረስ በመካከለኛው ምሥራቅ ከ40 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርሱ የአሜሪካ ወታደሮች በነዚህ ጣቢያዎች ሰፍረዋል፡፡ ከፍተኛ የአሜሪካ ወታደሮች ያሏቸው ሀገራትም ኳታር፣ ባሕሬን፣ ኩዌት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ለአሜሪካ የአየር እና የባሕር ኃይል ሥራዎች፣ ለክልላዊ ወታደር ትጥቅ፣  ስንቅ እና  መጓጓዣ አቅርቦት /ሎጂስቲክስ/፣ ለስለላ እና ለኃይል ትንበያ ወሳኝ ማዕከላት ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ታዲያ እነዚህን የጦር ሰፈሮች ነው ኢራን እየደበደበች የምትገኘው፡፡

የአሜሪካ ጦር ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ የኢራንን ከአምስት ሺህ በላይ ዒላማዎችን መምታቱን በአካባቢው የሚገኙትን የአሜሪካ ጦር ኃይሎች የሚቆጣጠረው የአሜሪካ ማዕከላዊ ኮማንድ (CENTCOM) አስታውቋል፡፡ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ኮርፕስ (IRGC) በበኩሉ  የአሜሪካ ወታደሮች በሚሰማሩባቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ቢያንስ 27 የጦር ሰፈሮችን እንዲሁም በቴል አቪቭ እና በሌሎች የእስራኤል ክፍሎች በሚገኙ የእስራኤል ወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል፡፡ እስካሁን ድረስ ኢራን በባሕሬን፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽማለች፡፡

እ.አ.አ እስከ መጋቢት 23ቀን 2026 ድረስ በየሀገራቱ ውስጥ የተከሰቱት የተረጋገጡ ጉዳቶችን አልጀዚራ የዘገበ ሲሆን በኩዌት አንድ ሰው ሲሞት 32 ቆስለዋል፡፡ በሊባኖስ እስራኤል ሄዝቦላን ለማጥፋት ሰፊ ጥቃት ከፈጸመች ወዲህ በሀገሪቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አንድ ሺህ በላይ መሆኑን የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር አስታውቋል፡፡

ሕፃናት ጦርነትን አያስነሱም፣ አይወስኑም፣ አይመሩም፤ ነገር ግን ከፍተኛውን ዋጋ  ይከፍላሉ፡፡ በሊባኖስም ከተገደሉት መካከል   አንድ መቶ አስራ ስምንት የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፡፡ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችም ቆስለዋል፡፡ ጦርነቱ ከጀመረ በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን ነው ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው ያስታወቀው፡፡

በኢራቅ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የኦማን የዜና ወኪል የደኅንነት ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለት ድሮኖች የዱክም ወደብን ዒላማ አድርገው አንድ የውጭ ዜጋ ሠራተኛን አቁስለዋል፡፡ በኋላ ላይ የኦማን የባሕር ኃይል ደኅንነት ማዕከል እንዳስታወቀው የፓላው ሰንደቅ ዓላማ የያዘ የነዳጅ መርከብ ከኦማን ሙሳንዳም ግዛት ዘጠኝ ኪ.ሜ ርቀት ላይ ጥቃት ደርሶበት አራት ሰዎች ቆስለዋል፡፡ በኦማን ሶሃር ግዛት አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን ከወደቀ በኋላ ሁለት ሰዎች ሞተዋል፡፡

የኳታር የውስጥ ጉዳይ ሚኒሥቴር የቆሰሉት ሰዎች ቁጥር 16 መሆኑን አረጋግጧል፡፡ አብዛኛዎቹ ጉዳቶች የደረሱት  በወደቁ የሚሳኤል ቁርጥራጮችና ፍርስራሾች ሲሆን አንድ ሰው ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በሀገሪቱ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥርዓታቸውን ወደ ርቀት ትምህርት ቀይረዋል፡፡

 

ሳዑዲ አረቢያ በማዕከላዊው የአል ካርጅ ግዛት በአንድ የመኖሪያ አካባቢ ላይ  ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እና 12 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጻለች፡፡ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ቢያንስ ስምንት ሰዎች ከፓኪስታን፣ ኔፓል እና ባንግላዲሽ የመጡ ዜጎችን ጨምሮ መሞታቸው ተረጋግጧል፤ 157 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ሁለት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወታደሮችም በተጠናቀቀው ሳምንት ሄሊኮፕተራቸው በቴክኒክ ችግር ምክንያት ከተከሰከሰ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉ የመከላከያ ሚኒሥትሩ ተናግረዋል፡፡

የአሜሪካ ጦር በአካባቢው በተፈፀመው የኢራን ጥቃት 13 ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም አንድ የጦር ሰራዊት አባል በኩዌት ከጤና ጋር በተያያዘ አደጋ ሕይወቱ አልፏል፡፡ መጋቢት 13 ቀን 2026 በምዕራብ ኢራቅ አንድ የአሜሪካ ነዳጅ መሙያ አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ ስድስቱም የመርከብ አባላት መሞታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

መጋቢት መጀመሪያ ላይ  የኢራን ባላስቲክ ሚሳኤል በማዕከላዊ እስራኤል በፈጸመው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎችን ገድሎ ከ20 በላይ ሰዎችን አቁስሏል፡፡ በአጠቃላይ በኢራን በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 15 እስራኤላዊያን ተገድለዋል፤ ከ3ሺህ በላይ ደግሞ ቆስለዋል፡፡

የኢራን የጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር እንዳስታወቀው ጥቃቱ ከተጀመረበት ከየካቲት 28/ 2026 ጀምሮ በአሜሪካ እና በእስራኤል በኢራን ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ቢያንስ 3ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል፤ 18ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ያህል ኢራናዊያን ደግሞ የውስጥ መፈናቀል ደርሶባቸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ  የኢራን አብዮታዊ ዘብ እንዳስታወቀው ኢራን በአንድ ቀን ብቻ በእስራኤል ላይ አንድ መቶ ጥቃቶችን ሰንዝራለች፡፡ ጥቃቱም በእስራኤል  ለተገደሉት ራስ ገዝ የደኅንነት መሪ አሊ ላርጃኒ የተሰጠ አፀፋ ነው፡፡ በአፀፋ ጥቃቱ ኮሮማሻር-4፣ ቃድር፣ ኤማድ እና ኬባር ሼካን ሚሳኤሎች ጥቅም ላይ መዋላቸው ተገልጿል፡፡ ጥቃቱ ከቴል አቪቭ በተጨማሪ በሀይፋ ወደብ፣ ኢየሩሳሌም እና ቤርሳቤህ ከተሞች በሚገኙ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ነው የተፈጸመው፡፡ በጥቃቱም 192 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 11 ሰዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የእስራኤል ጤና ሚኒስቴር አረጋግጧል፡፡

በመሠረተ ልማት ላይ የደረሰ ጉዳት

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በኢራን ቢያንስ 13 ሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት ተመትተዋል፡፡ ስድስት ሆስፒታሎች  ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው 18 ጥቃቶች በጤና ዘርፉ ላይ የተፈጸሙ ናቸው፡፡ በብዙ ከተሞች (ቴህራን፣ፓራንድ፣ሚናብ ) ትምህርት ቤቶች ተመትተዋል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ሕግ “የጦር ወንጀል” ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡ 20ሺህ የሲቪል ሕንፃዎች ተጎድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 16ሺህ  የመኖሪያ ቤቶች ናቸው፡፡ የነዳጅ እና ጋዝ ተቋማት (South Pars)፣ የውኃ አቅርቦት ፋብሪካ ተጎድቶ በ30 መንደሮች ውኃ ተቋርጧል፡፡ በአጠቃላይ ከ15ሺህ በላይ የወታደራዊ እና ሌሎች ቦታዎች ዒላማ ተደርገዋል፡፡ በጦርነቱ ኢራን ከሦስት እስከ አራት ቢሊዮን ዶላር  ወጪ ማድረጓን ልብ ይሏል፡፡

በሊባኖስ ድልድዮች ወድመዋል፤  በሰሜናዊው የሀገሪቷ ክፍል በርካታ መንደሮች እና ቤቶችም ተጎድተዋል፡፡ በባሕረ ሰላጤው (ገልፍ) ሀገሮች (በኳታር እና በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ) የኢራን የጋዝ መሠረተ ልማቶች እና  የነዳጅ ስፍራዎች ተጎድተዋል፡፡

ኢራን በእስራኤል ላይ የክላስተር ሚሳኤል ጥቃት ካደረሰች በኋላ የሲቪል እና መሠረታዊ አውታር መረቦች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እስራኤል በዚህ ጦርነት  ሦስት ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በጉዳቱ የንግድ መቆምን፣ የሥራ ገደብን፣ የትምህርትቤት መዘጋትን እና ለተጠባባቂ ጦር የወጡ ወጪዎችን  ያካትታል፡፡ አሜሪካም በዚህ ጦርነት የምታወጣው ወጪ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የአሜሪካ ዲፌንስ ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የ800 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት ማድረሷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

 

የነዳጅ ዋጋ መናር

የዓለማችን 20 በመቶ የነዳጅ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በመዘጋቱ በአሁኑ ጊዜ የአንድ በርሜል የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ ከአንድ መቶ አስራ ሁለት ዶላር በላይ ሆኗል፡፡ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የኀይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ናቸው፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያን እያናጋ ነው፡፡

ከአሜሪካዊያን  ጀምሮ እስከ አውሮፓ ፋብሪካዎች እና የእስያ ኢኮኖሚዎች ድረስ ተፅዕኖው እየተሰማ ነው፡፡ ይሁንና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “የነዳጅ ዋጋ መጨመር ለደኅንነትና ለሰላም የሚከፈል በጣም ትንሽ ዋጋ” ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ባለሀብቶች ግጭቱ ከቀጠለ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ እንደሚሄድ  እያስጠነቀቁ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም ድርጅት ባወጣው መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ በነዳጅ ዋጋ መጨመር፣ ለእርዳታ መንገዶች መዘጋት እና በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ከ318 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ አሃዙ 350 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ነው ያስጠነቀቀው፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝን ሰርጥ የማትከፍት ከሆነ የኃይል ማመንጫዋን እንደምታወድም ዝታለች፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 14  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here