“ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ ማስተላለፍ ትልቅ ርካታ ይሰጠኛል”

0
277

የዚህ እትም የበኩር እንግዳችን አቶ ያረጋል ገረመው ይባላሉ። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የስራ መደቦች እና በኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩ፣ የባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ቤተ መዘክርን እንዲሁም የቀድሞ ተማሪዎች ማህበርን የመሠረቱ፣    በስፖርቱ ዘርፍም የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ምስጉን እና ታታሪ ስብዕና ያላቸው የሀገር ባለውለታ ናቸው። ደራሲም ናቸው’  ስላበረከቱት አስተዋጽኦ የሚከተለውን መረጃ አጋርተውናል።

መልካም ንባብ!

አቶ ያረጋል በቅድሚያ ስለ ልጅነትዎና የትምህርት ዘመንዎ እናውጋ?

የተወለድኩት በ1948 ዓ.ም ነው። ትውልዴ አሁን ጎንጅ ቆለላ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ ሲሆን  (ከአዴት አቅራቢያ) ትልቅ ወንድሜን  ተከትዬ ነው ወደ ባህር ዳር የመጣሁት። ልክ የዛሬ 60 ዓመት ገደማ መጋቢት ወር ላይ እንደመጣሁ ትዝ ይለኛል። በ1957 ትምህርቴን በሠርጸ ድንግል ትምህርት ቤት ጀምሬያለሁ። ያጠናቀቅኩት ደግሞ በ1969 ዓ.ም ነው።

ወደ ስራው ዓለም እንዴት ገቡ?

ስራ የጀመርኩት በ1971 ዓ.ም ፔዳ ነበር። መጀመሪያ የተቀጠርኩት በንብረት ክፍል ውስጥ በጸሐፊነት ነው። ለሰባት ወር ያህል ከሰራሁ በኋላ በንብረት አያያዝ ላይ በነበረ ክፍተት ምክንያት የእቃ ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኘ ተሾምኩ። በወቅቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥተውኝ አየር መንገድ ድረስ ሄደን የንብረት አያያዝ ተምረን መጣን። እኔም ያንን ልምድ ተጠቅሜ ዘመናዊ እና የተደራጀ የንብረት አያያዝ ስርዓት ዘረጋሁ።

ስራዬን እየሰራሁ ትምህርቴን መማር ጀመርኩ። በ1977 ዓ.ም በሂሳብ ትምህርት ዲፕሎማዬን አገኘሁ። ከዚያም በዲፕሎማዬ በዚያው ተቋም ውስጥ ረዳት መምህር ሆኜ ማስተማር ጀመርኩ። ትምህርቴን ሳላቋርጥ ቀጥዬ በ1984 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪዬን በሂሳብ ትምህርት ማግኘት ቻልኩ።

የፖሊቴክኒክ  ተቋምን ታሪክ የሚዘክር ቤተ መዘክር የማቋቋም ሐሳብ እንዴት መጣ?

ሐሳቡ የመነጨው በ2005 ዓ.ም. አካባቢ ነው። እኔ በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ አስተባባሪ ሆኜ እሠራ ነበር። ያኔ ዶክተር ፀሐይ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ነው የተቋሙ ታሪክ መጥፋት የለበትም በሚል ከእሳቸውና ከሌሎች ሁለት ጓደኞቼ ጋር ሆነን የጀመርነው። በኋላ ግን አጋሮቼ በተለያየ ምክንያት ተለዩኝ። አንዱ አዲስ አበባ ተቀየረ፤ አንዱ ደግሞ በሞት ተለየ። እኔ ግን ኃላፊነቱን ብቻዬን ወስጄ ቤተ መዘክሩን የማደራጀቱን ሥራ ገፋሁበት። በ2008 ዓ.ም. ጡረታ ብወጣም፣ ዩኒቨርሲቲው ሥራውን እንድቀጥል ስለፈለገ በውል መልሶ ቀጠረኝ።

ቤተ መዘክሩን ለማደራጀት ምን ዓይነት መረጃዎችን እና ቅርሶችን ማሰባሰብ ነበረባችሁ?

መጀመሪያ ሬጅስትራር በመሄድ የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች ፎቶግራፍ እና የግል መረጃ አሰባሰብን። ያንን መረጃ አውጥቶ ለማደራጀት ብቻ ሦስት አራት ወራት ፈጅቶብናል። ከዚያም ከመጀመሪያው ዲን ጀምሮ ያሉትን መሪዎች ፎቶግራፍ አደራጀን። በተጨማሪም የቀድሞ ተማሪዎች የሠሯቸው መኪናዎች፣ ሞተሮች እና የጥጥ ማጽጃ መሣሪያዎች በተለያዩ ክፍሎች ተበታትነው ነበር፤ እነርሱን ሰብስበን በአንድ ቦታ አስቀመጥን። የኢትዮጵያንና የራሺያን የ125 ዓመት ግንኙነት የሚገልጹ ሰነዶችንም አካትተናል።

ቤተ መዘክሩን እነማን ጎበኙት?

ቤተ መዘክሩ በየዓመቱ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ይጎበኛል። በተለይ በ2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት በዓል ላይ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል። ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር የሚመጡ እንግዶች፣ ሚኒስትሮች እና አምባሳደሮች ይጎበኙታል። ለምሳሌ የራሺያ አምባሳደር መጥተው ሲጎበኙ፣  “ይህ ኮሌጅ የኢትዮጵያ ኩራት ነው” ብለው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የብሪቲሽ ካውንስል እና ሌሎች አምባሳደሮችም በመዝገባችን ላይ የሚደነቅ አስተያየት አስፍረዋል።

ቤተ መዘክሩ ለወጣቱ ትውልድ እና ለባህር ዳር ከተማ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?

ቤተ መዘክሩ ለወጣቱ ትውልድ በተለይም ለቴክኖሎጂ ተማሪዎች የፈጠራ ተነሳሽነት ይፈጥራል። የቀድሞ ተማሪዎች ያለ ቴክኖሎጂ በእጃቸው የሠሯቸውን መሣሪያዎች (ማሽኖች) ሲያዩ “እኛም መሥራት እንችላለን” የሚል ተስፋ ያገኛሉ። ለባህር ዳር ከተማም ትልቅ የታሪክ ማዕከል ነው። ከተማዋና ዩኒቨርሲቲው የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም መጥተው ታሪካቸውን እንዲያውቁ ዕድል ይፈጥራል። ቤተ መዘክሩ የታሪክ ብቻ ሳይሆን የልምድ ልውውጥ ማዕከልም ነው።

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የባህል ማዕከልን በማቋቋም በኩልም የእርስዎ ስም ይነሳል። ያ ሂደት እንዴት ነበር?

በ2006 ዓ.ም አካባቢ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የባህል ማዕከል በመዋቅር ሲደራጅ የመጀመሪያው ኃላፊ ሆኜ ተሾምኩ። የባህል ማእከሉ እንዲለወጥ በትጋት ሰርቻለሁ። ጡረታ ከመውጣቴ በፊት ማዕከሉ አሁን ላለው ቅርጽ መሰረት እንዲጥል የበኩሌን አበርክቻለሁ።

ከቀድሞ ተማሪዎች ጋር ያላችሁ ትስስር እንዴት ነው?

በጣም ጠንካራ ነው። የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር እንዲቋቋም  ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ከአሜሪካና ከአዲስ አበባ የመጡ የቀድሞ ተማሪዎች እዚህ መጥተው ለሳምንታት ቆይተው ቤተ መዘክሩን ጎብኝተዋል። እነርሱ ለቤተ መዘክሩ እድገት ትልቅ አቅም ናቸው። ምክንያቱም ተቋሙንና ቅርሶቹን በጥሩ ሁኔታ ስለሚያውቁና ትዝታቸው ስለሆነ ነው።

ከሙያዎ ውጪ በስፖርቱ ዘርፍ በተለይም በእግር ኳስ ረገድ ትልቅ ስም አለዎት። እስኪ ስለዚህ ታሪክዎ ያጫውቱን?

ስፖርት ሕይወቴ ነው። ፔዳ  በነበርኩበት ጊዜ ለኮሌጁ ቡድን እጫወት ነበር። በኋላም ባህር ዳር ከነማ ሲመሰረት በከፍተኛ ሁለት ሊግ ለቡድኑ ተጫውቻለሁ። እንዲያውም “ወዛደር” የሚባል ክለብ አቋቁሜ፣ የክለቡ ፕሬዚዳንትም ተጫዋችም ሆኜ ስንቀሳቀስ ነበር። ሰዎች “እንዴት አንድ ሰው ፕሬዚዳንትም ተጫዋችም ይሆናል?” እያሉ ይገረሙ ነበር። ከዚያም ባለፈ “ጣና ባህር ዳር” የተባለ የህጻናትና ወጣቶች ፕሮጀክት አቋቁመን ብዙ ጎበዝ ልጆችን አፍርተናል።

ጡረታ ከወጡ በኋላ ምን እየሰሩ ነው?

ጡረታ ከወጣሁ በኋላ ዝም ብዬ አልተቀመጥኩም። በባህር ዳር ከተማ የፖሊ ቤተ መዘክርን በማደራጀት ላይ እና በቀድሞ ተማሪዎች ማህበር ውስጥ በንቃት እየተሳተፍኩ ነው። ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ ማስተላለፍ ትልቅ ርካታ ይሰጠኛል። በዩኒቨርሲቲው ቆይታዬም ሆነ በውጪው ስራዬ ብዙ ሰዎችን ማገልገሌ ደስታ ይፈጥርልኛል።

እስኪ በትዳርዎ ዙሪያ ይንገሩን?

ከውድ ባለቤቴ ሲስተር ተዋበች ጋር በ1992 ዓ.ም ትዳር መስርተን 25 ዓመታትን በፍቅር ኖረናል፤ አንድ ልጅ አለን። ትዳራችን በፍቅር በመተሳሰብ እና በመከባበር የተሞላ ነው። እኔ ላሳካሁት ነገር ሁሉ የውድ ባለቤቴ አስተዋጽኦ ትልቅ ነው’

አንድ መጽሐፍ እንደደረሱም መረጃ አለን እናም በዚህ ዙሪያ ይንገሩን?

አዎ! አንድ መጽሐፍ አሳትሜለሁ፤ ርእሱ አቮካቦት ይባላል፤ የባህር ዳርን ታሪክ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው’ ባህር ዳርን በጣም ስለምወዳት ነው የጻፍኩት፤ መቼም በባህር ዳር አልደረደርም’ እንደው ሌላ ሀገር ወጣ ስል እንኳ ፈርሳ የምትጠብቀኝ መስሎ ነው የሚሰማኝ’ እናም ታሪኳን በመጻፌ ክብር ይሰማኛል፤ በቅርቡም አንድ መጽሃፍ ለማበርከት በዝግጅት ላይ ነኝ’

ከወጣቱ ምን ይጠበቃል?

ወጣቱ አሁን ያለውን የቴክኖሎጂ እድል ተጠቅሞ እውቀቱን ሊያሰፋ ይገባል። እኛ በነበርንበት አስቸጋሪ ወቅት እንኳን ተስፋ ሳንቆርጥ ተምረን እዚህ ደርሰናል። ስለዚህ ጠንክሮ  ለሀገር የሚጠቅም ስራ መስራት ያስፈልጋል። ታሪክ ካልተመዘገበ ይጠፋል፤ እኛ ግን ይህ እንዳይሆን የበኩላችንን አድርገናል።

ስላካፈሉን መረጃ ከልብ  እናመሰግናለን!

እኔም አመሰግናለሁ!::

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የመጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here